የ2005 ፕሪምየር ሊግ አሸናፊው አሰልጣኝ ንጉሤ ደስታ ሲታወሱ

አሰልጣኝ ንጉሤ ደስታ ከዚህ ዓለም የተለዩት በዚህ ሳምንት የዛሬ ሁለት ዓመት ግንቦት 27 ቀን 2010 ነበር። ይህንን ምክንያት በማድረግም ሶከር ኢትዮጵያ የቀድሞውን ተጫዋች እና አሰልጣኝ በተለያዩ ፅሁፎች ታስባለች።

በትግራይ ክልል ማይጨው ከተማ የተወለዱት ንጉሤ ደስታ የእግርኳስ ሕይወታቸውን በተወለዱበት ማይጨው ጀምረው ለመከላከያ ሠራዊቱ 16ኛ ክፍለጦር በኋላም ለምድር ጦር ለረጅም ዓመታት ተጫውተዋል። በመከላከያ የአሰልጣኝነት ሕይወታቸውን የጀመሩት ንጉሴ የአሥራት ኃይሌ ምክትል በመሆን ያገለገሉ ሲሆን በአዲሱ ሚሌንየም (2000) አሰልጣኝ አሥራትን በመተካት የመከላከያ ዋና አሰልጣኝ ሆነዋል። አሰልጣኙ በመከላከያ ባለ ክህሎት ተጫዋቾችን በማሰባሰብ ማራኪ እግርኳስ የሚያሳይ እና ውጤታማ ቡድን መስራት የቻሉ ሲሆን እስከ 2002 የውድድር ዓመትም በክለቡ ቆይተዋል።

ከጦሩ ቆይታ በኋላ በ2003 በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያሳለፉት አሰልጣኝ ንጉሤ በ2004 አጋማሽ አየር ኃይልን ከክፍሌ ቦልተና በመረከብ እስከ ዓመቱ መጨረሻ መርተዋል። በመቀጠልም በ2005 አጋማሽ ደደቢትን ከአብርሀም ተክለኃይማኖት በመረከብ ክለቡ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን እንዲያነሳ አድርገዋል። በቀጣዩ ዓመት (2006) ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስን 2-1 በማሸነፍ የኢትዮጵያ ዋንጫን ከደደቢት ጋር ማንሳት ችለዋል።

በ2007 ከደደቢት ጋር ጥሩ ጅማሮ ያደረጉት አሰልጣኙ ኋላ ላይ በተከታታይ ሽንፈቶች በማስተናገዳቸው ከቡድኑ ጋር የተለያዩ ሲሆን በ2008 በከፍተኛ ሊግ ተወዳዳሪ የነበረው ወልዲያን በመረከብ ከምድባቸው ሁለተኛ በማጠቃለያ ጨዋታ ደግሞ 3ኛ ደረጃ በመያዝ ወደ ፕሪምየር ሊግ መልሰውታል። ወልዲያ በ2009 በፕሪምየር ሊጉ ጥሩ ዓመት ሲያሳልፍም ጠጣር እና በቀላሉ ጎሎች የማያስተናግድ ቡድን ገንብተው ነበር። ሆኖም በውድድር ዓመቱ መጠናቀቂያ ወራት ከክለቡ ጋር ተለያይተው ወደ ቀድሞ ክለባቸው ደደቢት ተመልሰዋል።

በ2010 የደደቢትን ተፎካካሪነት በመጠኑ የመለሱት አሰልጣኙ የመጀመርያውን ዙር በመሪነት ቢጨርሱም በሁለተኛው ዙር በተጣለባቸው የሦስት ወራት ቅጣት እና የቡድኑ አቋም መውረድ ከደረጃቸው ተንሸራተዋል። በመጨረሻም ከቅጣት መልስ ቡድኑን አንድ ጨዋታ ከመሩ በኋላ ደደቢት በሀያ አምስተኛው ሳምንት አርባምንጭን ለመግጠም ሲዘጋጅ ከጨዋታው ቀን በፊት ጨጓራዬን አሞኛል ብለው ወደ ህክምና ከሄዱ በኋላ ባልታወቀ ምክንያት ግንቦት 27 ቀን ምሽት ላይ በድንገት ሕይወታቸው አልፏል። ከሁለት ቀናት በኋላም (ግንቦት 29) በትውልድ ሥፍራቸው ማይጨው ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈፅሟል።

*በቀጣይ ፅሑፎች ከንጉሤ ደስታ ጋር አብረው የሰሩ ተጫዋቾች እና ባለሞያዎች ያላቸውን ትውስታ ይዘን እንቀርባለን።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ