በኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ እና በአሰልጣኝ አምሳሉ ፋንታሁን አማካኝነት በሀገራችን ላሉ አሰልጣኞች ስልጠና ከቀናት በኃላ መሰጠት ይጀምራል፡፡
በኮሮና ወረርሺኝ የተነሳ በሀገራችን ያሉ የእግር ኳስ ውድድሮች በያዝነው አመት ሙሉ በሙሉ መሰረዛቸው ይታወሳል፡፡ በዚህም ምክንያት ክለቦች ተጫዋቾቻቸውን እና አሰልጣኞቻቸውን በመበተናቸው ከእግር ኳሱ ያለፉትን ሁለት ወራት በላይ ለመራቅ ተገደዋል፡፡ ከሰሞኑ ግን ለአሰልጣኞች ጥሩ ሳምንት ያለፈ ይመስላል በአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ አማካኝነት አሰልጣኞች በየቤታቸው በሚሆኑበት ወቅት አሰልጣኞች የዘመናዊ የቪዲዮ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ስለ ቴክኖሎጂው፣ ስለ ኮሮና ቫይረስ እና ስለ ቀጣዩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዙሪያ ከፕሪምየር ሊጉ እና ከአንዳንድ የሀገሪቱ አሰልጣኞች ጋር ለመቀራረብ ይረዳ ዘንድ ባሳለፍነው ሳምንት ለሁለት ጊዜያት ያህል የቪዲዮ ስብሰባን ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
በበርካታ አሰልጣኞች ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ የመጣው የዚህ የቪዲዮ ግንኙነት አሁን ከውይይት ባለፈ ወደ ስልጠና በማደግ ከቀናት በኃላ በሁለት ትልልቅ አሰልጣኞች በሀገራችን ላሉ አሰልጣኞች ስልጠናን ለመስጠት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል፡፡ ስልጠናው በሀገራችን ውስጥ ላሉ የፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች በዋናነት የተዘጋጀው ሲሆን በሴቶች እግር ኳስ ላይ ለተሰማሩ አንድ አንድ አሰልጣኞችንም እንደሚያካትት ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡
ይህ ስልጠና በካፍ ኢንስትራክተር እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአሰልጣኝ አብረሀም መብራቱ የተዘጋጀ ሲሆን ስልጠናውም በዋናነት በኢንስትራክተሩ ይሰጣል። በተጨማሪም በርካታ ኢትዮጵያዊያን አሰልጣኞችን ወደ አሜሪካ እና ስፔን ተጉዘው ስልጠና እንዲሰለጥኑ ከዚህ ቀደም ሲያመቻቹ የነበሩት በአሜሪካ የሳክሬም የእግር ኳስ አካዳሚ የሴቶች ዳይሬክተር እና አሰልጣኝ አምሳሉ ፋንታሁን አማካኝነት ከአስር ቀናት በኃላ ይሰጣል ተብሏል፡፡ ስልጠናው በዋናነት አሰልጣኞች ራሳቸውን በዚህ ኮረና ወቅት ማሻሻል ባለባቸው እግር ኳሳዊ ሀሳቦች ላይ ትኩረቱን የሚያደርግ ሲሆን የአሰልጣኝነት ብቃት ላይም ያውጠነጠነ እንደሚሆን ሰምናል፡፡
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ