የቀድሞው አንጋፋ ዳኛ እና ኮሚሽነር ጌታቸው ገ/ማርያም በዳኞች ገፅ…

ሶከር ኢትዮጵያ የእናንተ ቤተሰቦቻችንን የመረጃ ፍላጎት ለማርካት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ አምዶችን በመክፈት ፁሑፎችን ስታደርስ መቆየቷ ይታወሳል። በዛሬው ዕለትም የእግርኳሱ አንድ ወሳኝ አካል የሆኑት ዳኞችን በተመለከተ የምትዳስስበትን አምድ ጀምራለች። በዚህ አምዳችን የቀድሞቹ ዳኞች ከአሁኖቹ ዳኞች ድረስ ይዳሰሳሉ፣ ልምዳቸውን ያካፍላሉ፣ በዳኝነት ዘመናቸው ያጋጠማቸው አዝናኝ እና አስተማሪ ገጠመኞች እና መልዕክቶች ይቀርባሉ። በዕለተ ዓርብ ወደ እናንተ በሚደርሰው የዳኞች ገፅ በዛሬው የመክፈቻ ፁሑፋችን የቀድሞ አንጋፋ ዳኛ እና ኮሚሽነር ጌታቸው ገ/ማርያምን ይዘን ቀርበናል።

ትውልድና ዕድገታቸው በአዲስ አበባ ኳስ ሜዳ አካባቢ ነው። ለነጮች መጫወቻ ጃን-ሜዳ ሲፈቀድ ለጥቁር መጫወቻ እንዲሆን በተፈቀደው በሽቦ በታጠረ ሜዳ ላይ እግርኳስን እየተጫወቱ አድገዋል። በእግርኳስ ህይወታቸውም ከ1952–56 ለኦሜድላ ተጫውተዋል። በመቀጠል የወታደር ቡድን ከእግርኳሱ ይውጣ ተብሎ ሲወሰን በ250 ብር ወደ ድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ አምርተው ከ1959–64 መጫወት ችለዋል። አዲስ አበባ በነበሩበት ወቅት ለአዲስ አበባ ምርጥ፤ በድሬዳዋ ደግሞ ለሐረርጌ ምርጥ ተጫውተዋል። ኢትዮጵያ አስተናግዳ ዋንጫውን ባስቀረችው በሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቡድን ውስጥ ጥሪ ተደርጎላቸው ለአንድ ወር በዊንጌት ትምህርት ቤት ሲዘጋጁ ቢቆዩም “ከእኔ የሚበልጡ ተጫዋቾች በወቅቱ የነበሩ በመሆኑ ያለ ምንም ቅሬታ ተቀንሻለሁ።” ሲሉ ወቅቱን ያስታውሳሉ።

በ1964 እግርኳስ መጫወት ሲያቆሙ በክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ግፊትና ጥቆማ “አንተ ዳኛ እንጂ አሰልጣኝ መሆን አትችልም” የሚል ምክር ሰምተው ወደ ስልጠናዎችን በመውሰድ ወደ ዳኝነቱ ጎራ ተቀላቅለዋል። ሐረር ላይ ቅዱስ ሚካኤል ከወቅቱ ጠንካራ ቡድን ኢትዮ ሴሜንት ጋር ያደረገለትን ጨዋታ በመምራት “ሀ” ብለው የጀመሩት ዳኝነትም በሦስት ዓመት ውስጥ እስከ ኢንተርናሽናል ዳኝነት ማዕረግ አድርሷቸዋል። እግርኳስን ተጫውቶ ማለፋቸውም በፍጥነት ከፍተኛ እድገት አግኝተው ኢንተርናሽናል ዳኛ ለመሆን እንዳበቃቸውም ይታመናል።

በየትኛውም አጋጣሚ አዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታ ካለ እኚህ ቀልድ አዋቂ ሰው በፍፁም አይታጡም። በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ከነ ገበየሁ ዱቤ፣ አየለ ተሰማ፣ ተስፋዬ ገብረየሱስ ፣ ደመቀ አባተ፣ ኮሎኔል ደነቀ መንግሥቱ፣ ሥዩም ታረቀኝ (ሁሉም በህይወት የሉም) በመቀጠል ሰባተኛ ኢንተርናሽናል ዳኛ በመሆን በ1969 በመሾም አገልግለዋል። በአፍሪካ ውስጥ የተለያዩ ውድድሮችን መምራት የቻሉት ፈርጣማው የእግርኳስ ሰው ለዳኝነት ያልተጓዙባቸው የአፍሪካ ሀገራት ማዳጋስካር እና ቦትስዋና ብቻ እንደሆኑ ይገልፃሉ። ይልቁንም ዩጋንዳ እና ግብፅ ከስምንት ጊዜ በላይ ተመላልሰው ማጫወታቸውን ያስታውሳሉ።

በኢትዮጵያ ዳኞች ታሪክ ቀደምት ዳኞች ከሚባሉት መካከል አንዱ የሆኑት አንጋፋው ሰው በኢንተርናሽናል ዳኝነት ዘመን የሚቆጩት የኦሊምፒክ ውድድር ላይ ጨዋታ እንዲመሩ ተመርጠው የቀሩበት መንገድ እንደሆነ ይገልፃሉ። በዳኝነት ህይወታቸው የማይረሱት አጋጣሚ ደግሞ በወቅቱ ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት የሶማሊያ ብሔራዊ ቡድንን በሜዳው ጨዋታ ሲያጫውቱ በፕሬዝደንት ዚያድ ባሬ የንቀት ሰላምታ ቢሰጣቸውም ሀገራቸው ሲመለሱ የጀግና አቀባበል ተደርጎላቸው አሁን የት እንዳለ ባይታወቅም የእጅ ሽጉጥ ከ30 ጥይት ጋር ተሰጥቷቸዋል።

በ16 ዓመት በቆየው በዳኝነት ዘመኑ በሀገር ውስጥ ያላጫወቱት ወሳኝ ጨዋታ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ፈታኝ እና ወሳኝ ጨዋታዎችን በሚዛናዊነት እና በቁርጠኝነት በመዳኘት ይታወቃሉ። ዳኛነቱን ካቆሙ በኃላም ለረዥም ዓመታት ኮሚሽነር በመሆን አገልግለዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በፀጥታ ኮሚቴ ውስጥ እየሰሩ ይገኛሉ። ያለፉትን 20 ዓመታት በአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሸን ውስጥ በስራ አስፈፃሚነት ሲያገለግል መቆየታቸውም ይታወሳል።

ለረጅም ዓመታት ከዳኝነት እስከ ኮሚሽነርነት ያገለገሉት የኢትዮጵያ ዳኞች አባት ጋሽ ጌታቸው ገብረማርያም የመጀመርያ በሆነው የዛሬው የዳኞች ገፅ አምዳችን በዳኝነት ዘመናቸው ያጋጠማቸውን አስገራሚ ገጠመኞች እንዲህ አጫውተውናል።

” 1966 ሚያዚያ ወር ሀማሴን ከኤሌትሪክ አስመራ ላይ ፣ አዲስ አበባ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከእምባሶይራ ጋር ጨዋታ ነበራቸው። በወቅቱ ለዋንጫ የሚፋለሙት ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሐማሴን እና እምባሶይራ ናቸው። ኤሌትሪክ ዕድል አልነበረውም። ጨዋታውን ለመምራት ወደ አስመራ ሄድኩኝ ፤ የሐማሴን ደጋፊዎች ገና ከድሬደዋ ጀምሮ የኤሌትሪክ ተጫዋቾችን አማለው እስከ 3000 ብር እንደሰጡ በኃላ የኤልፓ ተጫዋቾች ራሳቸው መስክረዋል። በፌዴሬሽኑ አንቀፅ መቶ ስልሳ አምስት ላይ ‘ዳኛው ጨዋታው ከአቅም በታች መሆኑን ካመነ በመጀመርያ ሁለቱን አንበሎች ያናግራል። መሻሻል ከሌለ ጨዋታውን ያቆማል ፣ ሆኖም ጨዋታውን ለማቆም ንብረት ይወድማል፣ የሰው ህይወት ይጠፋል ብሎ ካመነ ለሁለቱ ረዳት ዳኞች ነግሮ ጨዋታውን ቀጥሎ በሪፖርት መልክ ያቀርባል።’ ይላል ደንቡ. በዚህ መሠረት ሐማሴኖች ሠላሳ ሺህ ብር ለእኔም ሰጡኝ፤ ተቀበልኩ፤ ብሩን ይዤ ጨዋታውን ጨረስኩ። አዲስ አበባ ስመጣ ብሩን አስረክቤ ሪፖርት አደረኩኝ። የሚገርመው ሐማሴን ውሸት ነው ብለው ቅሬታ አቅርቦ ተከሰስኩ። በወቅቱ ጉዳዩ ከፌዴሬሽኑ ቅሬታ ሰሚ አልፎ እስከ የሀገሪቷ መወሰኛ ምክር ቤት ድረስ ደርሶ ተጠርቼ በመሄድ ያለውን ነገር አስረዳሁ። በመጨረሻም የጨዋታው ውጤት እንዲሰረዝ እና መብራት ኃይልም ፣ ሀማሴንም ተቀጡ። የኢትዮጵያ ሻምፒዮናን እምባሶይራ አሸነፈ። ፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተጠርቼ የዕድሜ ልክ የስታዲየም መግቢያና እና የጣት ቀለበት ተሸለምኩ።

” ሌላ አጋጣሚ ላጫውትህ… በደርግ ዘመን ከመንግስት ለውጥ በኃላ በ1969 ነው። ሶማሊያ ኢትዮጵያን ወራ ጅግጅጋ ድረስ ዘልቃ ነበር። ፊፋ በዚህን ወቅት መቋዲሾ ሄጄ ሶማሊያ ከኒጀር እንዳጫውት መደበኝ። ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ጠርተውኝ “ፊፋ መድቦሀል ግን አንድ የተፈጠረ ነገር አለ” ብለው የወቅቱ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደ ሆኑት ጎሹ ወልዴ ጋር ወሰዱኝ። ያለውን ነገር ካስረዳን በኋላ አቶ ጎሹ ይህ ከእኔ አቅም በላይ ነው በሚል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ጋር ደውለው ከአምስት ቀን በኋላ ቤተመንግስት እንድንገባ ቀጠሮ አስያዙ። ቀኑ ደረሰና ቤተ መንግስት ጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም ፊት ቆምን። ጓድ ጎሹ ወልዴም ያለውን ሁኔታ በዝርዝር አስረድተው ከጨረሱ በኃላ በመቀጠል ጋሽ ይድነቃቸው ” ኢትዮጵያ የፊፋ አባል ሀገር ናት ይህ ልጃችን መቋዲሾ ሄዶ እንዲያጫውት ተመድቧል” ብለው ተናግረው እንደጨረሱ ጓድ መንግስቱ ንዴት በተሞላበት ፊት እያግረጠረጡ ጠረንቤዛውን በመምታት በጣም እየጮሁ “እንዴት!!! የሶማሊያ ወንበዴ የሠራዊታችንን አስክሬን ተረማምዶ ጅግጅጋ ገብቷል፣ ነገ ድሬዳዋ ይገባል ፣ ከነገ ወድያ ደግሞ አዲስ አበባ ይገባል ስንል እንዴት ይሄን ሰው ሞቃዲሾ እንልከዋለን? አይሆንም ” አሉና በቁጣ ቃል ተናገሩ። ትንሽ ቆየት ብለው ጓድ መንግሥቱ “ሌላ ቀን ለምን አይሄድም” አሉ። ክቡር ይድነቃቸውም ተሰማም ” ካልሄደ ሀገራችን ትቀጣለች፣ እርሱም ይቀጣል።” አሉ። ጓድ መንግሥቱ መለስ አሉና ወደ እኔ ዞር ብለው ” ትፈራለህ ወይ?” አሉኝ። “አልፈራም” አልኩ “መልካም መንገድ፤ እዛ ሄደህ ኢሠፓ ነኝ እንዳትል” ብለውኝ ከቤተ መንግስት ወጣሁ። (እየሳቁ)

” የኢትዮጵያ አውሮፕላን እንዳይመታ ተብሎ በጣልያን ሀገር አድርጌ ከኬንያ እና ዩጋንዳ ረዳት ዳኞች ጋር ሶማሊያ ገባው። መቋዲሾ ውስጥ ፋራአዶን የሚባል ዳኛ ኢትዮጵያ ሆቴል የሚባል ከፍቶ ስለ ነበር እዛ አረፍን። የጨዋታው ቀን ደርሶ ወደ ሜዳ ስንሄድ ሁለት ነገር ገጠመን። አንደኛው ቀድሞ የሚጫወቱ ሀገሮች ሰንደቅ አላማ ይሰቀል ነበር። ይገርምሀል የኢትዮጵያን ቀዩን ከላይ አረንጓዴውን ከታች አድርገው ገልብጠው ሰቅለውታል። ይህ የኔ ሀገር መለያ ባንዲራ ባለመሆኑ ይቀየር ብዬ አስለወጥኩ። እንደገና ደግሞ የሚገርመው እንደ ሀዘን ቀን ሰንደቅ አላማውን ዝቅ አድርገው ሰቀሉት። እርሱንም አስተካክሉ ብዬ ተስተካከለ እና ወደ ሜዳ ገብተን ተሰልፈን የዕለቱን የክብር እንግዶች ሠላምታ መለዋወጥ ተጀመረ። የሶማሊያው ፕሬዝደንት ዚያድ ባሬ ቁመቱ ረዥም ነው እንደምታቀው ያስፈራል፣ እኔ ጋር ለሠላምታ ሲደረስ ይገርምሀል ሁለት ጣቱን ብቻ ሰጠኝ እኔን ተጠይፎ  (እየሳቁ)። ትንሽ ተረበሽኩ ግን ትኩረቴን ወደ ጨዋታው አድርጌ ገባው። ሜዳው አጥር የለውም ሶማሌው ከነ ግመሉ ይመለከታል። አቧራው ተወው ልነግርህ አልችልም። ጨዋታው ቀጥሎ በ87ኛው ደቂቃ ላይ ሱማሌ አገባች። በዚህ ሰዓት የደጋፊዎቹ ደስታ ልነግርህ አልችልም። የማልዋሽህ ነገር እንኳን እነርሱ እኔም ተደስቻለው። (በጠም እየሳቁ) ያው ያለቀ ነገር ነው። የጨዋታው መጠናቀቅን በፊሽካዬ እንዳበሰርኩ ተመልካቹ ወደ ሜዳ ገብቶ ተሸክመውኝ እስኪብርቶ፣ ቢጫ እና ቀይ ካርድ የት እንደጠፋ አላውቅም በስንት መከራ ፖሊሶች አላቀውኝ፣ ፊሽካውም ካርዱ ተለቅሞ ተገኘና ተሰጠኝ፤ ወደ ሀገሬም ተመለስኩ። ጓድ መንግሥቱ ቤተ መንግሥት አስጠሩኝ። አሁን አለ ወይስ የለም ብለህ እንዳትጠይቀኝ (እየሳቁ) አንድ ሽጉጥ፣ ከሠላሳ ጥይት ጋር እና አንድ በብራና የተፃፈ የእሳቸው ፊርማ ያለበት ምስክር ወረቀት ተሰጠኝ እልሀለው።

“በመጨረሻም የዳኝነት ህይወቴን ካነሳህ አይቀር የሚያንገበግበኝን አንድ ነገር ላጫውትህ ” የኦሊምፒክ ጨዋታን ለመዳኘት ተመርጬ ነበር። ሆኖም በጊዜው አዲስ አበባ ላይ 31ኛው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ይከበር ነበር። በደርግ ዘመን ማለት ነው። አንድ ኮሚሽነር ነበር አሁን በህይወት የለም መድን እና ጊዮርጊስ እያጫወትኩ በጣም ኃይለኛ ከባድ ዝናብ ይዘንባል። በወቅቱ እነ ጓድ መንግሥቱ፣ ብርሀኑ ባዬ፣ ፍቅረሥላሴ ወግደረስ እና ሌሎች የአፍሪካ መሪዎችም ተቀምጠው ጨዋታውን እየተመለከቱ ነበር። እኔ ደግሞ ጨዋታውን ለማስኬድ ሜዳው ኳስ እንኳን ማንጠር ስላልቻለ ጨዋታውን አቋረጥኩት። ኮሚሽነሩ መጥቶ መቋረጥ የለበትም እንግዶች አሉ አለኝ። “እኔ የፊፋ ዳኛ ነኝ፤ ህጉን አስከብራለው ብዬ በውሳንዬ ፀናው።” ቂም ቋጥረው ፖለቲካ ውስጥ ገብቷል ብለው ለፊፋ ፋክስ አደረጉብኝ ፣ እዚህ ደግሞ በድጋሚ የማይመጡ እንግዶች መሆናቸውን እያወቀ ሆን ብሎ ጨዋታ አቋረጠ ብለው ቅጣት ቀጡኝ። እኔም ሳልሄድ በምትኩ ከግብፅ ተላከ። በዚህም ምክንያት በዳኝነት ህይወቴ የኦሊምፒክ ጨዋታ አለመጫወቴ በጣም ነው የሚቆጨኝ። ”

*በቀጣይ ማክሰኞ በትውስታ አምዳችን አይረሴው የሙሉጌታ ወልደየስ ጉዳት እና የጌታቸው ገ/ማርያም የህክምና ጥሪ ይዘን እንቀርባለን።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ