በታላላቅ የእግርኳስ ሰዎች የተሰጠው የኦንላይን የአሰልጣኞች ስልጠና ትላንት ምሽት ተከናውኗል

በኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ የግል ጥረት እና አስተባባሪነት የተዘጋጀ የማነቃቂያ ስልጠና ትላንት ምሽት ለበርካታ የሃገራችን አሰልጣኞች ተሰጥቷል።

ከጥቂት ቀናት በፊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ለበርካታ ኢትዮጵያዊ አሰልጣኞች እና ኢንስትራክተሮች በቪዲዮ ኮንፍረንስ የታገዘ የምክክር መድረክ አዘጋጅተው ውይይቶች እንዲደረጉ ማመቻቸታቸው ይታወሳል። በተለይ አሰልጣኞች ይህንን የኮሮና ወቅት እንዴት ማሳለፍ እንዳለባቸው፣ እውቀታቸውን በተሻለ ማሻሻል ስለሚችሉባቸው መንገዶችን እና ስለ ቀጣይ የኢትዮጵያ የእግርኳስ ጉዞ ትኩረት በመስጠት ውይይቶች ተደርገው ነበር። ትላንት ምሽት ደግሞ በዙም (Zoom) አማካኝነት በተደረገው የቪዲዮ ኮንፍረንስ ላይ ከ41 በላይ የሃገራችን አሰልጣኞች ከየመኖሪያ ቤታቸው በኮንፍረንሱ ተካፍለው የማነቃቂያ ስልጠናውን ወስደዋል።

12:30 ላይ የጀመረው ይህ ስልጠና በዋነኝነት በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደነበር ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጡት መረጃ ይጠቁማል። የመጀመሪያው ርዕስ የጨዋታ ሞዴልን (Game model) በተመለከተ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የአጨዋወት ዘዴ (Style of play) ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር። እነዚህን ሁለት ርዕሶች ደግሞ ለአሰልጣኞቹ ያብራሩት የካርሎሃ ስፖርት ክለብ የቀድሞ አሰልጣኝ እና የአሁኑ የክለቡ ፕሬዝዳንት ቤንጃሚን ዛይማ ናቸው። ግለሰቡ ለ1 ሰዓት ያክል ማብራሪያውን መቀመጫቸውን ካደረጉበት አሜሪካ ካቀረቡ በኋላ ለ30 ደቂቃዎች የጥያቄ እና መልስ መርሃ ግብር ተከናውኗል። ይህ መርሃ ግብር ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ በቤኔፊካው ምክትል አሰልጣኝ ሬናቶ ፋቢያን አማካኝነት ለ1 ሰዓታት የቆየ የቴክኒክ ስልጠና ተሰጥቷል። ሚስተር ሬናቶ ፖርቹጋል ሊዝበን ከሚገኘው ቢሯቸው ከ2:00 ጀምሮ ከላይ በተጠቀሱት ርዕሶች ላይ ትምህርቶችን ሰጥተዋል።

ሁለቱ ትላልቅ የእግርኳስ ግለሰቦች ከሰጡት አጠቃላይ የ2 ሰዓታት ትምህርት መጠናቀቅ በኋላ ስልጠናውን የወሰዱት የሃገራችን አሰልጣኞች በጥሩ ተሳትፎ ለ30 ደቂቃዎች ያክል ውይይቶችን እና ጥያቄዎችን ሲያንሸራሽሩ እንደነበረ ኢንስትራክተር አብርሃም ገልፀዋል። ከሰዓት ጋር በተያያዘ ግን ከትምህርቱ በኋላ ለተነሱት በርካታ ጥያቄዎች ሚስተር ቤንጃሚን ቀጣይ መልሶችን አሜሪካ ከሚገኘው አሰልጣኝ አምሳሉ ጋር በመነጋገር ምላሾችን እንደሚሰጡ ተገልጿል።

ለ3 ሰዓታት በቆየው የቪዲዮ ኮንፍረንስ ላይ የኢትዮጵያ ወንዶች እና ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች (የሴቶች አሰልጣኞች ለመጀመሪያ ጊዜ)፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ወንዶች እና ሴቶች ብሄራዊ ቡድን የአሰልጣኝ ቡድን አባላት፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ የካፍ ኢንስትራክተሮች እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ተሳትፎ አድርገዋል። ከዚህ ውጪ የካፍ እና የፊፋ ኢንስትራክተር የሆኑት ሚስተር ዶምኒክ ቤንዜማ ኮንፍረንሱን እንደተከታተሉ ታውቋል። በተጨማሪም የአፍሪካ የሴቶች ልማት ኮሚቴ አባል የሆኑት ወ/ሮ መስከረም ትምህርቱን ተካፍለዋል።

ይህንን ስልጠና በመልካም ፍቃዳቸው ያስተባበሩት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በቀጣይ ቀናትም ተመሳሳይ ስልጠናዎች እና ውይይቶች በቴክኖሎጂ በመታገዝ እንደሚደረግ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል። ” እነዚህ ነገሮች ቀጣይነት አላቸው። የሚቀጥለው ሳምምንት ቅዳሜ እንኳን ‘ኮዲድ 19 እና እግርኳስ በኢትዮጵያ’ በሚል ርዕስ ላይ ትምህርት ይሰጣል። ወደፊትም በወጥነት ትምህርቶችን እንዲሰጡ እናደርጋለን። ነገርግን ትምህርቶቹ በተጋባዥ ግለሰቦች ብቻ እንዲሰጡ አናደርግም። በሃገር ውስጥ የሚገኙ አሰልጣኞችም እርስ በእርስ እንዲማማሩ እንፈቅዳለን። ለሃገር እግርኳስ እና ለአሰልጣኞች የሚጠቅም ሃሳብ ያለው ማንኛውም የሃገር ውስጥ አሰልጣኝ ትምህርት መስጠት ይችላል። ምክንያቱም ዓላማው መማማር፣ እውቀትን ማሳደግ እና ልምድ እንዲለዋወጡ ማድረግ ስለሆነ።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ