ዮናስ ገብረሚካኤል እና የኢትዮጵያ ወጣት ቡድን የቦነስ አይረስ ገጠመኝ

ባለፈው ሳምንት በዘጠናዎቹ ኮከቦች አምዳችን የዮናስ ገብረሚካኤል የህይወት ጉዞ ማስቃኘታችን ይታወሳል። አሁን ደግሞ ተጫዋቹ ከአርጀንቲና ትውስታዎቹ አንዱን አጋርቶናል።

ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው የታዳጊዎች አፍሪካ ዋንጫ በብዙ አነጋጋሪ ጉዳዮች ታጅበው ውድድራቸው ያካሄዱትና በመጨረሻም ወደ 2001 የአርጀንቲና ዓለም ዋንጫ የሚወስዳቸውን ትኬት የቆረጡት የወጣት ቡድን ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት ያጋጠማቸው አይረሴ ነገሮች በዘጠናዎቹ ኮከኮች እና በትውስታ ዓምዶቻችን እያጋሩን መቆየታቸው ይታወሳል። አሁን ደግሞ የመስመር ተከላካዩ ዮናስ ገብረሚካኤል ሁለት የብሄራዊ ቡድን አባላት ያጋጠማቸውን ነገር እንዲህ ያስታውሰናል።

” አርጀንቲና ሄደን ከቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ ያጋጠመን ነገር አለ። ልክ አርጀንቲና ከሄድን በኃላ ወደ ዋናው የምንጫወትበት ሳልታ ከተማ ከመሄዳችን በፊት በቦነስአይረስ ከተማ ትንሽ ቆይተን ነበር። ያረፍንበት ሆቴልም በጣም ትልቅ እና ዘመናዊ ነበር። ለሁላችንም አከባቢውን የሚያሳዩን እና ክፍል ክፍላችን የምያስይዙን ባለሞያዎች ነበሩ፤ ሁለት ስማቸውን መጥቀስ የማልፈልጋቸው ተጫዋቾች ግን በራሳቸው ከሪሴፕሽን ቁልፍ ተቀብለው ሻንጣቸውን ይዘው ሄዱ። ሁለት ካርድ ተቀብለው ወደ ክፍላቸው አመሩ፤ ካርድ የምን እንደሆነ አላወቁም። እንደ አጋጣሚ ግን ክፍላቸው ክፍት ሆኖ ጠበቃቸውና ሳይቸገሩ ገቡ።

ወደ ክፍሉ ቢገቡም መብራት በምን እንደሚበራ ጠፋባቸው፤ ብዙ ሞከሩ አልሆነም። ከዛ ሁለተኛው ተጫዋች እስኪ በሰጠችን ካርድ እንሞካክር ቢለው ያኛው ተጫዋች ‘ተወው እሱማ የበሩ ካርድ እስኮርት ነው።’ አለው። (ረጅም ሳቅ ) ከዛ ስለ ቴክኖሎጂው ምንም እውቀት ስለሌላቸው በጨለማ ቤት አደሩ። በአርጀንቲና ቦነስአይረስ ከገጠሙን ነገሮች ሁሌም ሳስታውሰው የምስቅበት አጋጣሚ ነው።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ