በእግርኳስ የጨዋታ ትንተና የሥልጠና ወሳኙ አካል ነው፡፡ ጨዋታን የመገምገም ብቃት ለቡድን ውጤታማነት ጉልህ ሚና ስላለው በከፍተኛ ሁኔታ ትኩረት ሊቸረው ይገባል፡፡ በጨዋታ ወቅት በየትኛው ሰዓት የተጫዋች ቅያሪ መደረግ እንዳለበት ማወቅ የአሰልጣኝ ኃላፊነት ይሆናል፡፡ ከጨዋታው በኋላ የለውጡን ምክንያት ለተጫዋቾች በግልፅ የማብራራት ድርሻም እንዲሁ የዋና አሰልጣኙ ሊሆን ይገባል፡፡
ብዙ አሰልጣኞች በልምምድ ጊዜ ውጤታማ መርኃግብር እንደሚያካሂዱ ይናገራሉ፡፡ ቡድናቸው እንዲጫወት የሚፈልጉትንም ሥልት በልምምድ ፕሮግራማቸው ይነድፋሉ፤ ለተጫዋቾቻቸውም በድግግሞሽ የተግባርና የቲዎሪ ትምህርት ይሰጣሉ፡፡ የዚህ ሁሉ ልፋታቸው መጨረሻ የሚታየው በጨዋታ ላይ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ቡድን ለስኬቱም ሆነ ለውድቀቱ መነሻ የሆኑ አንኳር ጉዳዮችን ለማወቅ ግምገማ ወይም ጥልቅ ትንተና ማካሄድ ያስፈልገዋል-በተለይ በነጥብ ጨዋታዎች ወቅት፡፡ የእያንዳንዱን ተጫዋች የተናጠል ብቃት፣ በየመጫወቻ ክፍሎች (Departments) ያሉ የተጫዋቾችን ጥምረት፣ አጠቃላይ የቡድን አወቃቀር፣ በጨዋታ ሒደቶች (Phases) የሚፈጠሩ ህጸጾች፣ በተጋጣሚ ቡድን ጠንካራ ጎን ወይም ደካማ አቋም አማካኝነት የተፈጠሩ ተግዳሮቶች-እድሎች እና ሌሎችም የጨዋታ ኹነቶች በአግባቡና በሰለጠነ መንገድ ተገምግመው ማብራሪያ ሊሰጥባቸውና እርምት ሊወሰድባቸው ይገባል፡፡ አለበለዚያማ ሜዳ ላይ ለሚፈጠሩ ችግሮች ተገቢውን ምላሽ መስጠት፣ አሳማኙን ምክንያት ማቅረብ፣ አስፈላጊውን መፍትሄ ማመላከት ካልተቻለ ሥልጠናው ሁሉ ከንቱ፥ ልምምዱ ሁሉ ፉርሽ ይሆናል፡፡ ጨዋታን በዝርዝር የመተንተን ልማድ ከውድድር ያለፈም ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ በእያንዳንዱ የጨዋታ ልምምድ ላይ ምን መስራት እንሚኖርብን ያስተምረናል፡፡
★ እየተከናወነ ያለ ጨዋታን መገምገም
-በመከላከልም ሆነ በማጥቃት ሒደት በመፈጠር ላይ ያሉ የእንቅስቃሴና የውሳኔ ግድፈቶችን መመልከት
* እዚህ ላይ የሁለቱንም ቡድኖች ማለትም የራስንና የተጋጣሚን ቡድን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ማጤን የግድ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
-የቡድንም ሆነ የግል ስህተቶችን ለማረም እና ለውጦች ለማድረግ መዘጋጀት
ለምሳሌ፡- የተቃራኒ ቡድን የግራ መስመር ተከላካይ ደካማ የፍጥነት ደረጃ ካሳየ በእርሱ በኩል ፈጣኑን የመስመር አማካይ ወይም አጥቂ በማጫወት ከተከላካዩ ጀርባ በሚኖሩ ክፍት ቦታዎች ላይ ኳሶች እንዲጣሉ ማድረግ
ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ጥያቄዎች በመከናወን ላይ የሚገኝን ጨዋታ ለመገምገም አስፈላጊ ግብዓቶች ይሆናሉ፡፡
-የጨዋታ ዕቅዳችን ወደ ተግባር እየተለወጠ ነውን?
-የጨዋታ ዘይቤያችንን በአግባቡ ለመተግበር እየቻልን ነው?
-ኳስ ተቆጣጥረናል(ኳስ የመቆጣጠር ዕቅድ ከነበረን)?
-በሜዳው እያንዳንዱ ክፍል የማጥቃት እና የመከላከል ሒደታችን ውጤታማ ነው?
-ተጫዋቾች በግል እያሳዩ ያለው አቋም እንዴት ይታያል?
*እረፍት የሚያስፈልገው ተጫዋች አለ?
*በጥሩ ብቃት እየተጫወተ ያለው የትኛው ተጫዋች ነው?
*ደካማ አቋም ላይ የሚገኘውስ ማነው ?
-በመከላከል እና በማጥቃት ሒደት ያለን ታክቲካዊ አቀራረብ አዋጭ ነውን?
-ተጋጣሚ ቡድን በምን ዓይነት መንገድ ጨዋታውን በማካሄድ ላይ ይገኛል?
-ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ የተጋጣሚ ቡድን ችግር አለ?
-የተቃራኒ ቡድን ዋናው ጥንካሬ ምንድ ነው?
-ለማሸነፍ ምርጡ መንገድ የትኛው ይሆናል?
-ከተጋጣሚ ቡድን በእኛ ቡድን ላይ ጫና እያሳደረ ያለው ተጫዋች የትኛው ነው?
-ይህን (ተጽዕኖ ፈጣሪውን) ተጫዋች ለማቆም ምን መደረግ አለበት?
★ከጨዋታ በኋላ የሚኖር የጨዋታ ትንታኔ
-የተወሰኑ አዎንታዊ ማበረታቻዎችን መስጠት
-ከጨዋታ በኋላ ተጫዋቾች የሚገኙበትን የአካል ብቃት ደረጃ ለማወቅ ሰፊ ውይይት ማድረግ
-ስለ ቀጣዩ የልምምድ መርኃግብር መነጋገር
-በጨዋታው ዙሪያ ለመነጋገር ቀጣዩን የልምምድ ዕለት መጠበቅ
-ስላለፈው ጨዋታ በልምምድ ቀን ማብራራት የሚመከረው ከስሜት ነፃ በሆነ አዕምሮና በግልጽ ተጫዋቾችን በግል እንዲሁም በጋራ መገምገም ስለሚያስችል ነው፡፡
ማስታወሻ፦ በተለይ ለአሰልጣኞች ጨዋታን ለመገምገም ብቻችሁን የምትሆኑበትንና ቁጭ ብላችሁ የምታሰላስሉበትን ጊዜ መምረጥ የተሻለ ይሆናል፡፡
ቀጣዮቹ ጥያቄዎች ደግሞ ከጨዋታ በኋላ ጨዋታን ለመገምገም ይረዱ ዘንድ ሊነሱ የሚገባቸው ናቸው፡፡
-በጨዋታ ወቅት በቁጥር የተቀመጡ መረጃዎችን በማጤን የቡድኑ የሜዳ ላይ ነባራዊ ሁኔታ ቡድኑን ጠቅሟል ወይስ ጎድቷል?
-እንዴት እና ለምን ጎሎች ተቆጠሩ?
-ከመከላከል ወደ ማጥቃት እንዲሁም ከማጥቃት ወደ መከላከል የሚደሰገው ሽግግር ምን ያህል ውጤታማ ነበር?
-በሜዳው የማጥቃት ሲሶ በተጋጣሚ ክልል የማጥቃት እና እዚያው ወረዳ የመከላከል ሓደቱ ምን ያህል ውጤታማ ነበር?
-የአማካይ ክፍሉስ ምን ያህል አመርቂ እንቅስቃሴ አድርጓል?
-በመከላከያ ወረዳ ላይ የተከላካዮቹ ጥምረት ምን ያህል ስኬታማ ነበር?
-የእያንዳንዱ ተጫዋች የግል ብቃት እንዴት ይመዘናል?
-በዕረፍት ሰዓት የቡድኑ አባላት የተወያዩባቸው ጉዳዮች ተተግብረዋል?
-ደካማ ጎንን ለማሻሻል ምን ዓይነት ልምምድ መስጠት ይኖርብናል?
-ጨዋታዎችን በአግባቡ ከገመገሙ በኋላ መሻሻል የሚያስፈልጋቸው ቦታዎችን ነጥቦችን ለይቶ በማውጣት እነርሱ ላይ አብዝቶ መስራት
-አጋዥና ብቁ የሚያደርጉ ልምምዶችን ማዘጋጀት
ማሰብ ያለብን ሁሉንም የሜዳ ላይ ችግሮች በአንድ ወይም በሁለት የልምምድ መርኃግብሮች ልንለውጥ እንደማንችል ነው፡፡ በጊዜ ሒደት ከቡድናችን የምንሻውን እስክናገኝ ማሻሻያዎችን በአግባቡ በማዘጋጀት፣ አዳዲስ የስልጠና ሥልቶችን በመንደፍ፣ ተጫዋቾቻችን ምርጡን ብቃታቸውን አውጥተው እንዲያሳዩ በማስቻልና በመሳሰሉት ንድፈ ሐሳባዊ ግምገማችንን ወደ ተግባር መቀየር እንችላለን፡፡
ስለ ፀሐፊው
የአስተያየቱ ፀሐፊ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል ፡፡ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፅዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ