በሃገራችን የተለያዩ የሊግ እርከኖች እየተጫወቱ የሚገኙ እና ለሙከራ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ጋናዊያን እግርኳስ ተጫዋቾች ትላንት በአዲስ አበባ ወደሚገኘው ጋና ኢምባሲ በመሄድ ለመንግስታቸውን ምሬት የተቀላቀለበት ጥያቄ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሼር ኩባንያ እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን በጋራ በመመካከር በዓለማችን ብሎም በሃገራችን እየተስፋፋ ባለው ኮቪድ 19 ምክንያት የእግርኳስ ውድድሮችን በኢትዮጵያ መሰረዛቸው ይታወቃል። ይህንን ውሳኔ እና መንግስት ያስተላለፈውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት በሃገራችን ውድድሮች እየተከናወኑ አይገኝም።
ውድድሮች መቋረጣቸውን ተከትሎ በርካታ ተጫዋቾች ወደ መኖሪያ ቀያቸው ሲያመሩ ከሌላ ሃገር የመጡ አብዛኞቹ ተጫዋቾች ግን መኖሪያቸውን በጊዜያዊነት በሆቴል አድርገው ቆይተዋል። ይህ የሆቴል ኑሮ ያማረራቸው ከ20 የሚበልጡ ጋናዊያንም ትላንት ጦር ኃይሎች አካባቢ ወደሚገኘው ጋና ኢምባሲ ድረስ ተሰባስበው በመሄድ በናና አኩፎ አዶ ለሚመራው መንግሥታቸው ጥያቄ አቅርበዋል።
ተጫዋቾቹ በኢምባሲው ደጃፍ ላይ ሆነው የቀፈፁትን ምስል ተመልክተው የጋና ሚዲያዎች በዘገቡት ዘገባ መሰረት የተጫዋቾቹ ጥያቄ መንግስታቸው ትራንስፖርት አመቻችቶላቸው በቶሎ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ እንደሆነ ተነግሯል። በተለይ ተጫዋቾቹ ለቤት ኪራይ እና ለምግብ ብሎም ለተለያዩ መገልገያዎች የሚያወጡት ወጪ ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ገልፀው ኢምባሲው ጥያቄያቸውን ለሃገሪቱ መንግስት እንዲያደርስላቸው ተማፅነዋል።
ወደ ኢምባሲው ካመሩት ተጫዋቾች መካከል ኦሴ ማውሊ፣ አዳሙ መሐመድ፣ አሞስ አቼምፖንግ፣ አልሃሰን ካሉሻ፣ መሐመድ ሙንታሪ፣ ሪችሞንድ አዶንጎ፣ ቢስማክ ኦፖንግ እና ቢስማክ አፒያ እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል።
ከቀናት በፊት በእንግሊዝ የሚገኙ 224 ጋናዊ ተጫዋቾች (108 ወንድ፣ 103 ሴት፣ 9 ህፃናት እና 4 ታዳጊዎች) በልዩ ሁኔታ በተዘጋጀላቸው ትራንስፖርት ወደ ጋና እንዲመለሱ መደረጉ ይታወሳል። ከአራት ቀናት በፊትም በአውሮፓ የሚገኙ ጋናውያን በተመሳሳይ በተዘጋጀላቸው ልዩ ትራንስፖርት ወደ ሃገራቸው ገብተዋል። በበርሊን የሚገኘው የጋና ኢምባሲም በጀርመን የሚገኙ ጋናዊያንን ወደ ትውልድ ሃገራቸው ለመመለስ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ንግግር መጀመሩ ተሰምቷል።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ