ያልተጠበቁ እና ተጫዋቾች ከሚሳተፉበት ውድድሮች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ውጪ የሆኑ ጉዳቶች በማንኛውም ቦታ እና ጊዜ ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ግብ ከተቆጠረ በኋላ ከሚደረጉ የደስታ አገላለፅ ትዕይንቶች ጀምሮ ወደ መጫወቻ ሜዳ ጥሰው በገቡ እንስሳት ምክንያት በሜዳ ውስጥ ተጫዋቾችን ላልተለመዱ ጉዳቶች ሲዳርጉ ተመልክተናል። ከእግርኳስ ሜዳ ውጪም በተለያዩ የዕለት ተለት ተግባሮች ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች በአስገራሚ አጋጣሚዎች ለረጅም ጊዜ ከጨዋታ እንዲገለሉ ያስገደዷቸውን ጉዳቶች ሲያስተናግዱ ተመልክተናል። ከእግርኳስ ጋር የተያያዙ የህክምና ጉዳዮችን በምንዳስስበት የሶከር ሜዲካል አምዳችን የዛሬ ዕሁፍ ከሜዳ ውጭ ያጋጠሙ እና በወቅቱም የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስበው የነበሩ ጉዳቶችን የሚያስታውስ ይሆናል። ለዚህም ‘The Secret Footballer: What the physio saw’ የተሰኘውን መጽሃፍ በዋቢነት ተጠቅመናል።
ስፔናዊው ግብ ጠባቂ ሳንቲያጎ ካኒዛሬስ በክለቡ ቫሌንሲያ ባሳየው ጥሩ ብቃት በ2002ቱ የዓለም ዋንጫ የብሔራዊ ቡድኑ ቋሚ ተሰላፊ እንደሚሆን በሚጠበቅበት ወቅት ዕድለቢስ ያደረገውን ጉዳት አስተናግዷል። ተጫዋቹ ፂሙን በሚላጸጭበት ሰዓት ወድቆ በተሰበረ መስታወት እግሩ ላይ ጉዳት ስለደረሰበት ከውድድሩ ለመቅረት ተገዷል።
እንግሊዛዊዉ ግብ ጠባቂ ዴቪድ ጄምስ ደግሞ ሪሞት ኮንትሮል ለማንሳት ሲንጠራራ የጀርባ ጡንቻዉ በመሳቡ ጉዳት አጋጥሞታል። አሌክስ ስቴፕኒ የተባለው በ1970ዎቹ ሲጫወት የነበረ የማንችስተር ዩናይትድ ግብ ጠባቂ በሚጮህበት ወቅት የአገጩ መገጣጠሚያ ተላቆ ለጉዳት ተዳርጎም ነበር። አሜሪካዊው ግብ ጠባቂ ኬሲ ኬለር በበኩሉ የጎልፍ መጫወቻ ዱላ በሚያወጣበት ሰዓት አፉን በመምታቱ የፊት ጥርሱ ረግፏል።
ኬቨን ካይል እና አደም ቻፕማን የተባሉት ተጫዋቾች ያጋጠማቸው ጉዳት ደግሞ ከህፃናት ልጆቻቸው ጋር የተያያዙ ነበሩ። የስኮትላንዱ ኪልማርኖክ ክለብ አጥቂ የነበረው ኬቨን እ.ኤ.አ. በ2006 የ8 ወር ህጻን ልጁ በደፋበት የሞቀ ውሃ በመቃጠሉ አንድ ሌሊት በሆስፒታል ተኝቶ ለማሳለፍ ተገዶ ነበር። እንግሊዛዊው የአማካይ ስፍራ ተጫዋች አደም ቻፕማን በበኩሉ ለህጻን ልጁ ወተት በሚያዘጋጅበት ጊዜ የጡጦውን ክዳን መክደን በመዘንጋቱ ትኩስ ወተት ተደፍቶበት ተመሳሳይ ጉዳት ደርሶበታል፡፡
ታዎቂው የቀድሞ የእንግሊዝ እንደዚሁም ማንችስተር ዩናይትድ ተከላካይ ሪዮ ፈርዲናንድ ለሊዲስ ዮናይትድ በሚጫወትበት ጊዜ በቤቱ ለረጅም ሰዐት በአንድ አይነት አቀማመጥ ሆኖ የቪድዮ ጌም በመጫወቱ የጉልበቱ ጅማት ላይ ጫና በዝቶበት ለሳምንታት ከሜዳ ያራቀው ጉዳት አስተናግዷል።
ኢኳዲሪያዊው አጥቂ ኤነር ቫሌንሺያ የተሰበረ ሲኒ በመርገጡ የእግር ጣቱ ላይ ጉዳት አጋጥሞት ነበር። ዲሪክ ላይል የተሰኘው የስኮትላንዱ ክለብ ደንዲ ዩናይትድ ተጫዋች ቤቱ ውስጥ የነበረ የመስታወት ጠረጴዛ ላይ በመውደቁ ወሳኝ የሆነ የግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ እንዲያመልጠው ሆኗል። በ1960ዎቹ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች የነበረው አለን መሪ ሀገር ሰላም ብሎ ጥርሱን በሚፍቅበት ወቅት በጡንቻ መሳሳብ ምክንያት ጀርባው ላይ ጉዳት ገጥሞታል።
ከላይ ከተጠቀሱት ምሳሌዎች ማየት እንደምንችለው ለወራት ከሜዳ ሊያርቁ የሚችሉ ጉዳቶች በማንኛውም ሰዓት ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ተጫዋቾቻችንም ከሜዳ ውጭ በሚኖረው ህይወታቸው በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ፤ በተለይም ከባድ ዕቃዎችን እንደመሸከም ያሉ ስራዎችን ባለመስራት፣ እንቅስቃሴ ሳያደርጉ በአንድ አቀማመጥ ለረጅም ጊዜ ባለመቆየት እና የመቁረጥ እና የመውጋት ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ቁሶችን በጥንቃቄ በመጠቀም ራሳቸውን ከተለያዩ ጉዳቶች መጠበቅ ይኖርባቸዋል። እግርኳስ ተጫዋቾች ሰዉነታቸው እና የአካል ብቃታቸው ገንዘባቸው ስለሆነ የቻሉትን ሁሉ እንክብካቤ እንደዚሁም ጥንቃቄ ሊያደርጉለት ይገባል።