የጳውሎስ ጌታቸው ከባድ ጉዳት እና የናይጀርያ ጨዋታ ትውስታው

“መኪና የወደቀብኝ ያህል ነው የተሰማኝ። አንድ ዓመት ሙሉ ከእግር ኳስ አርቆኛል”

በተጫዋችነትና በአሰልጣኝነት ጥሩ ስም ካላቸው አንዱ ነው። የእግርኳስን ሕይወቱ በህንፃ ኮንስትራክሽን ጀምሮ እስከ 1981 በአሳዳጊ ክለቡ በመቆየት በቀጣዩ ዓመት ወደ ኢትዮጵያ ቡና ያመራው ጳውሎስ እስከ ተጫዋችነት ዘመኑ ፍፃሜ ድረስ (እስከ 1991) በቡናማዎቹ ጥሩ ጊዜያት አሳልፏል። በብሔራዊ ቡድን ደረጃም ለሰባት ዓመታት ኢትዮጵያን ማገልገል ችሏል።

በህንፃ ቆይታው ያሰለጠኑት አሥራት ኃይሌን በልዩ ሁኔታ የሚያመሰግነው ጳውሎስ በሜዳ ውስጥ በሚያሳያቸው ተጋድሎዎች እና የከረረ የኳስ ምቱ በልዩ ይታወቅ ነበር። ለዛሬ በ1994 አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ሌጎስ ላይ በ1993 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር ሐምሌ 17 ቀን 1985) ከናይጀርያ ጋር ባደረጉትና 6-0 በተሸነፉበት የመጨረሻ የምድብ ማጣርያ ጨዋታ ላይ ስለደረሰበት ከባድ ጉዳት እና ስለ ጨዋታው ያለውን ትውስታ እናቀርብላችኃለን።

” ጨዋታው ከባድ ነበር፤ ይህ የናይጄርያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫውን ያሸነፈ እና በዓለም ዋንጫም 16 ውስጥ የገባ ቡድን ነበር። በናይጀርያ ታሪክ ውስጥ ምርጥ ከሚባለው ትውልድ አንዱ ነበር። የኛ ብሄራዊ ቡድንም በጣም ጥሩ ቡድን ነበር። እነ መሰለ አካለወልድ፣ ሸሪፍ፣ ተስፋዬ ኦርጌቾ፣ ክፍሎም መብራቱ፣ ሙሉጌታ ከበደ፣ ሚልዮን በጋሻው እና ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስን የመሳሰሉ ምርጥ ተጫዋቾች የነበሩበት ቡድን ነበር እና እኔም በሰዓቱ ጥሩ ብቃት ላይ ነበርኩ።

” ናይጀርያ ከኛ በተሻለ ጥሩ ቡድን ሆኖ ነው እንጂ የኛ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ የሚገባው ቡድን ነበር። ሱዳን እና ዩጋንዳን አሸንፈን ጥሩ ደረጃ ላይ ነበርን። በመልስ ጨዋታ በሱዳን ባንሸነፍ ኖሮ ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ዕድልም ነበረን። በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ከነቱኒዝያ እና ሞሮኮ ተመድበን በጣልያን ስድስት ተጫዋቾች ጠፍተውብን ያደረግነው ጨዋታም በዛኑ ዓመት ነበር።

” ወደ ወሳኙ የናይጀርያ ጨዋታ ትውስታዬ ስመልስህ እዚህ አዲስ አበባ በተስፋዬ ኦርጌቾ ብቸኛ ግብ አንድ ለባዶ አሸንፈናቸው ነበር፤ ለግንቦት ሀያ በተዘጋጀ ጨዋታም አራት ለአንድ አሸንፈናቸው ነበር። በመጀመርያው የማጣርያ ጨዋታ በልጠናቸው ነበር፤ በሰፊ ልዩነት ማሸነፍ እንችል ነበር። ሆኖም ከጨዋታው በፊት ትልቅ ግምት ሰጥተናቸው ሰለነበር በሥነ-ልቦና ደረጃ አልተዘጋጀንም ነበር።

” በሁለተኛው የናይጀርያ ጨዋታ ግን በሰፊ ውጤት የተሸነፍንበት እና በእኔ ላይም ከበድ ያለ ጉዳት የደረሰበት ጨዋታ ነበር። ጉዳቱም ከራሺድ ያኪኒ ጋር የተያያዘ ነበር። ያኪኒ በዛን ወቅት ከዓለም ምርጥ አጥቂዎች አንዱ ነበር። ግዙፍ ነው፤ 96 ኪሎ ነበር። እኔ ደግሞ በዛን ወቅት ከኢትዬጵያ የተሻልኩ ጉልበተኛ እና ጀብደኛ የምባል ተጫዋች ነበርኩ። ለዛም ነው አሰልጣኝ ካሳሁን ተካ ያኪኒን በቅርብ ርቀት እንድከታተል ትእዛዝ የሰጠኝ። እስከ ሰላሣ ደቂቃ ድረስ ጥሩ ተቆጣጥረናቸው ነበር ከዛ በኃላ ግን በአንድ ተጫዋቻችን ጥፋት ግብ አስተናገድን ቀሪው የጨዋታው ክፍለ ጊዜ እንደዝናብ ነው የሆኑብን።

” ከባዱ ጉዳት ያስተናገድኩበት ቅፅበት ራሺድ ያኪኒን ኳስ ለማስጣል ገብቼ ተጫዋቹ እላዬ ላይ ወደቀ። ጉዳቱ በጣም ከባድ ነበር፤ ንዝረት በለው። መኪና የወደቀብኝ ያህል ነው የተሰማኝ። አንድ ዓመት ሙሉ ከእግር ኳስ አርቆኛል። እንደውም እኔ በአካል ብቃት የተሻልኩ ስለነበርኩ ነው እንጂ ጉዳቱ ከዛ የባሰ ይሆን ነበር። በደረሰብኝ ጉዳት ሙሉ ቡድናችን አዝኖ ነበር፤ ከጨዋታው በኃላም ራሺድ ያኪኒ ሆቴል ድረስ መጥቶ ጠይቆኛል። ያኪኒ ሕይወቱ ማለፉን ስሰማ በጣም ነው ያዘንኩት፤ የሞተበት መንገድ ራሱ ያሳዝናል ተጎሳቁሎ ነው የሞተው።

” በወቅቱ የነበረው ሀኪማችን ዶክተር አያሌው ብዙ ጥረት አድርጎልኛል። ጉዳቱ ባይደርስብኝ ቢያንስ ለቀጣይ አስር ዓመታት በጥሩ ብቃት መቆየት እችል ነበር። ሆኖም ከጉዳቱ በኋላ እንደ ቀድሞ በትልቅ ደረጃ መጫወት አልቻልኩም። የአካል ብቃት ልዩነቱ በጣም ትልቅ ነበር፤ ኳስ ይዘን በራሳችን መንገድ መጫወት ነበረብን፤ ለነሱ በሚመች መንገድ መቅረብ አልነበረብንም። በአጠቃላይ በጨዋታው የነበረኝ ትውስታ ይህንን ይመስላል።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ