የዘመናችን ከዋክብት ገፅ | ከፍሬዘር ካሳ ጋር…

በቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ እና ዋናው ቡድን ተጫውቶ አሳልፏል፡፡ በፍጥነትም ባሳየው ድንቅ አቋም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መመረጥም ችሏል፡፡ ዘንድሮ ለድሬዳዋ ከተማ ፈርሞ ሊጉ እስከ ተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ጥሩ ቆይታ የነበረው የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ ፍሬዘር ካሳ የዛሬው የዘመናችን ከዋክብት ገፅ ተጋባዥ ነው፡፡

ትውልድ እና ዕድገቱ አዲስ አበባ ፒያሳ በተለምዶ ገዳም ሰፈር አካባቢ ቢሆንም ኳስን መጫወት የጀመረው በጃን ሜዳ ነው፡፡ ብዙ የታዳጊ ቡድኖች እና ክለቦች ለልምምድ የሚጠቀሙበት እና በርካታ ተጫዋቾችን ያፈራው ጃን ሜዳ ለዛሬው ዕንግዳችንም መሠረት ጥሎለት አልፏል፡፡በዚሁ ሜዳ ላይ በአሰልጣኝ ፈለቀ በሚሰለጥነው ‘ሂሳብ’ በተሰኘ የስልጠና ቡድን ውስጥ የልጅነት የኳስ ህልሙን የጀመረ ሲሆን ዕድሜው እየበሰለ ሲመጣ 2005 ለንግድ ባንክ የታዳጊ ቡድን የነበረውን ምልመላ በማለፉ ወደ ቡድኑ ገብቶ የአንድ ዓመት ቆይታን ብቻ አድርጎ 2006 ላይ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ‘ቢ’ ቡድን 2007 ደግሞ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተስፋ ቡድን በማደግ መጫወት ችሏል።

በፈረሰኞቹ በታዳጊነት ዕድሜው ከዓመት ዓመት ፈጣን ዕድገትን እያሳየ በመምጣቱ በ2008 ግማሽ ዓመት ላይ ወደ ዋናው ቡድን አድጎ ክለቡን በሚገባ አገልግሏል፡፡ ከ2009 ጀምሮ በቋሚነት በክለቡ የመሀል እንዲሁም የመስመር ተከላካይነት ቦታ ላይ ሲሰለፍ የነበረው ተጫዋቹ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ2010 ተጠርቶ መጫወትም ችሏል፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የተለያየበት ምክንያት ዛሬም ድረስ እንደሚቆጨው የሚናገረው ፍሬዘር ካሳ ዘንድሮ ወደ ድሬዳዋ ካመራ በኃላ በክለቡ መልካም የሚባል ዓመትን ሊጉ እስከ ተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ሲያሳልፍ ከአሰልጣኝ ስምኦን አባይ መልቀቅ በኃላ በአሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳን የተከላካይ አማካይነት ስፍራ ላይ እንዲጫወት የተለየ ሚና የተሰጠው ይህ ወጣት ተጫዋች አዝናኝ ጥያቄን ባዘለው የዘመናችን ክዋክብት ገፅ የዛሬው ዕንግዳችን ነው፡፡

በቅዱስ ጊዮርጊስ ፈጣን ዕድገት አሳይተህ በዋናው ቡድንም ጥሩ እንደነበርክ ይታወቃል። እስቲ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታህ እናውራ …

ጊዮርጊስ ይከብዳል ፤ ያው ለሁሉም ነገር ራስን ማዘጋጀት ነው። በክለቡ ብዙ ተጫዋቾች ሲኒየር ከመሆናቸውም የተነሳ ብዙ ነገር ነበር ከእኔ ሚጠበቀው። ከባድ ነው። ያው ግን ከገባህበት በኃላ ያለውን ነገር ስታየው እየለመድከው ስለምትመጣ እኔ አሁን የታዳጊነት ጊዜ ጀምሮ ስለነበረ የነበርኩበት ያሉትን ነገሮች በአንዳንድ ጓደኞቼ እና ተጫዋቾች ምክንያት እየለመድኩ እንድመጣ አድርጎኛል፡፡ በዚህ ደረጃ ከብዶኛል ብዬ አላስብም እንደመጀመሪያ የሚከብድ ነገር ይኖራል፡፡ ከዚያ በኃላ ግን ከሚነግሩህ ነገር እና በምታሳየው ጥሩ ነገር እየቀለለህ ይመጣል። እና ከሰራህ ምንም ነገር ማለፍ ትችላለህ ያን ነገር በነበረኝ ጊዜ አይቼበታለሁ፡፡

በድሬዳዋ ዘንድሮ ከመከላከሉ ባለፈ ወደ መሀል ሜዳውም ጭምር ገብተህ ትጫወት ነበር ፤ ጥሩ ነገርም ነበረህ። ሊጉ በኮሮና መቋረጡ የፈጠረብህ ነገር የለም ?

በዕርግጥ እኛ ከለመድንበት የአጨዋወት ዘይቤ ዓይነት ወጣ ያለ ነው። ኮሮናው አስቸጋሪ ስለነበር ጥሩ ነገር እያሳየው መቋረጡ ትንሽ ይከብድ ነበር። ከተቋረጠ በኃላ ግን አብዛኛዎቹን ጊዜ ማሳልፈው ቤት ውስጥ ነበር። ግን ጠዋት ጠዋት ብዙ ጊዜ ስፖርቴን እሰራለሁ። ባይቻልም ጊቢ ውስጥ ባለው ነገር መስራት የምትችለውን ያህል ትሰራለህ። ከዛ በተረፈ ቤተሰቦቼ ጋር ነበረ የማሳልፈው ፤ ፊልምም አያለሁ። አሁን ላይ ደግሞ ትንሽ ይሄን ሰፋ ሳደርገው ከፍቅረኛዬ ጋር ባህርዳርም እየመጣው ከሷ ጋር አሳልፍ ነበር። እና ደግሞ እዚህም የተሻለ ነገር ስለነበረ በባህርዳር ጥሩ ነገር መስራትም ችያለሁ። ያለው የአየሩ ሁኔታ ጥሩ ስለሆነ ለመስራት እና ለመንቀሳቀስም ምቹ ስለሆነ እዚህ ለማሳለፍ ነው የተገደድኩት እና ብቻ ወጣ ያለ ነገር ነው፡፡ የምናሳልፈው ነገር ትንሽ ይከብዳል ግን መቻል ነው፡፡

እንደ ስፖርተኛ ኮሮናው መጣ አሁን ደግሞ ክረምቱ ገባ የጊዜውስ መርዘም ውድድር ሳታደርግ መቆየቱስ አልከበደህም? ድብርቱስ ?

ኡ በጣም ከባድ ነው፡፡ የመጣውን ነገር ትችለዋለህ አሁን ካቆምን ወደ ስድስተኛ ወራችን ገብተናል ያለ ኳስ አንድ ቀን እንኳን ማሳለፍ ይከብዳል፡፡ ግን ይሄ በሀገር ደረጃ የመጣ ስለሆነ ያለህ አማራጭ በቃ እንደጊዜው መሆን ነው፡፡ እና በጣም ከባድ ጊዜ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆንም ከዚህ በኃላ ከባድ ጊዜዎች ይምጡ አይምጡ አናውቅም። ፈጣሪ ነው እንግዲህ የሚያውቀው ብቻ የተሻለውን ጊዜ ያምጣልን ነው የምለው፡፡

ፍሬዘር ካሳ እግር ኳስ ተጫዋች ባይሆን ኖሮ በዚህን ጊዜ ምን ላይ እናገኘው ነበር ?

በእርግጥ እንደዚህ እሆናለሁኝ ብዬ አላስብም። እግር ኳስ ተጫዋች ባልሆን ምን ልሆን እንደምችል አላስብም ፤ አስቤውም አላውቅም። ግን ያው ፈጣሪ ያለልኝን ነበር የምሆነው።

በፕሪምየር ሊጉ በቅዱስ ጊዮርጊስ አሁን ደግሞ በድሬዳዋ እንዲሁም በብሔራዊ ቡድንም ጭምር መጫወት ችለሀል። በነዚህ ሁሉ ቆይታህ አብሬ ተጣምሬ ብጫወት ደስ ይለኛል የምትለው ተጫዋች ማነው ?

እኔ አሁን ለምሳሌ አብሬ ከተጫወትኳቸው አሁን ከእነአስቻለው ታመነ ፣ ሳልሀዲን በርጊቾ እንን ደጉ ደበበ በየጊዜው አብሬያቸው ተጫውቻለው፡፡ ግን በቃ በይበልጥ ከአስቻለው እና ሳልሀዲን ጋር አብሬ በመጫወቴ ደስተኛ ነኝ። ትንሽ ጊዜም ቢሆን አብሬ በማሳለፌ እና ለእኔ ትልቅ ነገር ነው ከእነሱ አይቼም ሰርቼም ነው ያለፍኩት። በቀጣይም ከአስቻለው ታመነ ጋር ብጫወት ደስተኛ ነኝ፡፡

በተቃራኒው ሆኖ በሜዳ ላይ ከአንተ ክለብ ጋር ሲጫወት የሚከብድህ ተጫዋች አለ ?

እኔ በዚህ ደረጃ ይከብደኛል ያልኩት ተጫዋች የለም። እኔ ሁልጊዜ የተሻለ ነገርን ሰራለሁ ብዬ ስለማስብ ይከብደኛል ብዬ ማስበው ተጫዋች የለም ከብዶኝም አያውቅም እስከ አሁን፡፡

እግር ኳስ ተጫዋች ሆኖ ለፍሬዘር የቅርብ ጓደኛው አልያም የምስጢሩ ተጋሪ ማነው ሊባል ይችላል ?

ለእኔ ሁለት ሦስት ልጆች አሉ ግን በይበልጥ ምንተስኖት አዳነ ነው በጣም ምስጢረኛዬ። ሳልሀዲን በርጌቾም በጣም ጓደኛዬ ነው። ግን ምንተስኖት ይቀርበኛል። እንደወንድምም እንደጓደኛም ነው። እሱን ነው በተሻለ የማማክረው፡፡

ስለ ቤተሰብ መመስረት እናውራ አግብተሀል ? ወይንስ ከወላጆችህ ጋር ነው ኑሮህ ?

ለጊዜው ከቤተሰብ ጋር ነው ኑሮዬ። ፍቅረኛ ግን አለችኝ። አሁን ከጊዜ በኃላ እግዚአብሔር ከፈቀደ ከእሷ ጋር በትዳር እጣመራለሁ ብዬ ከማስባት ፍቅረኛዬ ጋር ነው አሁን ያለሁት። አምላክ ከፈቀደ ወደ ፊት አብረን እንኖራለን፡፡

በእግርኳሱ ያዘንክበት ጊዜ ?

በእግር ኳስ ሁለቴ አዝኛለሁ። አንድ በጊዮርጊስ እያለሁ ቻምፒዮስ ሊግ ስምንት ውስጥ ለመግባት ይመስለኛል ከሳንዳውንስ ጋር ስንጫወት የወደቅንበት እና ሁለተኛ ደግሞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የወጣውበት ጊዜ በህይወቴ ያዘንኩባቸው ጊዜያቶች ናቸው፡፡ ዛሬም ለመልቀቄ ይሄ ነው የምለው ነገር የለም።

በተቃራኒው ደስተኛ የሆንክበትስ ?

ደስተኛ የሆንኩበት በ2009 በግሌ በቅዱስ ጊዮርጊስ የተሳካ ዓመት አሳልፌያለሁ ብዬ የማስብበት ጊዜ ነበር። ትልልቅ ስም ካላቸው ጋር የተጫወትኩበት ነበር፤ ቢያንስ እዛ በነበርኩበት አንድ ታሪክ ፅፌያለሁ ብዬ የማስብበት ደስተኛም የነበርኩበት ነው ያ ጊዜ፡፡

ምን አይነት ምግቦች ይመቹሀል? እንደ ስፖርተኛስ ምን አይነት ምግብ ታዘወትራለህ?

እኔ እንኳን በዚህ ደረጃ ምግብ አላማርጥም። ግን ያው ስፖርትን በምሰራ ሰዓት መጠቀም ያለብኝን ማለትም እንደ ፓስታ፣ ሩዝ እና አትክልት ነገሮችን አዘወትራለሁ። ግን ከዛ ውጪ ቤት ውስጥ ያገኘሁትን ነው የምጠቀመው። ችግር የለውም ምግብ ላይ፡፡

ሰዎች የማያውቋቸው የተለየ ባህሪ አለኝ ብለህ ታስባለህ ?

በዚህ ደረጃ እንኳን አለኝ ብዬ አላስብም። እንደማንኛውም ሰው ከጓደኞቼ ጋር ስሆን መሳቅ መጫወት እወዳለሁ። በተለይ ከምንተስኖት ጋር ስሆን በቃ ዝም ብዬ ነው የምስቀው፤ ስለሚያስቀኝ እስቃለሁ። ሜዳ ውስጥ ስሆን ግን የሚቀይረኝ ነገር አለ፤ ያው ውጤት ከመፈለግ አንፃር። ከሜዳ ውጪ ዝምተኛ ባህሪ ስላልኝ ሜዳ ውስጥ አንዳንድ ሰው ስቀየርበት ይገረማል። በልዩነት የማነሳው ባህሪ ግን የለኝም፡፡

ከዋና መጠሪያ ስምህ ውጪ ቅፅል መጠሪያ አለህ ?

(ሳቅ) …አዎ ሁለት ስሞች አሉኝ። አንዱ “ኒኖ” ነው አንዱ ደግሞ “ስፔን” ነው፡፡ ስፔን የሚለውን አዳነ ግርማ ነው ያወጣልኝ። አብዛኛዎቹም አዳነ ባወጣልኝ ስም ነው የሚጠሩኝ። ትንሽ ፈን ያደርጋል አወጣጡ። አንዴ ጊዮርጊስ እያለን ክፍል ውስጥ ቁጭ ብለን ስፖርት ዜና በቴሌቪዥን ተሰብስበን እያየን ብዙ ነን፤ አዳነም ነበረ… ይህን ሳስበው አሁንም ስቃለሁ። እያየን ጋዜጠኛው እንዲህ አለ ኢትዮጵያዊያን ብስክሌተኞች በስፔን የነበራቸውን ውድድር አጠናቀው መጡ ብሎ እየነተነ ነው። ‘እንዴ ከሚመጡ አይጠፉም እንዴ’ ብዬ ስሜታዊ ሆኜ ነበር የተናገርኩት። አዳነም ‘የት ነው የሚጠፉት? ስፔን? አለኝ’ በቃ በዛ ነገር ተሳቀብኝ። ከዛ ስፔን ብሎ መጥራት ጀመረ። በዛው ቀረ። አልፎ አልፎ ኒኖ በምትባለውም እጠራለሁ። ቶሬስን በጣም ነበር የምወደው። አንድ የሰፈር ልጅ ነው ኒኖ ብሎ ያወጣልኝ፡፡

ከእግር ኳሱ ውጪ ምን ያዝናናሀል?

ከእግር ኳስ ውጪ ከጓደኞቼ ጋር ሳሳልፍ ማለት ቁጭ ብዬ አብሬያቸው ስጫወት ደስ ይለኛል። ፊልምም አያለሁ። ያው እነዚህ እነዚህን ሳደርግ ያዝናናኛል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ