ሲዳማ ቡና የፍቅሩ ወዴሳ፣ ግሩም አሰፋ እና ይገዙ ቦጋለን ውል ሲያራዝም ለወልቂጤ ከተማ አሳልፎ ሰጥቶት የነበረውን ጫላ ተሺታን ለማስፈረም ከስምምነት ደርሷል፡፡
ከሰሞኑ የአሰልጣኞቹን ውል ለሁለት ተጨማሪ ዓመት ያራዘመው ክለቡ ላለፉት አራት ዓመታት ቡድኑን ያገለገለው ግብ ጠባቂው ፍቅሩ ወዴሳ እንዲሁም ከሀዋሳ ታዳጊ ቡድን እስከ ዋናው ድረስ መጫወት የቻለውና በሲዳማ ቡና የተሳኩ ዓመታትን ያሳለፈው የቀኝ መስመር ተከላካዩ ግሩም አሰፋ ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ውሉን አራዝሟል፡፡ ሦስተኛው ውሉን በክለቡ ያራዘመው ከ2011 ጀምሮ ለሲዳማ ቡና አስደናቂ ጉዞ የራሱን ድርሻ ያበረከተው አጥቂው ይገዙ ቦጋለ ሌላኛው ለቀጣዮቹ ዓመታት በክለቡ የሚቆይ ተጫዋች ሆኗል፡፡ ተጫዋቾቹ በክለበለ ለመቆየት በቃል ደረጃ መስማማታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
የነባር ተጫዋቾችን ውል ከማራዘሙ ጎን ለጎን አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማስፈረም በጥረት ላይ ያለው ክለቡ ለወልቂጤ ከተማ በያዝነው ዓመት አሳልፎ የሰጠውኝ የመስመር አጥቂ ጫላ ተሺታን ዳግም ለማስፈረም ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡ በኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ካሳየው ድንቅ እንቅስቃሴ በኃላ በሰበታ ከተማ እንዲሁም ከሦስት አመት በፊት ደግሞ ሰበታን በመልቀቅ በሲዳማ ቡና እስከ 2011 ድረስ ያገለገለው ጫላ ዘንድሮ ሲዳማ ለቆ በወልቂጤ አስገራሚ የውድድር ዓመትን ሊጉ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ አሳይቷል። ለቀጣዩ ዓመትም ዳግም በሲዳማ ቡና መለያ ለመታየት ከክለቡ ጋር በጥቅማጥቅም እና በግል ጉዳዮች በመስማማቱ በጥቂት ቀናት ውስጥ የቅድመ ኮንትራት ፊርማውን ያኖራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህም በአዲስ ግደይ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ማምራት የተፈጠረውን ክፍተት ይደፍናል ተብሎ ይጠበቃል።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ