በእግርኳስ የደረት አካባቢ ጉዳቶች ተብለው የሚጠቃለሉት የደረት ጡንቻዎች ጉዳት እና የጎድን አጥንቶች ስብራት ናቸው። የጎድን አጥንቶች ሊሰበሩ ከሚችሉባቸው መንገዶች መካከል በእንቅስቃሴ ወቅት ከጠንካራ ነገር ጋር የሚኖር ግጭት በዋናነት የሚገለፅ ነው። እንደምሳሌ ለመውሰድ ተጫዋቹ በደረቱ አካባቢ በክርን ቢመታ ይህ ጉዳት ሊያጋጥመው ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም በሀይል መሬት ላይ መውደቅ እና ከግብ ቋሚ ጋር መላተም ተመሳሳይ አይነት ጉዳቶች ሊያደርሱ ይችላሉ።
ደረት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ዋንኛ መገለጫ በጣም ከፍተኛ የሆነ የህመም ስሜት ነው። ይህ በሚያጋጥምበት ወቅት ተጫዋቾች ከሜዳው እንዲወገዱ ይመከራል። እንደ ጉዳቱ መጠንና አይነትም ለተወሰኑ ደቂቃዎች አልያም ጨዋታውን ሙሉ ለሙሉ አቋርጠው እንዲወጡ ሊደረግ ይችላል። በደረት ላይ ያለውን ህመም በማሸግ መቀነስ እና መደበኛ ስራን መመለስ የሚቻል ከሆነም እንደ አማራጭነት የሚቀርብ ይሆናል።
የጎድን አጥንት በሚሰበርበት ወቅት የሚስተዋሉ ምልክቶች እንደሚከተለው ቀርበዋል:
- የተጎዱት አጥንቶች ጋር ከፍተኛ የህመም ስሜት
- በመተንፈስ ወቅት የህመም ስሜት (በተለይም ወደውስጥ ሲተነፈስ)
- የተጎዳው አጥንት ሲጫኑት የሚታወቅ ህመም
- የመቁሰል እና የማቀጥ ምልክቶች
- ከጉዳቱ በኋላ የተጫዋቹ ንቃት ፣ አተነፋፈስ እና የደም ዝውውር የሚታይ ሲሆን እርዳታ ካስፈለገም የሚጀመር ይሆናል።
- የአተነፋፈስ ፍጥነት እና አኳሃን በቅርበት የሚታይ ይሆናል።
- የአተነፋፈስ ድምፅን ካዳመጡ በኋላ ሳንባው አየር መያዝና አለመያዙ ይታወቃል።
በአጠቃላይ የጎድን አጥንቶች ስብራት ደረት ላይ ከሚደርሱ ጉዳቶች ግማሹን ቁጥር የሚይዝ ሲሆን በግጭት ከሚፈጠሩ ጉዳቶች ደግሞ 10 በመቶ የሚሆነው የጎድን አጥንት ስብራትን ይመለከታል።
የደረሰው ጉዳት መጠኑ ከፍተኛ ሲሆን እና ከሳንባ ውጪ ክፍተት በመፍጠር አየር እንዲጠራቀም በሚያደርግበት ወቅት Tension Pneumothorax ይፈጠራል። የዚህም ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው።
- በተቀመጡበት ለመተንፈስ መቸገር
- ከእንቅስቃሴ ውጭ ቶሎ ቶሎ መተንፈስ
- የትንፋሽ ድምፅ በተጎዳው የደረት ክፍል አለመኖር እና ሌሎችም ናቸው።
የደረሰው ጉዳት የአጥንት ስብራት እናም የውስጥ አካላት ጉዳትን ካስከተለ ቅርብ ወደሚገኝ ሆስፒታል መላክ አስፈላጊ ሲሆን እንደኦክስጅን ያሉ ተጓዳኝ እና የሚረዱ ነገሮችን ማድረግ ይገባል።
በአጠቃላይ በደረት ምክንያት ከሳምባ ውጪ በተቋጠረ አየር ምክንየዓት የአየር ዝውውር በሚቋጥርበት ወቅት በተለያዩ መንገዶች ማከም ይቻላል። በመጀመሪያ ሁኔታውን በቅርበት መከታተል ሲሆን ከዚህም ላቅ ካለ aspiration እና small bone catheter insertion በተባሉ መንገዶች ማከም እና ፋታ መስጠት ይቻላል። እነዚህ ቴክኒኮች ጊዜያዊ ሲሆኑ ደረት ላይ ቱቦን በማስገባት በደረት ውስጥ ከሳምባ ውጪ የተቋጠረ አየር እና ደም ማስወጣት ቀጣዩ እርምጃ ይሆናል።
እንደዚህ ላሉት ጉዳቶች በአብዛኛው የደረት ራጅ ምርምራ ቀዳሚ ምርጫ ነው። ምንም እንኳን ስብራትን ሙሉ በሙሉ ማሳየት ባይችልም በተደጋገሚ ማየት አስፈላጊ ነው። ካልሆነም የህመም ስሜቱ የሚታከም ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ ከሳንባ ውጪ በደረት ውስጥ ሊኖር የሚችለውን የአየር እና የደም መቋጠር የሚያሳየን ይሆናል።
የጎድን አጥንት ጉዳቶችን ለመመርመር ከራጅ በተጨማሪ የደረት ሲቲ ስካን ሌላው የመመርመሪያ መንገድ ነው ። በሳንባ ውስጥ አየር በሚኖርበት ወቅትም ሌላው መመርመሪያ መንገድ በደም ውስጥ የሚገኙ ጋዞችን መመልከት (pulse oximetry and arterial blood gas) ወሳኝ መንገድ ነው።
የጎድን አጥንት ጉዳቶችን ለማከም በደረት ላይ የሚደረግ ድጋፍን ጨምሮ ማስታገሻዎች (analgesics) ይወሰዳሉ። ጉዳቱ በጣም ህመም የሚያስከትል ከመሆኑ የተነሳ ተጫዋቾች ረዘም ላለ ጊዜ ከሜዳ ለመራቅ ይገደዳሉ። በአጠቃላይ ከአራት እስከ ስድስት ሳምንታት ያህል ቆይቶ ወደ ሜዳ መመለስም የተለመደ ነው።
በአጠቃላይ ህይወትን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ የደረት ላይ ጉዳቶች በአብዛኛው የሚታዩ ባይሆኑም ሊከሰቱ ይችላሉ። ስለዚህም በመጀመሪያ የአተነፋፈስ ፤ ዝውውር እና ንቃት ሁኔታዎችን ቅድሚያ በመስጠት ተጫዋቾችን ማከም ይገባል። ልብ ላይ ሊከሰት ከሚችል ጉዳትም የተነሳ እንደAED (Automated External Defibrillator) አይነት መሳሪያዎች በአቅራቢያው እንዲገኙ ይመከራል።
በመጠን አናሳ የሆነና ምንም አይነት ምልክት የማያሳይ በሳንባ ውስጥ የተቋጠረ አየር በአውሮፕላን በረራ በሚደረግበት ወቅት በመጠን የመጨመር እድል እንዳለው በFIFA Medical Network የፃፉት የSport Emergency Medicine specialist የሆኑት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ቢ ክራመር ገልፀዋል። በመሆኑም በተለይ በመጨረሻ ጨዋታቸው የደረት ግጭት አጋጥሟቸው የነበሩ ተጫዋቾች ከበረራ በፊት ራጅ መነሳት እና የተቋጠረ አየር (pneumothorax) አለመኖሩን ማረጋገጥ ያለባቸው መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ