ዕለተ ሀሙስ በምናቀርበው ይህንን ያውቁ ኖራል? አምዳችን ስለ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና ክለቦችን የተመለከቱ እውነታዎችን ስናቀርብ ቆይተናል። ዛሬም በሊጉ እና ክለቦች ዙርያ ያሉ እውነታዎችን በክፍል 6 ጥንቅራችን ይዘንላችሁ ቀርበናል።
– ከ1990 ዓ/ም ጀምሮ በተደረገው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 51 ክለቦች በውድድሩ ተሳትፈዋል። ከተሳተፉት አጠቃላይ 51 ክለቦች ውስጥ 9 ንግድ እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ 18 የከተማ እና ዞን አስተዳደር፣ 3 የግል እና ሕዝባዊ ክለቦች፣ 14 የአምራች እና የፋብሪካ፣ 2 ዩኒቨርሲቲ (አንደኛው በጋራ የሚተዳደር) እና 5 የጦር እና ፖሊስ ቡድኖች ናቸው።
– በአንድ የውድድር ዓመት በርካታ ክለቦችን ያሳተፈች ከተማ አዲስ አበባ ናት። በ2000 የውድድር ዓመት ከነበሩ 25 ተሳታፊ ክለቦች መካከል 11 ቡድኖች ከአዲስ አበባ ነበሩ።
– በአንድ የውድድር ዓመት ጥቂት የአቻ ውጤቶችን ያስመዘገቡ ክለቦች ምድር ባቡር፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት ናቸው። በ1991 ዓ/ም በተደረገው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ 8ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ምድር ባቡር ካከናወናቸው 18 የሊግ ጨዋታዎች 1ዱን ብቻ በአቻ ውጤት አጠናቋል። ጨዋታውም ታህሳስ 4 የተደረገው የሊጉ የ7ኛ ሳምንት ግጥሚያ ነበር። በጊዜው ቡድኑ ከሜዳው ውጪ ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅን ገጥሞ 1ለ1 ጨዋታውን አጠናቋል። በ1992 የሊጉን ዋንጫ ያነሳው ቅዱስ ጊዮርጊስም እንደ ምድር ባቡር ሁሉ በአንድ የውድድር ዓመት ከተደረጉ ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። በጊዜው አዲስ አበባ ላይ በተደረገ የ22ኛ ሳምንት ግጥሚያ ቡድኑ ከሀዋሳ ከተማ ጋር 1ለ1 ተለያይቷል። ደደቢት ደግሞ ዓምና በተደረገው የውድድር ዘመን ከአዳማ ከተማ ጋር በ11ኛ ሳምንት መርሃ ግብር 1ለ1 አቻ ተለያይቷ የምድር ባቡርን እና ቅዱስ ጊዮርጊስን ሪከርድ ተጋርቷል።
– በአንድ የውድድር ዘመን አቻ ከወጡት ብቸኛ 3ቱ ክለቦች (ምድር ባቡር፣ ቅ/ጊዮርጊስ እና ደደቢት) መካከል በጨዋታ ብዛት ታሳቢነት ጥቂት ጨዋታ የአቻ ውጤቶችን ያስመዘገበው ክለብ ደደቢት ነው። (ቡድኑ ወደ ታችኛው የሊግ እርከን በወረደበት ዓመት ያከናወናቸውን 30 ጨዋታዎች ታሳቢ ስናደርግ)
– በአንድ የውድድር ዓመት በርካታ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁበት ዓመት 2009 ዓ/ም ላይ ነው። በዚህ ዓመት ከተደረጉ አጠቃላይ ጨዋታዎች 86ቱ በአቻ ውጤት ተገባደዋል። ይህም ቁጥር በሊጉ በርካታ የአቻ ውጤት የተመዘገቡበት ዓመት 2009 ዓ/ም እንዲሆን አድርጎታል።
– በሊጉ ታሪክ በአንድ ዓመት ከፍተኛ የግብ ልዩነት ያስመዘገበው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው። በ2000 የውድድር ዓመት 51 የግብ ልዩነት ማስመዝገብ ችሏል።
– በተቃራኒው በአንድ የውድድር ዓመት ከፍተኛ የግብ እዳ ያስመዘገበው ክለብ አርባምንጭ ጨርቃጨርቅ ነው። ክለቡ በ1997 ከሊጉ በወረደበት ዓመት 48 የጎል እዳ አስመዝግቦ ነበር።
– በሊጉ ታሪክ በውድድር ዓመቱ የቡድን እና የግል ሽልማት ከአንድ ክለብ የተገኘው በሁለት አጋጣሚዎች 2004 እና 2006 ነበር። በ2004 ቅዱስ ጊዮርጊስ ቻምፒዮን ሲሆን የቡድኑ አጥቂ የነበረው አዳነ ግርማ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ፣ ተከላካዩ ደጉ ደበበ ኮከብ ተጫዋች፣ ሮበርት ኦዶንካራ ደግሞ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆኗል። በተመሳሳይ በ2006 ቅዱስ ጊዮርጊስ ቻምፒዮን ሲሆን ኡመድ ኡከሪ ኮከብ ተጫዋች እና ጎል አስቆጣሪ፣ ሮበርት ኦዶንካራ ደግሞ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆነዋል።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ