ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ | ምዕራፍ አስር – ክፍል ስድስት

ጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም ምዕራፍ አስር ላይ ደርሷል። ይህ ምእራፍ በእግርኳስ ታክቲክ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ካገኙ የአጨዋወት አቀራረቦች አንዱ የሆነው ካቴናቺዮን ከስር መሠረቱ ጀምሮ ያለፈባቸውን መንገዶች ይመለከታል። የዛሬው መሰናዶም ካለፈው ሳምንት የቀጠለ ነው።


ሄሌኒዮ ሄሬራ ባርሴሎናን ሲለቅ ከበርካታ ክለቦች የ”አሰልጥንልን!” ጥያቄዎች ቢቀርቡለትም እርሱ ግን ከዝውውሩ እጅግ ትርፋማ የሚያደርገውን ክለብ መርጦ ኢንተርን ለማሰልጠን ወደ ሚላን ከተማ ተጓዘ፡፡ በወቅቱ ክለቡን በፕሬዘዳንትነት ይመሩ የነበሩት አንጄሎ ሞራቲ ቀደም ባሉት አምስት ዓመታት ውስጥ የአስራ ሁለት አሰልጣኞች ሹም-ሽር አካሂደዋል፡፡ ሄሬራ ስምምነት ሲፈጽም ፕሬዘዳንቱ ከልባቸው ሲሹ የከረሙትን ስኬት እንደሚያመጣ የእርግጠኝነት ቃል ገባላቸው፡፡ ለዚህም በጊዜው በአለም እግርኳስ ለአሰልጣኞች እጅግ ከፍተኛ የተባለውን ሰላሣ አምስት ሺህ ፓውንድ ክፍያ ጠየቀ፡፡
” አንዳንዴ ውድ የተባለ ምርጫ ርካሽ ሆኖ ሊገኝ ይችላል፤ በተቃራኒው ርካሽ የተባለው ምርጫም ውድ ሆኖ ይገኛል፡፡” ይላል ሄሬራ፡፡ የሚገርመው አርጀንቲናዊው የታክቲክ ሊቅ በመጀመሪያ የውድድር ዘመኑ ከጠበቀው ክፍያ አምስት እጥፍ ያልተጣራ ገንዘብ መቀበሉ ነበር፡፡

ሄሬራ ኢንተርን ማሰልጠን ከጀመረ ጥቂት ሳምንታት በኋላ የተጫዋቾችን ሚስቶች አግኝቷቸው የሥነ-ምግብ ጠቀሜታን አብራራላቸው፡፡ ባሎቻቸው ሊከተሏቸው የሚገቡ መመሪያዎችንም አሳወቃቸው፡፡ አሰልጣኙ በሥራው በቁጥጥሩ ሥር እንዲሆኑ የሚሻቸው ነገሮች ገደብ እንዲኖራቸው አልፈቀደም፡፡ ተጫዋቾች ዘወትር ከቀጣይ ጨዋታቸው ቀደም ብሎ በሚኖረው የዋዜማ ምሽት በአፒያኖ ጄንቲሌ ዋና መሥሪያ ቤት እንዲያሳልፉ የሚያደርግበት “ሪትሮ” የተባለውን ልማድ እንኳ እምብዛም እንዲታወቅ አይፈልግም ነበር፡፡ ” ሐሳቡ ለቀጣዩ ጨዋታ ልዩ ትኩረት ለመስጠት እንጂ ሌላ ነገር አልነበረውም፡፡” ይላል የቡድኑ ተከላካይ ታርጊሲዮ በርኚች፡፡ ” በካምፓችን በምንቆይበት ጊዜ ወደ ውጭ አንወጣም፡፡ ትሰለጥናለህ፤ ትመገባለህ፤ ትተኛለህ፤…በቃ፡፡ ነጻ የምንሆንበት ሰዓት ስናገኝ ካርታ ከመጫወት የዘለለ ሌላ እንቅስቃሴ አንከውንም፡፡ ስለዚህ ስለ ቀጣዩ  ጨዋታ በጥልቀት ከማሰብና ማሰላሰል ያለፈ ተግባር አይኖረንም ማለት ነው፡፡ ለከባድ ጨዋታዎች ትኩረት ለመስጠት ሲባል በአንድ ውስን ቦታ ላይ ተሰብስቦ የመቀመጥ ሥርዓቱ (Retreats) አልፎአልፎ ከሆነ ያን ያህል አስቸጋሪ ላይሆን ይችላል፤ ነገርግን በተደጋጋሚ ጊዜ ለመተግበር ካሰብክ ተጫዋቾችህን ታሰላቻቸዋለህ-እናም ችግር ይፈጠራል፡፡” ብሏል ታርጊሲዮ፡፡

ሁሉም ነገር- ከመኝታ እስከ ልምምድ፣ ከአመጋገብ እስከ እረፍት አወሳሰድ ድረስ ተጫዋቾች የሚያደርጓቸው ማናቸውም እንቅስቃሴዎች የቅርብ ክትትል ይካሄድባቸዋል፡፡ እንግሊዛዊው አጥቂ ጌሪ ሂችንስ የሄሬራን ኢንተር ሲለቅ ” እጅግ ጥብቅ ቁጥጥር ካለበት የጦር ሰራዊት ካምፕ የመውጣት ያህል ነው፡፡” እስከማለት ደርሷል፡፡ አንድ ጊዜ ደግሞ እርሱ (ጌሪ ሂችንስ)፣ ሉዊስ ሱአሬዝ እና ማሪዮ ኮርሶ የአካል ብቃት ልምምድ እየሰሩ በረጅም ርቀት ሩጫ (Cross-Country Run) ወቅት እጅግ ዘግይተው ወደ ማዕከሉ በመድረሳቸው የቡድኑን ተጫዋቾች የሚያመላልሰው አውቶቡስ ትቷቸው እንዲሄድ በመታዘዙ አስር ኪሎሜትር ገደማ ያህል በእግራቸው ሄደው የክለቡ ማረፊያ ወደሚገኝበት ከተማ  መጓዛቸውን ያስታውሳል ሂችንስ፡፡ በወቅቱ የኢንተር ኮከብ የነበረው ሳንድሮ ማዞላም ሄሬራ ለቅድመ-ዝግጅት የሚሰጠው ልዩና የበዛ ትኩረት የልክፍት ያህል ሆኖበት እንደነበር ያምናል፡፡
” በ1966-67 የውድድር ዘመን በአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ <ቫሳስ> የተባለውን ክለብ ካሸነፍን በኋላ በየመታጠቢያ ክፍላችንን ሆነን ገላችን እየታጠብን ‘ሁለት የእረፍት ቀናት የምናገኝበት ዕድል ቢመቻችልን…..’ ብለን እንነጋገራለን፡፡ ምክንያቱም ያለምንም ማጋነን ያን ሰሞን በካምፕ መኖርን ልምድ አድርገነው ነበር፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ይህን ፍላጎታችንን ስንጨዋወት ሄሬራ ለካ ይሰማን ኖሯል፡፡ በቀጥታ ወደ’ኔ መጣና ‘ የቱንም ያህል ስኬታማ እንደሆንክ ብታስብ ሁሌም ቢሆን በእግርህ መሬት መርገጥ እንዳለብህ አትዘንጋ!” አለኝ፡፡ ማናችንም አንዲት ትንፍሽ ሳንል ወደ  አፒያኖ ጄንቲሌ (ካምፓችን) ተመለስን፡፡” ብሏል ማዞላ የሄሬራን ቆራጥ አመራር እና የተጫዋቾች አያያዝ ትውስታውን በተመለከተ ሲያወጋ፡፡

በሄሬራ ዘንድ ሥነ-ምግባር አይነኬ ጉዳይ ነበር፡፡ በአሰልጣኙ ስልጣን ሊመጣ የሚሞክር ማንኛውም አካል በጣም የከፋ ጭቆናን ለመጋፈጥ ይገደዳል፡፡ ሄሬራ በባርሴሎና ሳለ ሃንጋሪያዊውን የመሃል አጥቂ ላዲስላኦ ኩባላን ” በአሰልጣኝነት ህይወቴ ከገጠሙኝ ተጫዋቾች በሙሉ የላቀው ባለክህሎት” እያለ ቢያሞካሸውም ያለበት ከባድ የመጠጥ ሱስ የግል ብቃቱን እያሳጣው፥ ለክለቡ የሚሰጠውን ግልጋሎትም እየቀነሰበት ስለሆነ በሚል ከቡድኑ እስከማግለል ደርሷል፡፡ በወቅቱ የኩባላ ይቅርታ መጠየቅ አርጀንቲናዊው አሰልጣኝ ተጫዋቹ በባርሴሎና የገነባውን የአድራጊ-ፈጣሪ ግለ-ስብዕና  (Kubalismo) መስበር መቻሉን አመላክቷል፡፡ በተመሳሳይም ሄሬራ ኢንተርን እንደያዘ በ1958-59 የውድድር ዘመን በሰላሣ ሶሥት ጨዋታዎች ሰላሣ ሶሥት ግቦች ማስቆጠር የቻለውን አርጀንቲናዊ የክለቡ አጥቂ አንቶኒዮ አንጄሊዮን አሽቀንጥሮ ለማስወጣት ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ አጥቂው በማህበራዊ ህይወቱ የነውጠኝነት ባህርይ ይታይበት ነበር፡፡ ስመ-ጥሩ “ሊቤሮ” አርማንዶ ፒቺ እንኳ በክለቡ የረጅም ጊዜ ቆይታ ዋስትና አላገኘም፡፡ ፒቺ የሄሬራን ውሳኔ- አሰጣጥ በተመለከተ ጥያቄ በማንሳቱ በ1967 <ቫሬዜ> ለተባለው ክለብ እንዲሸጥ ተደርጓል፡፡

” በተጫዋቾች ዘንድ ጨቋኝ እና ፍጹም ምህረት-የለሽ ተደርጌ ስከሰስ ኖሬያለሁ፡፡ እኔ ያደረግኹት ግን ኋላ ላይ ሌሎች ብዙ ክለቦች ቀጥታ ወስደው ሲጠቀሙበት የነበረውን ነው፡፡ ጠንክሮ መሥራት፣ ምሉዕና እንከን አልባ ሆኖ መገኘት፣ ከበድ ያለ የአካል ብቃት ልምምድ፣ ምክንያታዊ የአመጋገብ ሥርዓት እና ከየትኛውም ጨዋታ በፊት ለጥልቅ ትኩረት ሲባል ለሶስት ቀናት ያህል ተጫዋቾች በካምፕ እንዲቆዩ ማድረግ፡፡” ሲል በተጫዋቾች አያያዝ ላይ የሚቀርብበትን ትችት ለመከላከል ይሞግታል፡፡

ሄሬራ ለቅድመ-ዝግጅት ብሎ ዝርዝር መረጃዎች የሚያሰፍርባቸው ሰነዶቹ በራሱ ቡድን ሥራ ላይ ብቻ አተኩረው የሚያበቁ አይደሉም፤ ከዚያ አልፈው ተጋጣሚን የመገምገም ተግባርንም ያካትታሉ፡፡ የእርሱ ተጫዋቾች ቀጥተኛ ባላጋራዎቻቸውን በአግባቡ ለማወቅ በምስል የተደገፈ ማብራሪያ ሳያስፈልጋቸው በሄሬራ አንደበት በሚሰጡ ጥልቅ ትንታኔዎች ብቻ በቂ መረጃ ያገኙ ነበር፡፡ በ1961 ከባርሴሎና ወደ ኢንተር ሲያቀና የዓለም ከፍተኛው የዝውውር ሒሳብ የወጣበት ሉዊስ ሱአሬዝ የሄሬራን የስልጠና አቀራረብ ቀደም ሲል ያልታየ እንደነበር ያስረዳል፡፡ ” እርሱ ለአካል ብቃትና ስነ-ልቦና የሚቸረው ትኩረት ከዚያ ቀደም በማንም የታየ አልነበረም፡፡ ሄሬራ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ የአሰልጣኞች ፋይዳ እምብዛም ነበር፡፡ በንጽጽር ላቅ-ላቅ ያሉ ተጫዋቾችን ይመርጥና ያሰልፋቸዋል፤ ጥሩ ካልሆኑ የተሻለ ብቃታቸውን እንዳላወጡ ያሳምናቸዋል፤ ሌሎቹን ደግሞ ያሞጋግሳቸዋል፡፡ በመጨረሻ አሰልጣኙ ገሚሶቹ (የተወደሱት) ልክ መሆኑን፥ ቀሪዎቹ (የተተቹት) ደግሞ ትክክል አለመሆኑን ለማረጋገጥ ሁሉም ለቡድኑ ያላቸውን ለማበርከት ይነሳሳሉ፡፡” ሲል የሄሬራን ብልሃታዊ አመራር ይተነትናል፡፡ 

ሄሬራ ኢንተርን በተረከበ የመጀመሪያው ጨዋታ በቤርጋሞ አታላንታን 5-1 ረታ፤ በቀጣዩ የሜዳ ውጪ ጨዋታም ዩድኒዜን 6-0 ረመረመ፤ ቪቼንዛ ላይም አምስት ግቦች አስቆጥሮ አሸነፈ፡፡ኢንተር ያን ዓመት ከሊጉ ባለድል ጁቬንቱስ በቀር ከሌሎቹ ክለቦች በላቀ መጠን በሰላሣ አራት ጨዋታዎች ሰባ ሶሥት ጎሎች በማስቆጠር በደረጃ ሰንጠረዡ ሶስተኛ ሆኖ ጨረሰ፡፡ ቀጣዩን ዓመትም ኢንተሮች መሻሻል አሳይተው በሊጉ ሁለተኛ በመሆን ቢያጠናቅቁም ለሞራቲ በቂ አልነበረም፡፡ ፕሬዘዳንቱ በክረምቱ ኤድሙንዶ ፋብሪ የሄሌኒዮ ሄሬራ መንበር ተረካቢ እንዲሆን ከጅለው አፒያኖ ጄንቲሌን እስከማስጎብኘት ደረሱ፡፡ በመጨረሻ ደቂቃ ሐሳባቸውን ቀይረው ፋብሪን ወደ ቤቱ ከሸኙ በኋላ ሄሬራ በክለቡ ሲቀጠር ለማሳካት ቃል የገባውን ውጤት ማምጣት እንዳለበትና ለዚያ ደግሞ አንድ ዓመት ብቻ እንደተሰጠው ገለጹለት፡፡  ይህን ጊዜ ሄሬራ ራሱን መቀየር እንዳለበት ወሰነ፡፡

” የመሃል አማካይ ከቦታው አንስቼ ከተከላካዮቹ ጀርባ በጠራጊ-ተከላካይነት እንዲሰለፍ አደረግሁ፤ የግራ መስመር ተከላካዩ (Left-Back) ደግሞ ነጻ ሆኖ የማጥቃት ሒደቱ ላይ እንዲሳተፍ ፈቀድኩ፡፡ በማጥቃት የጨዋታ ሒደት ሁሉም ተጫዋቾች ምን እንደምፈልግ ያውቃሉ- የተጋጣሚ ሳጥን ክልል ለመድረስ ከሶስት ቅብብሎች በላይ የማያስፈልግበት እና ከፍተኛ ፍጥነት የተላበሰ ቀጥተኛ እግርኳስ፡፡ በሜዳው ቁመት (Vertically) ስትጫወት ቅብብሎችህ ተበላሽተው ኳስ ብትቀማ ብዙ ችግር ላትፈጥር ትችላለህ፡፡ በሜዳው ስፋት (Laterally) ይህን ስህተት ብትፈጽም ግን መዘዙ የከፋ ይሆናል- ምናልባትም ግብ ተቆጥሮብህ ዋጋ ልትከፍል ትችላለህ፡፡” በማለት የለውጡን መነሻ ያወሳል፡፡

በሴሪ-ኤ ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ አስቆጥሮ የከረመው ፒቺ  ትጉህ ጠራጊ-ተከላካይ (Sweeper) ሆነ፡፡ ጂያኒ ብሬራ ፒቺን ” በአጭር ጊዜ ውስጥ የተከላካይ ክፍሉ መሪ ለመሆን የበቃ፤ አስደናቂ እይታን የታደለ እና ቅብብሎቹ ዘፈቀዳዊ አልያም እንዲሁ በነሲብ የማይከወኑ ነበሩ፡፡” በማለት ምስክርነት ይሰጥለታል፡፡ አርስቲዴ ጓርኔሪ በመከላከል ሲሶው የመሃለኛውን ክፍል በመያዝ   እንደ መሃል ተከላካይ ወይም እንደ ተከላካይ አማካይ (Stopper Central-Back) ሆኖ ሲጫወት የቀኝ መስመር ተከላካዩ (Right-Back) በርኚች ደግሞ ከጎኑ ተሰልፎ ጠንካራ ጥምረት ለመፍጠር ይሞክር ጀመር፡፡ ማራዴይ የሄሬራን ለውጥ አስመልክቶ ” በጊዜው በርካታ ቡድኖች የቀኝ መስመር አማካያቸውን በ<ቶርናንቴ> ሚና
ማሰለፍ ጀምረው ነበር፡፡ ይህም የግራ መስመር አማካዮች የተሻለ የማጥቃት አበርክቶ እንዲኖራቸው አደረገ፤ ከመስመር ወደ መሃል እየገቡም የጎል ሙከራዎችን እንዲከውኑ አስቻላቸው፡፡ ጂጂ ሪቫና ፒዬሪኖ ፕራቲን የመሳሰሉ አብዛኞቹ ጣልያናውያን ታላላቅ የፊት መስመር ተሰላፊዎች የተገኙትም በዚሁ የቦታ ሽግሽግ ሒደት ነበር፡፡” ይላል፡፡

       ምስል፦ ታላቁ ኢንተር

ይቀጥላል...


ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሦስት ዓመታትም አስር መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡