ዘውዱ መስፍን የት ይገኛል?

በክለብ ደረጃ ለበርካታ ትላልቅ ክለቦች የተጫወተው ግብ ጠባቂው ዘውዱ መስፍን አሁን የት ይገኛል?

በሜዳ ውስጥ በሚያሳያቸው ባህርያት እና በእግሩ የመጫወት ብቃቱ ብዙዎች ያስታውሱታል። በእግር ኳስ ሕይወቱ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ መከላከያ ፣ ወንጂ ፣ መተሀራ ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ወልዋሎ ፣ ባህርዳር ከተማ እና አውስኮድ ተጫውቷል። ሜዳ ውስጥ የተለየ የአልሸነፍ ባይነት ባህሪ ያለው ይህ ግብ ጠባቂ በ2010 ለወልዋሎ እየተጫወተ ራሱ ላይ ጎል ካስቆጠረበት ክስተት በኋላ በትልቅ ደረጃ መጫወት አልቻለም፤ ሶከር ኢትዮጵያም ይህን አስመልክታ “የት ይገኛል?” ስትል ከተጫዋቹ ጋር ቆይታ አድርጋለች።

ስለ ወቅታዊ ሁኔታው

ወቅቱ የኮሮና ስለሆነ አብዛኛው ጊዜዬን በቤቴ ነው የማሳልፈው፤ ከዛ ውጭ በግል ልምምዶች እሰራለሁ። የአካል ብቃት እና ሌሎች የግል ልምምዶች እየሰራሁ ነው።

ከእግር ኳሱ የራቀበት ምክንያት

የመጫወት አቅሙ አለኝ። በቅርቡ በትልቅ ደረጃ ያልተጫወትኩበት ምክንያትም እንደ ሌሎች ብዙም አልሯሯጥም፤ ምክንያቱ እሱ ነው እንጂ የመጫወት አቅሙ እና ፍላጎቱ አለኝ። አሁንም በትልቅ ደረጃ መጫወት እችላለሁ።

ስለ አይረሴው የወልዋሎ ከፋሲል ከነማ ጨዋታ ትውስታ

ስለ ሁኔታው የተለየ ትውስታ የለኝም። በእግር ኳስ የሚያጋጥም ነገር ነው የገጠመኝ፤ በርግጥ ሁኔታው ከተከሰተ በኋላ የሚሰማህ ነገር አለ። ከዛ በኃላ ግን ትልቅ ትምህርት ሆኖኝ ነው ያለፈው። ትኩረቴን ጨዋታ ላይ ብቻ አድርጌ እንዴት መጫወት እንዳለብኝ ትምህርት ወስጄበታለሁ።

ከክስተቱ ባሻገር በወልዋሎ የመጨረሻ ጊዜያት ስለነበረው አቋም

በዛ ወቅት ልምምድ ላይ ተደጋጋሚ ጉዳት አስተናግድ ነበር። በዛ ሰዓት ሜዳው አመቺ አልነበረም ልምምድ ስሰራም ብዙ መላላጥ እና ሌሎች ጉዳቶች ነበሩ። በዛን ሰዓት የነበረኝ ጥሩ ወቅታዊ ብቃት እንዳላስቀጥልም በተደጋጋሚ የገጠሙኝ ቀላል ጉዳቶች እክል ሆነውብኛል። በዛን ሰዓት ግን ጥሩ ብቃት ላይ ነበርኩ።

ሌላው የማይረሳው አጋጣሚ

ወንጂ እያለሁ ከሀዋሳ ከተማ እየተጫወትን ያጋጠመኝ ማይረሳ አጋጣሚ አለ። እነሱ አንድ ለባዶ እየመሩን ነበር ከዛ አንድ ከጨዋታ ውጭ የሆነን ኳስ ለማምጣት ስሄድ በኃይሉ አሰፋ በአጋጣሚ በኳሳ መቶኝ ራሴ ስቼ ሆስፒታል የሄድኩበት አጋጣሚ አልረሳውም። እነሱ እየመሩን ስለነበር ሰዓት ለመግደል ኳሷን መቷት እኔም ላመጣት ስሄድ በአጋጣሚ ጎንበስ ስል ለካስ ኳሳን ቀድሞ መቷት ነበር፤ ከዛ መታችኝ እና ራሴን ስቼ ወደ ሆስፒታል ገባሁ ሁለት ቀን ቆይቼ ነው የወጣሁት። ይሄን አጋጣሚ አልረሳውም።

በድጋሚ በትልቅ ደረጃ የመጫወት እቅዱ

አቅሙ አለኝ በክለብ ደረጃም ብዛ ሳይሆን በብሄራዊ ቡድን ደረጃም የመጫወት ዕድሉ ከተሰጠኝ ብቃቴን አውጥቼ ለመጫወት አልቸገርም። በእግር ኳሳችን ለግብ ጠባቂዎች የሚገባውን ግምት አይሰጥም። ከዛ በተጨማሪ ደግሞ አሰልጣኞቻችን በእግር የሚጫወት ተጫዋች አይፈልጉም። እኔ በግሌ ደግሞ ኳስ መለጋት አልወድም መስርቼ መጫወት እና መቀባበል ነው የምፈልገው።

ስለ ቀጣይ እቅዱ

በቀጣይም በትልቅ ደረጃ መጫወት ነው። ቅድም እንዳልኩህ የመጫወት አቅሙ እና ፍላጎቱ አለኝ።

አርዓያዎቹ

በእግር ኳስ አርዓያዬ ስፔናዊው ኢከር ካስያስ ነው እሱን እያደነቅኩ ነው ያደግኩት።

በመጨረሻ 

መላው የሀገራችን እግርኳስ ደጋፊ ማመስገን እፈልጋለው። እኛንና እግር ኳሱን ለማየት ብሎ ለሚመጣው የእግር ኳስ ቤተሰብ ልዩ አክብሮት አለኝ።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ