የደጋፊዎች ገፅ | ትንፋሹን ለሚወደው ክለብ… – እዮብ እድሉ

የረጅም ዓመት የቅዱስ ጊዮርጊስ የልብ ደጋፊ ነው። በሁሉም የፈረሰኞቹ ደጋፊዎች ዘንድም የሚከበር እና የሚወደድ ነው። ባለው የሙዚቃ ተሰጥኦ የሚወደውን ክለብ የሚያወድሱ በርከት ያሉ ዜማዎችን ሠርቷል። የዛሬው የደጋፊዎች ገፅ አምዳችን እንግዳ የሙዚቃ ባለሙያው እዮብ እድሉ (እዮባ ሳንጃው) ነው።

ድምፃዊ ፣ የሙዚቃ መሳርያ ተጫዋች ፣ የሙዚቃ አቀናባሪ ፣ የግጥም ፀሐፊ ሁለገብ የሙዚቃ ባለሙያ ነው። ከልጅነት እስከ ዕውቀት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ነው። በተሰጠው ፀጋ ለሚወደው ክለቡ የተለያዩ የሙዚቃ ስራዎችን በመስራት የክለቡን ታሪክ ፣ ጉዞ ፣ ስኬት እና ወጣ ውረድ አሁን ላለው ትውልድ ለወደፊትም ጭምር እያስተላለፈ ይገኛል። በዛሬ የደጋፊዎች ገፅ አምዳችን የረጅም ዓመት የቅዱስ ጊዮርጊስ የልብ ደጋፊ የሆነው እና በስራዎቹ ተወዳጅነትን ያተረፈው እዮብ እድሉን አቅርበናል። መልካም ቆይታ

ቅዱስ ጊዮርጊስን ለመደገፍ ምን አነሳሳህ? ከዚህ ጥያቄ በመጠየቅ ልጀምር ?

ቅዱስ ጊዮርጊስ እግርኳስን ለሚወድ ሰው ስሙ ሩቅ አይደለም። በሬድዮ የምሰማው ነገር እና ትልልቅ ሰዎች የሚያወሩት ስሰማ ያጓጓኝ ነበር። ስታድየም ደግሞ ሄጄ ሳየው የእኔነት ስሜቱ ተጋብቶብኛል። ህፃን ሆነንም ኳስ ስንጫወት የጊዮርጊስን መለያ በሹራብ ‘V’ አስረተን የምንለብሰው ፣ ታላላቆቻችንም የሚያደርጉት ነገር ከሰው መሀል ነጥሎ ጊዮርጊስን እንድንሳብ አድርጎናል። እኔም በባህሪዬ ለየት ያለ ነገር ስለሚማርከኝ በእነዚህ በእነዚህ ምክንያቶች ጊዮርጊስን መደገፍ ልጀምር ችያለሁ።

ለመጀመሪያ ጊዜ የቅዱስ ጊዮርጊስን ጨዋታ የተመለከትክበትን ጊዜ ታስታውሰዋለህ ?

አዎ በ1988 ላይ የአንደኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ነው ፤ የጊዮርጊስ ወጣት ቡድን ከአየር መንገድ ጋር ሲጫወት ነበር የተመለከትኩት። ሆኖም ግን በተከታታይ ስታድየም እየገባው ኳስ ማየት የጀመርኩት 1994 ወይም 1995 ጀምሮ ነው። በጣም የሚገርም 1991 ላይም የመጀመሪያውን የፕሪምየር ሊጉን የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡናን የሸገር ደርቢ ጨዋታን ለማየት ችዬ ነበር። ያ ማለት ጊዮርጊስ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲያድግ ያደረገውን የመጀመሪያ ጨዋታ ማለት ነው። እንደሚታወቀው 1987 እና 1988 ጊዮርጊስ ቻምፒዮን ሆኖ 1989 ላይ ለብሔራዊ ቡድን ሄደው የጠፉ የዋና ቡድን ተጫዋቾች ነበሩ ፣ ለወጣት ቡድንም ሄደው የጠፉ ተጫዋቾች ነበሩ። በዚህ ምክንያት ከየትምህርት ቤቱ በሰበሰባቸው ተጫዋቾች ነበር የተጫወተው። በዚያ ዓመት ቡና ጊዮርጊስን 4-0 ሁሉ አሸንፎ ቻምፒዮንም ሆኖ ነበር። ቀጣዩ ዓመት ላይ ጊዮርጊስ እስከ ድሬዳዋው ጨዋታ ምንም ሳይሸነፍ መምጣት ችሏል። 1990 ላይ ኤልፓ ነበር ቻምፒዮን የሆነው። ከዚያ ነው 1991 ላይ የሊጉ መክፈቻ ላይ ጊዮርጊስ እና ቡና የተገናኙት። ያኔ እንደውም ትዝ ይለኛል ስታድየሙ ውስጥ የቡና ደጋፊዎች በመሐሙድ አህመድ ዜማ ‘እንዴት ይረሳል እንዴት ይረሳል ተረሳሽ ወይ ?’ ብለው ሲያዜሙ በጊዮርጊስ ደጋፊዎች በኩል ደግሞ በእሳቱ ተሰማ ዘፈን ‘ወደ ኋላ እየሄድሽ በሀሳብ ከማለም ፤ ቀኑ እንዳይመሽብሽ ትናንት ዛሬ አይደለም’ የሚል ምልልስ ነበር። በዚያ ጨዋታ ጊዮርጊስ 4-1 አሸንፎ የጨፈርንበትን በደንብ አስታውሳለሁ። ክፍለ ሀገር ደግሞ እየሄድኩ ማየት የጀመርኩት ከ1999 አካባቢ ጀምሮ ነው።

የሙዚቃ ባለሙያ ነህ እንዴት ነው ሙያህን ከቅዱስ ጊዮርጊስን ጋር ማስተሳሰር የጀመርከው ?

በእርግጥ ሙያተኞች ሆነው በሙያቸው ጊዮርጊስን የሚያገለግሉ ደጋፊዎች ድሮም ነበሩ ፤ አሁንም ብዙ አሉ። ሙዚቃ በባህሪው የሚታይ እና የሚገዝፍ ስለሆነ የኔ ተጋነነ እንጂ ከሌሎች ደጋፊዎች የተለየ ነገር አድርጊያለው ብዬ አላስብም። ነገር ግን ለጥበብ ካለኝ ፍቅር አንፃር እግር ኳስም ያው ጥበብ አይደል ? አንዳንዴ መስራትም መብላትም እንደመፈለግ ዓይነት ፤ እንደዛ ሆነብኝ እና እግርኳሱን ከጊዮርጊስ ጋር አያያዝኩት እና በሙያዬ ለጊዮርጊስ አንድ ነገር ማበርከት አለብኝ ብዬ ጀመርኩኝ። ደግሞም የተለያየ ሙያ እያላቸው እኮ ለክለቡ በምን መንገድ ማበርከት እንዳለባቸው ያላወቁ ሰዎችም ይኖራሉ ፤ ለእነዛ ሰዎችም ምሳሌ ለመሆን ነው። ለኔ ሙዚቃ ስራዬ ነው። ማንኛውንም የሙዚቃ ስራዬን እንደምሰራው ነው የጊዮርጊስንም ስራ የምሰራው። እኔ ባለኝ ነገር በሙያዬ ነው እየሰራሁ ያለሁት። ይህ ደግሞ ከክለቤም አልፎ ለሀገርም ጭምር ትልልቅ አርቲስቶችም ተሳተፉበት ከእስከ ዛሬ ስራዎቼ በተለየ አኳኋን የተለየ ስራ እየተሰራ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እየደረሰ ይገኛል።

እጅግ በርካታ ዜማዎችን ያለክፍያ በነፃ ለቅዱስ ጊዮርጊስ አበርክተሀል። እስቲ ምን ያህል ስራዎችን ሰራህ ?

በሙዚቃ ደረጃ የሰራሁዋቸው ከ25 በላይ ናቸው። ለ80ኛ ዓመት ክብረ በዓል ተብሎ ደግሞ የተለመዱ እና አዳዲስ 10 የሚሆኑ ስራዎችን ሰርቻለሁ። በተጨማሪም ስታድየም ውስጥ እየተቀባበልን የምንዘምራቸው በአልበም ያልተካተቱ ከ15 በላይ ዜማዎችም አሉ። እኔ ሁሌም ቁጥራቸውን አላስበውም። ብዙ ሰው መሰጠት የሚለውን ነገር ሲያስበው መጉደል ያለ ይመስለዋል ፤ እኔ ግን እንደዛ አላስብም። እንደውም እርካታው በቃላት የማይገለፅ ነው። ያንን ስለማስብ እና ይህንን ስሜትም ስለምወደው ነው ሁሌም ስለመስራት የማስበው። ወደፊትም የምወደውን ክለቤን በሙያዬ ለማገልገል ሳልታክት የምችለውን ሁሉ በደስታ አደርጋለው። ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደታላቅነቱም እንደቀደምትነቱም እኔ ካደረኩለትም በላይ የሚገባው ክለብ ነው። እንደውም ያደረኩት በጣም ትንሽ ብዬ ነው የማስበው።

ጠቅለል ወዳሉ ሁሉን ደጋፊዎች ወደሚመለከቱ ጥያቄዎች ልምጣ። በአሁን ሰዓት አብዛኛው ደጋፊ በተለያዩ መንገዶች ተስቦ ክለቡን እና ክለቡን ብቻ አስቦ ለመደገፍ ይመጣል። የዛኑ ያህል ሌላ ሀሳብ ይዞ የሚመጣም አለ። በአንዳንድ ወገኖችም ተደጋፊ እንጂ ደጋፊ የለም ፤ ከክለቡ ለመጠቀም ነው የሚመጣው’ ሲባል ይሰማል። በዚህ ላይ ምን ሀሳብ አለህ ?

እንግዲህ ይህንን የሚሉ ሰዎች የራሳቸው ምልከታ ይኖራቸዋል። እኔ ደግሞ እንደ አንድ ደጋፊ የምመለከተውን ነው መናገር የሚኖርብኝ። አብዛኛው ደጋፊ ስራውን ትቶ ፣ ቤተሰቡን ትቶ ፣ ገንዘብ አውጥቶ ፣ ጊዜውን ሰውቶ ፣ ዕውቀቱን ሰጥቶ ነው የሚመጣው ፤ እግርኳስን ከማየት አንፃር ብቻ። እኔ ጊዮርጊስን በማየት የማገኘውን ደስታ ማንም ሰው ፣ የትኛውም ኃይል አይሰጠኝም። እኔ ስታድየም የምመጣው ለራሴ ብዬ የትም ብሄድ የማላገኘውን ይህንን ደስታ ለማግኘት ስል ነው። አብዛኛው ደጋፊም እንደዚህ ብሎ ነው የሚመጣው። የጊዮርጊስ ብቻ ሳይሆን የትኛውም ደጋፊ ጓደኞቹንም አይቶ ይሁን በቴሌቭዥንም አይቶ የሚመጣው ለመደገፍ ነው። ይህን ስል ግን ከደጋፊነት ወደ ተደጋፊነት የሚያሸጋግሩ መስመሮች አይኖሩም ብዬ አላስብም። ነገር ግን አብዛኛውን ደጋፊ አይወክሉም። ቢበዛ 2% ቢሆን ነው ፤ እሱንም እርግጠኛ ሆኜ ሳይሆን የለም ብዬ መደምደም ስለማልችል ነው። አፌን ሞልቼ መናገር የምችለው ግን የየትኛውም ክለብ ደጋፊ መጀመሪያ የሚመጣው እግርኳሱን ብሎ መሆኑን ነው።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእግርኳሱ አካባቢ ከስፖርቱ መንፈስ ውጪ የሆኑ ነገሮች እየገቡ አደጋገፉ መስመሩን ሲስት ተመልከተናል። በዚህ ጉዳይ ምን ትላለህ ?

በመሀከላችን ያለው ርቀት እንደተጠበቀ ሆኖ መስመራችንን ግን ማጥራት አለብን ብዬ አስባለሁ። ለምሳሌ በደጋፊ እና በደጋፊ መካከል ያለው ልዩነት እና አንድነት በግልፅ መቀመጥ መቻል አለበ። በዳኞች እና በክለቦች መካከል ፣ በክለቦች እና በክለቦች መካከል ፣ በተጫዋቾች እና በክለቦች መካከል ፣ በክለቦች እና በደጋፊዎች መካከል ፣ በክለቦች እና በጋዜጠኞች መካከል ፣ በድጋፊዎች እና በደጋፊዎች መካከል ፣ በጋዜጠኞች እና በደጋፊዎች መካከል ፣ በጋዜጠኞች እና በጋዜጠኞች መካከል ያለው ግንኙነት ሁሉ መጥራት አለበት ብዬ አስባለሁ። ይሄንን በሚገባ ካላጠራን በቀር አሁንም እግርኳሳዊ ያልሆኑ ምክንያቶች መፈጠራቸው የሚቀር አይመስለኝም። ሁሉም ነገር እግርኳሳዊ የሚሆነው አወቃቀሩንም እግርኳሳዊ ስናደርገው ነው። ይሄንን ለማድረግ ደግሞ ተነሳሽነቱ ሊኖር እንደሚገባ አስባለሁ።

እግርኳሳችንን የሚታደግ ፣ ሜዳዎቻችን የእግርኳስ ጠረን እንዲኖራቸው እና ሁሉንም ክለቦች የሚያስተሳስር ፣ የሚያቀራርብ ሙዚቃ በሙያህ ለማበርከት ታስባለህ ?

አዎ ‘ሀ’ ብለን ጀምረናል። ሰዉ ልዩነቶችን ማስታረቅ አንድ መሆን ይመስለዋል። ለምሳሌ ‘እኛ እና ቡና አንድ ነን’ ሲባል ወይም ቡናዎች ‘እኛ እና ጊዮርጊስ አንድ ነን’ ሲሉ እሰማለሁ። ይሄ የተሳሳተ አባባል ነው። አንድ አይደለንም። አንድ ብንሆንማ የተለያየ ክለብ አንደግፍም ነበር። ነገር ግን በልዩነታችን ተከባብረን እንደ አንድ መቆም እንችላለን። በተለያዮ ሜዳዎች የሚፈጠሩ እግርኳሳዊ ያልሆኑ ያልተገቡ ነገሮች መቀረፍ አለባቸው። ማንም ሰው ወደ ስታዲየም መጥቶ ያለ ስጋት በእግርኳሱ ተዝናንቶ፣ የሚወደውን ክለብ ባማረ ዜማ ደግፎ በደስታ መጥቶ በደስታ መመለስ አለበት። ይህንንም አስመልክቶ ከሌሎች ክለቦች ደጋፊዎች ጋር የተነጋገርኳቸው ልሰራቸው ያሰብኳቸው ስራዎች አሉ። ወደፊት የሚወጣ ይሆናል። ዞሮዞሮ ሙዚቃ ትልቅ ጉልበት ያለው በመሆኑ ይህን ተጠቅመን ሜዳዎቻችን ሰላማዊ አየር የምንተነፍስበት እንዲሆኑ ማድረግ አለብን።

ወደምታዜምለት ክለብህ ጥያቄ ልመለስ በዚህ መጠን የምትደግፈው ክለብህ ቅዱስ ጊዮርጊስ በውጤት መለኪያ ሲታይ አሁን የምትፈልገው ደረጃ ላይ ነው ያለው ?

እንደሰው መቼም ፍላጎታችን ብዙ ነው። በእነባርሴሎና እና በእነማድሪድ ደረጃ ያሉ ክለቦችም የራሳቸው ፍላጎት ይኖራቸዋል። እኔም ክለቤ እዛ ደረጃ ይደርሳል ብዬ ተስፋ ያለኝ ሰው ነኝ። ለክለቤ ከዛሬ ለነገ ፣ ከነገው ደግሞ ከነገ ወዲያው ይሻላል ብዬ በክለቤ ላይ ትልቅ ዕምነት የምጥል ደጋፊ ነኝ። ክለቤን እንደ ልጄ ነው የማየው። ልጄ ኢንጂነርም ዶክተርም ሁሉንም ነገር ቢሆንልኝ ደስ ይለኛል። ባይሆንልኝም ግን ልጄ ነው። መጀመሪያ በእኔ እና በክለቡ መካከል ያለው ወዳጅነት ይበልጣል ብዬ ነው የማስበው። ከዚያ በኋላ ቀጣዮቹ በሀገር ፣ በክፍለሀገር ፣ በአህጉር አልፎም በዓለም ደረጃ ያሉ ስኬቶች ይመጣሉ ብዬ ነው የማስበው።

ቅዱስ ጊዮርጊስን በደገፍክባቸው እነኚህ ዓመታት ሁሉ ያንተ ምርጡ ተጫዋች ማነው ?

በጣም ይከብዳል። አስጨፋሪ ስትሆን ስሜትህን ከመግለፅ ትቆጠባለህ። ስሜትህ ሰዎች ላይ ይጋባል፤ በክፉም ይሁን በጥሩ። እኔ በተሻለ መጠን ስሜቴን መቆጠብን ነው የምመርጠው። በጣም የሚያስደስትም የሚያሳዝንም አጋጣሚ ሲኖር ስሜቴን እቆጣጠራለሁ። እና ይሄ ጥያቄ ቢያልፈኝ እመርጣለሁ። ለእኔ ሁሉም ተጫዋቾች መልካም ናቸው። ከስብስብ አንፃር ግን ከ2005 እስከ 2007 የነበረውን ጊዮርጊስ በጣም እወደዋለሁ። ጥሩ ስብስብ ነበር ፤ ከታች የመጡ እነ ዮናታን ብርሀነ ፣ መስፍን ኪዳኔ ፣ ምንተስኖት አዳነ ፣ ታደለ መንገሻ ፣ ዘሪሁን ታደለ ፣ ኤልያስ ማሞ ጊዮርጊሳዊ መሰላሉን የጠበቁ ተጫዋቾችም የነበሩበትም ስለነበር በጣም እወደዋለው።

ሁሉም የቅዱስ ጊዮርጊስ ማልያ የለበሱ የኔ ምርጦች ናቸው እያልክ ነው። እስቲ ምርጡ አሰልጣኝስ ላንተ ማነው ?

አፌን ሞልቼ እናገራለሁ። ለኔ ምርጡ አሰልጣኝ ሚኬል ክሩገር ነው። አንዴ ልምምድ ሜዳ ላይ የለመድናቸውን ሦስት ድርድር ያላቸው (4-4-2/4-3-3) አሰላለፎችን ለምን እንደማይጠቀም ስጠይቀው ‘ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች የፊትነስ ደረጃቸው ዘጠና ደቂቃ የሚያጫወታቸው አይደለም። ባለሦስት ድርድር አሰላለፍ ከሆነ አንድ ተጫዋች በአማካይ 45 ስኴር ሜትር መሸፈን ይኖርበታል። አራት ከሆነ ግን ወደ 33 ትቀንሰዋለህ ተጫዋቹም ትንፋሸን እንዲቆጥብ ይረዳዋል’ አለኝ እና ‘አሁን ካሉት ተጫዋቾች ውስጥ በፊትነስ እና በፍጥነት የተሻለ የምትለው ማነው ?’ አለኝ። ‘አሉላ ግርማ’ አልኩት። አሉላን ጠራውና ከአንደኛው ጎል ጫፍ እስከሌላኛው ጎል ጫፍ አስሮጠው። ቀጥሎ ‘ኳስ እየገፋህ ሂድ’ አለው። ኳስ እየገፋ በ20 ወይ በ21 ሰኮንዶች ደረሰ። ‘ይሄ ማለት ዳንኤል አልቬስ የሚፈጅበት ሰዓት ነው’ አለኝ። ከዛ ‘ይዘህ ተመለስ’ አለው። ሲመለስ ደግሞ ከአንድ ደቂቃ በላይ ፈጀበት። ‘ይሄ ደግሞ ዓለም ላይ ያሉ ዝቅተኛ ተመላላሾች ፍጥነት ነው።’ ብሎ አስረዳኝ። ምንአልባት ቀርቤ ስላየሁትም የማየውም ነገር ጥሩ ስለነበር ይሆናል ክሩገር ለኔ ምርጡ አሰልጣኝ ነበር።

ታላቅ ወንድምህ የቡና ደጋፊ ነው። አንተ የቅዱስ ጊዮርጊስ ከወንድምህ ጋር ያለውን የክለብ አደጋገፍ እና ተቃርኖ ከቤተሰባዊ ትስስር ጋር አያይዘህ አጫውተኝ?    
ወንድሜ የቤቱ ታላቅ ነው። በእርግጥ አብረን አላደግንም። ምንአልባት አብረን አድገን ቢሆን ማናችንም የቤተሰቦቻችን ነፀብራቅ እንደመሆናችን እሱን ከማየት እሱ ወደሚወደው ክለብ ላዘነብል እችል ነበር። አብረን አለማደጋችን በራሴ መንገድ የምወደውን ክለብ አግኝቻለው። ከወንድሜ ጋር በጣም የምንቀራረብ በየጊዜው የምንገናኝ ከወንድምነትም ባሻገር ጓደኛሞችም ነን። እኛ ቤት ብዙ ነን ግን እኔ እና እሱ ልዩ ቅርበት ነው ያለን ፤ ልደታችን ራሱ አንድ ቀን ላይ ነው። የሚገርመው ግን በብዙ ፍላጎቶቻችን ብዙ ልዩነቶች አሉት። በአውሮፓ ሊጎች ውስጥ ራሱ በድጋፋችን ሁሉም ጋር የተለያየን ነን። ይሄን ነገር እወደዋለው ፤ እንደውም በጣም ነው ደስ የሚለኝ። እንጂ ሌላ ተቃርኖ የለንም።

የመጨረሻ ጥያቄዬ ላድርገው ከኮሮና ጋር ተያይዞ ውድድሮች ቆመዋል ደጋፊዎች ተለያይታችኋል። በየሳምንቱ በስታድየም ለማትገናኙ ደጋፊዎች የምታስተላልፈው መልዕክት አለ ?

ይሄ የዓለም ችግር ነው። ችግር አንተ ላይ ብቻ ሲሆን ይከብዳል። ችግር የጋራ ሲሆን ግን ችግርነቱ ባይቀርም ይቀላል። እኛ ላይ ብቻ የመጣ ነገር አይደለም። በፈጣሪዬ ዕምነት አለኝ ፤ የተሻለ ነገ እንደሚመጣ። ናፍቆታችንን እና የዓይን ርሀባችንን እናስታግሳለን። ይህንን ደግሞ የምለው ለእኛ ደጋፊዎች ብቻ አይደለም ፤ ለሁሉም የእግርኳሱ ደጋፊ ነው። እግርኳሱ አካባቢ ላሉ ዳኞች ፣ አሰልጣኞች ጋዜጠኞች ለሁሉም በእግርኳሱ አነሰም በዛም አሻራ ላላቸው በሙሉ ነው። ዓለም ከዚህ በላይ ተፈትናም ታውቃለች እና እንደተለያየን ከነሙሉ ነገራችን እንድንገናኝ የተሻለ ጊዜ እስኪመጣ ባላችሁበት ቆዩ ነው የምለው። ለሀገራችንም ሠላም እመኛለሁ።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ