ረጅም ዓመት የዘለቀ የኢንተርናሽናል ዳኝነት ጉዞ – ክንዴ ሙሴ በዳኞች ገፅ

ሃያ ሰባት ዓመት በዘለቀው የዳኝነት ህይወቱ እስካሁን ለተከታታይ 14 ዓመታት ሳይወጣ ሳይገባ በኢንተርናሽናል ዳኝነት አቋሙ ሳይዋዥቅ ሀገሩን በመወከል እያገለገለ ይገኛል። የዳኝነት ብቃቱ ብዙዎች የሚመሰክሩለት ረዳት ዳኛ ክንዴ ሙሴ የዛሬው የዳኞች ገፅ እንግዳችን ነው።

ከመንግሥት ለውጥ በኃላ ወደ ዳኝነቱ ጎራ ተቀላቅሏል። የአባቱ እግርኳስ ተጫዋች መሆን እርሱን እያደር ወደ እግርኳሱ እንዲገባ መነሻ አድርጎት ከመጫወቱ ይልቅ ወደ ዳኝነቱ እንዲገባ አድርጎታል። ከሀገር ውስጥ ትልልቅ ጨዋታዎች አንስቶ ከሀገር ውጭ በርካታ ትላልቅ ውድድሮችን በብቃት ዳኝቷል። በተለይ የእርሱ ልዮ መገለጫ የሆነበት ከ1998 ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለተከታታይ አንድም ጊዜ ወጥቶ ሳይገባ ለተከታታይ አስራ አራት ዓመት አሁንም ጨምሮ በኢንተርናሽና ረዳት ዳኝነት እያገለገለ መሆኑ ለብዙዎች የፅናት፣ የጥንካሬ ተምሳሌት እንዲሆን አድርጎታል።

ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ክንዴ ሙሴ በዛሬው የዳኞች ገፅ አምዳችን ተነግሮ ከማያልቀው የዳኝነት ህይወቱ በጥቂቱ ልናካፍላቹ ወደድን። መልካም ንባብ

ለዳኝነት ህይወትህ መነሻ የሆነህን፣ ትውልድ እና እድገትህን አጫውተኝ ?

ትውልዴም እድገቴም ሀዋሳ ከተማ ነው። አባቴ እግርኳስን ይጫወት ስለነበረ ወደ ሜዳ ይዞኝ ይገባ ነበር። እንዲያውም አንድ ቀን ከአባቴ ጋር አዲስ አበባ ስንመጣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ሲጫወቱ ስታዲየም ገብቼ ጨዋታ ተመልክቻለው በዚሁ ጨዋታ ላይ ዳኞች የሚወስኑት ውሳኔ ደስ ይለኝ ነበር። በወቅቱ ማስተር ተሾመ፣ ቸርነት ከደብረዘይት እየመጡ ነበር የሚያጫውቱት። የሚሰጡት ውሳኔ ቁርጥ ቁርጥ ያለ ደስ የሚል ውሳኔ ነበር። ይሄንን ሳይ እኔም አንድ ቀን በዚህ ሜዳ ላይ ማጫወት አለብኝ የሚል ፍላጎት አደረብኝ። በዚህ ተነሳስቼ የዳኝነት ኮርሱን በሀዋሳ ለመውሰድ ችያለው።

ኮርሱን መቼ ወሰድክ? አንተ በነበርክበት ክልል ብዙ ጨዋታዎችን የማጫወት ዕድል አግኝተሀል? ብዙ ጊዜ በአዲስ አበባ የሚገኙ ዳኞች ብዙ የማጫወት ዕድሎች ማግኘታቸው የሰጣቸው ጠቀሜታ እንዳለ ይናገራሉ። በአንተ በኩልስ ?

የመጀመርያውን ስልጠና ከመንግስት ለውጥ በኃላ በ1985 መውሰድ ችያለው። ዳኝነት በድሮ ዘመን እድገቱ በጣም ውስን ነበር። አዲስ አበባ ሆኖ ማጫወት ምንድነው የነበረው ጥቅም ትላልቅ የሚባሉ ክፍለ ሀገሮች አሉ ሸዋ፣ ሀረርጌ፣ አስመራ በነዚህ ውስጥ የነበሩ ቡድኖች በጣም ጠንካራ ስለነበሩ እነዚህን በማጫወት ነበር ኢንተርናሽናል ዳኛ ይባሉ የነበሩት። እኛ ደግሞ ኮርሱን የወሰድነው ከለውጡ በኃላ ስለሆነ በዚህ ጊዜ ደግሞ የእግርኳስ እድገቱ እየጨመረ መጥቷል። በሀዋሳ ላይም በርከት ያሉ ክለቦች እየተፈጠሩ ብዙ ውድድሮችን እያገኘን መጥተናል። እንዲሁም የሀዋሳ ክለቦች አዲስ አበባ መጥተው የአዲስ አበባ ክለቦችን መፎካከር ጀመሩ። በዚህ ምክንያት ለዳኞችም ትኩረት እየተሰጠ እኛም የማጫወት እድሉን እያገኘን መጣን።

ወደ ፌደራል ዳኝነቱ እንዴት ገባህ?

1985 መምርያ ሁለት ወስጄ ወድያውኑ ማጫወት ጀመርኩ፤ ኳስም እጫወት ስለነበረ ብዙም ጊዜ አልወሰደብኝም። 1987 መምርያ ሁለትን ወስጄ የተለያዩ ጨዋታዎችን ለአራት ዓመት በድምሩ በመምርያ ደረጃ ስድስት ዓመት ሳገለግል ቆይቼ በ1991 ፌደራል ዳኛ ሆንኩኝ። በእነ አቶ ፀሀዬ የዳኞች ፕሮጀክት ተብሎ ሀምሳ አራት ዳኞች ለስልጠና እና የፐረሮጀክት ውድድር እንድናጫውት አዳማ ከተማ ገባን። በዚህን ወቅት የማጫውተው በዋና ዳኘረነት ነበር። ሆኖም ዓለም አሰፋ አንተ መሐል ስታጫውት ጥሩ ነህ ሆኖም ከሰውነትህ ቁመና አንፃር ረዳት ዳኛ ብትሆን የተሻለ ነው። ብሎ መክሮኝ ይህን ተቀብዬ በዛን ወቅት ከሀምሳ ምናምን ዳኞች ውስጥ ጥሩ የነበርነውን አስራ አምስት ዳኞችወደ ፕሪሚየር ሊግ እንድናጫውት ተደርጎ በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ የመጀመርያ ጨዋታዬን በረዳት ዳኝነት በአዲስ አበባ ስታዲየም በ1994 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሙገር ሲሚንቶ በማጫወት ጀመርኩ።

በዚህ የጀመረው የዳኝነት ህይወትህ እስከ ኢንተርናሽናል ዳኝነት መዝለቅ ችለሀል። እስቲ የኢንተርናሽናል ዳኝነትን መቼ ጀመርክ ?

እንግዲህ ለስድስት ዓመት በፌዴራል ረዳት ዳኝነት በክልሌ ደቡብ ደረጃ በዋና ዳኝነት፣ በኢትዮጵያ ደግሞ በረዳት ዳኝነት ስሰራ ቆይቼ በ1998 ኢንተርናሽናል ዳኝ መሆን ቻልኩ። ይህው እስካሁን ያለ ማቋረጥ ሳልወጣ ሳልገባ ለአስራ አራት ዓመት ያህል በዚሁ በኢንተርናሽናል ዳኝነት ባጅ አለሁኝ። በዚህም እኔ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ዳኛ ነኝ። ረጅም ዓመት በማገልገል።

ይህ ትልቅ ስኬት ነው። አይደለም ኢትዮጵያ ውስጥ በአፍሪካም ጭምር ያለማቋረጥ በተከታታይ ረጅም ዓመት ኢንተርናሽናል ሆኖ መዝለቅ የቻለ ዳኛን ማግኘት የማይታሰብ ነው? 

አዎ አይቻልም! አንዳንዴ ይገርምሀል ላጫውት አንዳንድ አፍሪካ ሀገራት ስሄድ ከእኔ ጋር አብረው ያጫውቱ የነበሩ የኔ ዘመን ዳኞች። አሁን እነርሱ ዳኘኝነትን አቁመው የኔ ኮሚሽነር ሆነው ሲያገኙኝ አንተ እስካሁን አለህ? እውነት የአካል ብቃትህ ፊት ሆነህ ነው የምታጫውተው ብለው ይጠይቁኛል። እኔ ደግሞ ሜዳ ላይ እዩኝ ብቁ ካልሆንኩ የዛን ጊዜ ትፈርዳላቹ እላቸዋለው። እነርሱም በዚህ አቋሜ በጣም ነው የሚገረሙት። በአሁን ሰዓት አብዛኛዎቹ የጨዋታ ታዛቢዎች ጓደኞቺ ናቸው።

በጣም ይገርማል! በየጊዜው ካፍ እና ፊፋ የሚያወጧቸውን የተሻሻሉ ጠንካራ ፈተናዎችን አሉ በዚህም ብዙዎች ከጊዜ በኋላ ከኢንተርናሽናል ዳኝነቱ ይወጣሉ። አንተ የአካል ብቃትህን አዘጋጅተህ በጥንካሬ ረጅም ዓመት የመዝለቅህ ሚስጢር ምንድነው ?

ስለ እውነቱ ከሆነ በመጀመርያ ደረጃ እንደዚህ ላቆየኝ የቻልኩት ፍላጎት ስላለኝ ነው። ፍላጎት ካለ ለዛነገር ክብር ትሰጣለህ። ሙያውን ከወደድከው ክብር ትሰጣለህ፣ ሙያህ የሚፈልገውን ነገር ብቻ ታደርጋለህ። እኔ የዳኝነት ሙያው ምድነው የሚፈልገው ብዬ መጀመርያ እርሱ ላይ ነው የማስቀድመው። የአካል ብቃት ፊት ለመሆን ልምምድ መስራት አለብኝ። በየጊዜው የሚወጡ የተሻሻሉ ህጎችን ለማወቅ ማንበብ አለብኝ። ከዚህ ውጭ ደግሞ የዳኝነት ሙያ የማይፈልጋቸውን ነገሮች አላደርግም፣ እርቃለው። የፈለገ ቢሆን መብላት ካለብኝ የሚገባውን እበላለው ከዛ በላይ የሆነውን አልበላም። ለምን? ዳኝነቴን ከወደድኩ ሰውነቴን መጠበቅ አለብኝ። አንተ ስለጋበዝከኝ ብቻ የፈለኩትን አልበላም። ምክንያቱም የሚጠቅመኝን እበላለው፣ እጠጣለው ለምን? ከሙያው ላለመውጣት ስለምፈልግ። ደግሞ የዳኝነት ሙያ ለኔ ብዙ ነገር አድርጎልኛል። እውነቴን ነው የምነግርህ አስቀድሜ የመጣሁት ሙያውን ወድጄ ነው። ሙያውን አስቀድሜ በመምጣቴ ሙያው ለኔ ከፍሎኛል። በሀገር ውስጥ ብር አንስቶ በዶላር ከፍሎኛል፣ በዩሮ ከፍሎኛል። እኔ ሙያው በዶላር፣ በዮሮ ከከፈለኝ ለምድነው የምልከሰከሰው ሙያው የምፈልገውን ካደረገልኝ እኔም ሙያው የማይፈልገውን ነገር ማድረግ የለብኝም። ያ ነው እስከ ዛሬ ድረስ እዚህ ደረጃ እንድደርስ ያበቃኝ። የፈለገ ነገር ቢሆን በሳንቲም አልታለልም። ሳንቲም የወሰዱ ሰዎች ተሰናክለው እንዴት እንደቀሩ አውቃለው። እኔ የማወራለህ ስለ ኢትዮጵያውያን ዳኞች አይደለም። ስለ አፍሪካውያን ዳኞች ነው። ሁሌም ለሰው ብዬ አይደለም። ልምምዴን ጠንክሬ በመስራቴ ፣ እራሴን በመጠበቄ እዚህ ደርሻለው።

እስቲ በዚህ ሁሉ የዳኝነት ቆይታህ የኮከብ ምስጉን ዳኝነት ክብርን ለምን ያህል ጊዜ አገኘህ?

ሦስት ጊዜ የምስጉን ኮከብ ረዳት ዳኝነትን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አግኝቻለው። በ1998 የመጀመርያውን ሳገኝ የሚገርምህ አንድ ሰው ምርጥ ረዳት ዳኛ ሆኖ መመረጥ ሲገባው ስምንት ረዳት ዳኞች ኮከብ ተብለን ተመረጥን። ይህን ኮከብ ብሎ ለመቀበል ይቸግረኛል። ሁለተኛ 2002 ከባምላክ ጋር እና 2008 ደግሞ ከኃይለየሱስ ባዘዘው ጋር ኮከብ ረዳት ዳኛ ሆኜ ተመርጫለው። በጣም የሚገርም አጋጣሚ በሦስቱም የኮከብነት ምርጫ ስሸለም እኔ ከሀገር ውጭ ጨዋታ የነበረኝ በመሆኑ ሽልማቱን በአካል አልተቀበልኩም።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ሆነህ መጀመርያ ያጫወትከውን ጨዋታ ታስታውሰዋለህ ?

አጋጣሚ ሆኖ ኢንተርናሽናል እንደ ሆንኩ በሀገሬ አራተኛ ዳኛ ሆኜ የመጀመርያ ጨዋታ አጫውቼ ብዙም ሳልቆይ የሱዳኑ አል ሂላል ኡምዱርማን እና ዛማሊክ ለአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ አራት ውስጥ ለመግባት ወሳኝ ጨዋታ ነበራቸው። የሱዳን እግርኳስ አመራሮች አራቱም የኢትዮጵያ ዳኞች ያጫውቱን ብለው ለካፍ ጥያቄ ያቀርባሉ። ግብፆችም ይሄን ሀሳብ ተቀበሉ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን ዳኞች በብቃት የሚታሙ ስላልሆነ። በዚህም ምክንያት ለኢትዮጵያ እድሉ ተሰጠ። የዳኞች ኮሚቴም ጨዋታው ከባድ ስለሆነ ልምድ ያላቸውን ዳኞች ይመደቡ ብሎ አራት ዳኞች ይመድባል። እንዳጋጣሚ ሆኖ በዛን ወቅት የዳኞች ኮሚቴ የወሰነውን ምደባ ፕሬዝደንቱ እና ሥራ አስፈፃሚው ነበር የሚያፀድቁት። የተመደቡትን ዳኞች ይመለከቱ እና እኔ የሰማሁትን ነው የምነግርህ ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ከሥራ አስፈፃሚዎች ጋር ይሆኑና ለምድነው አዳዲስ ዳኞች የማይመደቡት? መቼ ነው ልምድ የሚያገኙት? ልምድ ያላቸውን ብቻ የምትመድቡ ብለው ጠይቀው ከሦስቱ አንዱን አዲስ ጀማሪ ዳኛ አድርጋችሁ መድቡ ይሉና መመሪያ ይሰጣሉ። ኃይለራጉኤል እና እኔ ጋር ይደወላል። ኃይለራጉኤል ሲጠየቅ ፓስፖርት አላወጣም። እኔ ደግሞ ስለነበረኝ በአስቸኳይ ፓስፖርቴን አቅርቤ ከሰላሙ እና ከልዑልሰገድ ጋር በመሆን ይህን ትልቅ ጨዋታ ካይሮ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ አጫወትኩ።

ሀገርህ ወክለህ ብዙ ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን ባለፉት አስራ አራት ዓመታት አጫውተሀል እስቲ በትልልቅ መድረኮች ያጫወትከውን ንገረኝ ?

የአፍሪካ፣ የዓለም፣ የኦሎምፒክ ማጣርያ፣ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ፣ የኮንፌዴሬሽን ፣ ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫን ሞሮኮ ላይ፣ ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫን ሴኔጋል ላይ አጫውቻለወ። በደቡብ አፍሪካ ያዘጋጀችውን የአፍሪካ ዋንጫን ለማጫወት ተመርጬ እድሉን አግኝቼ ሄጄ ነበር። ሆኖም ሁሉንም ነገር አሟልቼ ዳኛ ቅነሳ ሲካሄድ እኔ ልቀነስ ችያለው። አንዳንዴ ሰው ሳይኖርህ ሲቀር ያገኘህውን ዕድለወ ታጣለህ። የፍፃሜ ጨዋታም ያለ መታደል ሆኖ
የቱኒዚያው ኤክስፕሪያስ ከአንድ ቡድን ጋር የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ እንድናጫውት ተመድበን ባምላክ እግሩን ታሞ ስለነበር እኔ ተመስገን ብቻ መሔድ ስለማንችል በምትኩ የሌላ ሀገር ዳኞች ተመደቡ። በጣም የሚገርም ያንን የፍፃሜ ጨዋታ አጫውተን ቢሆን ኖሮ የዓለም የክለቦች ውድድር ላይ የመመደብ እድላችን ሰፊ ነበር። ፈጣሪ አልፈቀደም

በዳኝነት ዘመንህ ካጋጠሙህ የማትረሳቸው ገጠመኜችህ መሀከል የተወሰነውን አጫውተኝ?

ብዙ ገጠመኞች ይኖራሉ በህይወቴ የማረሳው ግን ሁለት አሉ። አንደኛው ዳኝነት በጀመርኩ በዓመቱ በሲዳማ የወረዳዎች ጨዋታ ላይ አንደኛው ቡድን ከጨዋታ ውጭ እንቅስቃሴን በደንብ ያውቃል ጠብቆ ተጫውቶ ጎል ያገባል። አንደኛው ቡድን ደግሞ ከባለ ጋራው ቡድን በተቃራኒው ምንም የጨዋታ አቋቋም አያቅም ። በዚህ ምክንያት በኔ በኩል የጨዋታ አቋቋም የማያቀው ቡድን ኦፍ ሳይድ ሲገባ አነሳበታለው፣ ብድግ አደርጋለው። እነዛ የሚያቁት ቡድኖች በኔ በኩል ሲሆኑ ደግሞ አልፈው ጎል ያገባሉ። እነዛ ደግሞ ወደ እኔ ሲመጡ እይዛለው። መጨረሻ ላይ እንዴት እነርሱን ለቀህ እኛን ትይዛለህ ብለው ደጋፊዎች ተገልብጠው ሜዳ ገቡ። ከዚህ በኃላ ምን ልበልህ ተቀባበሉኝ ከሜዳ ጀምረው የመቱኝ እስከ ሆቴል ድረስ በጉማሬ እየገረፉ አደረሱኝ (እየሳቀ) በንጋታው ጠዋት እንደገና ልዮ ሀይል መጥቶ ጨዋታው እንዲደገም ተርጎ አጫውት አሉኝ። አላጫውትም ሞቼ እገኛለው ብዬ ያው ወጣትነት ስሜታዊነት፣ እልሁ አለ በስንት ልመና ኮሚቴው አጫውት ብሎኝ በመጨረሻ አልቅሼ፣ አልቅሼ አይኔ አብጦ አጫወትኩኝ። በህይወቴ የማረሳው አጋጣሚ ነው። ከሜዳ እስከ ሆቴል የተገረፍኩበትን።

ሌላው እኔ ባዓምላክ፣ ተመስገን እና ሀይለየሱስ ሆነን ካይሮ አሌክሳንድርያ እንድናጫውት ተነግሮን ነበር። በዱባይ ወደ ካይሮ ልንሄድ። ሆኖም ፕሮግራሙን ቀይረው በኢትዮጵያ አየር መንገድ በምሽት በረራ ወደ ካይሮ እንደሚኬድ አላወቅንም። በተሳሳተ በረራ ወደ ዱባይ ብቻ የሚሄድ አውሮፕላን ውስጥ ገባን በኋላ ኮሚሽነሩ ደውለው የት ናቹ ሲሉን? ወደ ዱባይ ለመሄድ አውሮፕላን ውስጥ ገብተናል ስንል ኧረ በረራው ተቀይሯል ውረዱ አሉን። እንዳጋጣሚ አውሮፕላኑ እያኮበኮበ ስለነበር ሳይነሳ አውርዱን ብንል ብንጮህ ፣ብንጠይቅ አይሆንም አንዴ ተሳፋሪ ቆጥረን ተረክበናል አውሮፕላኑ ደግሞ እያኮበኮበ ነው አትወርዱም አሉን። በመጨረሻም በተሳሳተ በራራ ዱባይ ገባን። ዱባይ ሆነን እየተፃፃፍን እንደ አጋጣሚ ብር ይዘን ስለነበር ሌላ ትኬት ለመቁረጥ የዱባይ ኤርፖርት የሀገር ነው (በጣም ሰፊ ነው) በቀሰ እላይ እታች ብለን ተመላልሰን በዓምላክ በጣም ደክሞት ነበር። በአሰንሰሩ (በሊፍት) በደረጃው ማለት ነው ወደ ታች እየወረድን እያለ ባዓምላክ ወደ ላይ ወደ እኔ ዞሮ ያወራል። አሳንሰሩ ወደ ታች ማውረጃውን ጨርሶ ወደ ውስጥ እየገባ ባዓምላክ አላቀም ተንሸራቶ ይወድቃል። እኛ ደግሞ ተንከባለን እንደ ሻንጣ ሦስታችንም እላዮ ላይ ተደራርበን የወደቅንበት ጊዜ አይረሳኝም። (እየሳቀ)



ከዚህ በኃላ ብዙ የመስራት አቅም እንዳለህ ቢታመንም እስካሁን ባለህ የዳኝነት ህይወትህ ብዙው ምሳሌ መሆን ትችላለህ። እስቲ ለዚህ ዘመን ዳኞች ምን መልዕክት ታስተላልፋለህ ?

እኔ ማስተላለፍ የምፈልገው ነገር በመጀመርያ ሙያውን አይቶ ወደ ዳኝነቱ የገባ ትልቅ ደረጃ ይደርሳል። አሁን የድሮ ዳኛ እና የአሁኑ ዳኛ ልዮነቱ ምድነው። የድሮው ሳንቲም የለም ፍቅሩ አለ። የአሁኑ ደግሞ ሳንቲም አለ። በዚህ ዘመን ያሉ ዳኞች ብዙ ርቀት ሳይጓዙ የሚቆሙት ሳንቲሙን አስበው ስለሚመጡ ነው። ሳንቲሚ በራሱ ሰዓት በራሱ ጊዜ ይመጣልሀል። ኢንተርናሽናል ደረጃ ከደረስክ ሳንቲሙ ይመጣል ማንም አይከለክልህም። ራሱ በርህን አንኳክቶ ይመጣል። ስለዚህ ሳንቲሙን እናገኛለን ብለው ሳይሆን በዳኝነት ሙያው ትልቅ ደረጃ እደርሳለው ብሎ መምጣት አለባቸው። በተጨማሪም ዳኝነት የሚፈልጋቸውን ነገሮች የማድረግ፣ ሙያው ከማይፈልጋቸው ነገሮች መራቅ አለባቸው። ልምምዳቸውን በአግባቡ መስራት ፣ በደንብ ህጉን ማንበብ እንዳለባቸው መልዕክቴን አስተላልፋለው።

የቤተሰብ ህይወት?

ባለ ትዳር እና የሁለት ወንድ እና ሴት ልጆች አባት ነኝ። በኑሮዬም በሁሉም ነገር ደስተኛ ነኝ።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ