በተደጋጋሚ እንደሚነገረው እግር ኳስ የንክኪ ስፖርት ነው። ተጫዋቾች እርስ በእርሳቸው ከሚያደርጉት ንክኪ በተጨማሪ ከመሬት፣ ከኳስ እና በግብ ጠባቂዎች ምሳሌ ደግሞ ከግቡ ቋሚ ጋር ሊጋጩ የሚችሉበት ዕድል ከፍ ያለ ነው። ማንኛውም ፊት ላይ የሚደርስ ጉዳት ከፍተኛ ችግር የማስከተል ዕድሉ ላቅ ያለ ስለሆነ በጥንቃቄ ሊመረመር እና ሊታከም ይገባል።
በአብዛኛው ጊዜ የጭንቅላት ግጭት እና ክርን ከጭንቅላት ጋር የሚኖረው መላተም የፊት ጉዳት መንስኤ ሲሆኑ ይታያል። ለሚደረገው ህክምና ጉዳቱ የተከሰተበት መንገድን እና የግጭቱን ፍጥነት (velocity) ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው ።
የፊት ጉዳቶችን ሜዳ ላይ ማወቅ እና መመርመር ከባድ ስለሆነ የተሟላ የራዲዮሎጂ ስፔሻሊቲ ወዳለበት ሆስፒታል መላክ አስፈላጊ ነው። ይህን ጉዳት የሚያክመው ባለሙያ ተያይዘው ሊመጡ የሚችሉ ጉዳቶችን በማወቅ እና በመጠርጠር ስራውን ማከናወን ይኖርበታል።
ማንኛውም የፊት ጉዳት ሲታከም መጀመሪያ የሚሰራው ስራ ‘ABC of life’ የሚባሉትን የህይወት አድን እርምጃዎች መተግበር ነው። Airway (የአየር ዝውውር) – Breathing (አተነፋፈስ) – Circulation (የደም ዝውውር) ላይ ያሉ ለከፍተኛ ጉዳት ሊዳርጉ የሚችሉ እክሎች መኖራቸው ከተጣራ በኋላ የተጫዋቹ ንቃተ ህሊና የሚታይ ይሆናል። አብዛኛውን ጊዜ ፊት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ለህይወት አስጊ የሚባሉ አይደሉም።
የፊት ጉዳት አይነቶች
የቆዳ መላላጥ (Abrasions)
ይህ ጉዳት ሁለቱን የቆዳ ክፍሎች (Dermis and Epidermis) የሚያጠቃ ነው። የሚያጋጥመውም ጠንኳራ ከሆነ ነገር ጋር ፊት ሲፋተግ እና ቆዳ ሲላጥ ነው። የመጀመሪያ የማከሙ ስርአት ትኩረት የሚያደርገው ኢንፌክሽን እንዳይፈጠር በመከላከሉ ላይ ነው። ቁስሉ እንዲድን ይህንም ተከትሎ ዘለቄታ ያለው ጠባሳ ቆዳ ላይ እንዳይፈጠር መከላከል አስፈላጊ ነው።
የቆዳ መበለዝ (Contusion)
ከግጭት በኋላ የሚኖር ከላይ የሚፈጠር (blunt trauma) አደጋ ነው ። ተጫዋቹ ሊያሳያቸው የሚችል ዋና ምልክቶች ህመም እና ደም መቋጠር ካለ ደግሞ ወደ ሰማያዊነት የሚለወጥ የቆዳ ቀለም ነው። ይህን ለማከም ጉዳት የደረሰበት ቦታ ላይ በረዶ መያዝ (ice packs) አስፈላጊ ነው። እየታረፈ ለ24-48 ሰዐት ያህል በረዶ መደረግ ይኖርበታል።
የደም መቋጠር (Hematoma)
ይህ በጡንቻዎች እና በተለያዩ የሰውነት አካላት (spaces) ላይ የሚኖር ደም መቋጠር ነው። ሰማያዊ ወይንም ጠቆር ያለ እብጠትን ጉዳቱ የደረሰበት ቦታ ላይ ማስተዋል ይቻላል።
ደም መቋጠር የተስተዋለው በአፍንጫ ወይንም ጆሮ ጫፍ ላይ ከሆነ ተጫዋቹ ጨዋታውን እንዲቀጥል የሚፈቀድለት ቢሆንም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በድጋሚ የሚታይ ይሆናል።
የቆዳ መሰንጠቅ (Laceration)
ይህ ጉዳት ክፍት የሆነና ቆዳን የሚያጋልጥ ነው ። ከላይ (Superficial) አልያም ጥልቅ (Deep) የሆኑ የቆዳ መሰንጠቅ ጉዳቶች አሉ። ፊት ላይ ከሚኖሩ ብዙ የሚባሉ የደም ስሮች ምክንያት መድማት የተለመደ ምልክት ነው። ሰለዚህ ደሙን ለማቆም በቀጥታ ቁስሉን ተጭኖ መያዝ አስፈላጊ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ፊት ላይ የሚኖረው የቆዳ መሰንጠቅ ለማስተካከል መስፋት ሊያስፈልግ ይችላል ።
ከላይ ከተዘረዘሩት በእግር ኳስ ጨዋታ ወቅት ፊት ላይ ከሚደርሱ ጉዳቶች ተዘውትሮ የሚታየው የአፍንጫ መድማት ነው።
አፍንጫ በሚደማበት ወቅት ተጭኖ በመዝጋት እና ለተወሰነ ደቂቃ ይዞ በመቆየት መቆጣጠር ይቻላል። መድማቱ እንደቆመም ተጫዋቹ ወደ ጨዋታ ሜዳ እንዲመለስ የሚፈቀድለት ይሆናል ማለት ነው። መድማቱ የሚቀጥል ከሆነ በፋሻ ለማቆም ጥረት መደረግ ይኖርበታል።
በቀጣይ ፅሁፋችን በፊት ላይ የሚደርሱ የአጥንት ስብራቶችን ይዘን የምንቀርብ ይሆናል።
ለዚህ ፅሁፍ Football Emergency Medicine Manual 2nd edition 2015 የተባለውን መጽሐፍ በዋና ግብዓትነት ተጠቅመናል።