የሴቶች ገፅ | መሪዋ ቱቱ በላይ

ክለብ ሳትገባ የሀገሯን መለያ መልበስ ችላለች። ከደሴ ከተማ በተነሳው የተጫዋችነት ህይወቷ ወደ ሰባት ለሚጠጉ ክለቦች ተጫውታለች። በኢትዮጵያ የሴቶች እግርኳስ እየተሻሻለ ለመምጣቱ የሷም እንቅስቃሴ ወሳኝነት ነበረው፡፡ ሜዳ ላይ መሪ ናት ፤ የአምበልነት ሚናም ተሰጥቷት በአግባቡ ተወጥተዋለች። የዛሬው የሴቶች ገፅ እንግዳችን ቱቱ በላይ፡፡

በኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ ታሪክን ካወሳን እሷን ሳንጠራ ማለፍ ከባድ እንደሆነ የነበራት ታሪክ ማሳያ ነው፡፡ የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋቿ ቱቱ በላይ ትውልድ እና ዕድገቷ በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ብዙም ክለቦች ።ባልተስፋፉበት በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ በትውልድ አካባቢዋ ከወንዶች ጋር ኳስ በመጫወት ስፖርቱን ጀምራለች። የሴቶች እግርኳስ ፕሮጀክት በሀገር አቀፍ ደረጃ መቋቋሙ ግን ለሷም ሆነ ለጓደኟቿ የተጫዋችነት ህይወት መንገድ ከፍቶላቸዋል፡፡

“ከወንዶች ጋር በምጫወትበት ሰዓት ነበር የሴቶች ፕሮጀክት የመጣው። በክልል ውድድር በሴቶች እንደሚኖር ተለጠፈ። እኔም ከእናቴ ጋር ሄጄ ተመዘገብኩ። እንደ ፕሮጀክት ተብሎ ያዙን። ደሴን ወክለን በአማራ ክልል ውድድር ላይ ሁለተኛ ወጣን። በዛው ዓመት ለአማራ ክልል ተመረጥኩኝ። ወንጂ ላይ አማራን ወክለን አራተኛ ወጣን። በተመሳሳይ ዓመት 1994-95 ብሔራዊ ቡድን ውድድር ነበር። እኔ ክለብ የለኝም። ውድድሩን ስጨርስ ወደ ደሴ ነው የምመለሰው። በዓመት ሁለት ጊዜ ነው ውድድር የማደርገው ፤ ደሴን ወክዬ ወይም አማራ ክልልን ማለት ነው። በወንጂው ውድድር ብሔራዊ ቡድን መመረጤን በአጋጣሚ ሰማሁ። የዋንጫ ጨዋታ ከመድረሱ ቀደም ብሎ አሰልጣኞች እና የቡድን አምበሎች ስብሰባ ነበር። በሰዓቱ የአሁኑ የሀድያ ሆሳዕና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ‘አሁን ለምሳሌ የአማራ ስድስት ቁጥርን ማየት እንችላለን’ ሲል ያን ሰዓት ብሔራዊ ቡድን መመረጤን አወቅኩኝ። እሱም ስለ ብሔራዊ ቡድን ነበር የሚያወራው። ለሌላ ሰው አልተነገረም ፤ እኔም በንግግሩ ሲያንፀባርቅ ነው ያወቅኩት። ወደ ደሴ ከተመለስኩኝ በኃላ የራሴን ዝግጅት ማድረግ ጀመርኩኝ። በክልሉ አማካኝነት ተደውሎልኝም ወደ ብሔራዊ ቡድን ገባሁ።” በማለት እናቷ እጇን ይዛ ወደ ፕሮጀክት ካስገባቻት ጊዜ አንስታ ያለ ክለብ ለመጀመሪያ ጊዜ ለብሔራዊ ቡድን የተመረጠችበትን ጊዜ ታነሳለች።

በአሰልጣኝ በለጥሽ ገብረማርያም ፣ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ፣ በሙገር ሲሚንቶው ማስተር አዳነ የተመራው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ስለነበራት ቆይታም እንዲህ ታወሳለች። “ለደሴም ሆነ ለአማራ ክልል ስጫወት ብሔራዊ ቡድንን አስቤ አልነበረም። እንዲህ ዓይነት ነገርንም ሰምቼ አላውቅም ነበር። ያው እኔ የሴቶች እግር ኳስ ስለተባለ ነው እንጂ ሴቶችም ጋር ልምምድ ሰርቼ እንደገና ተመልሼ ከወንዶች ጋር ነው የመጫወተው። ‘ብሔራዊ ቡድን ተመርጫለሁ’ ብዬ ለማንም ሰው አላወራሁም። ግን ሌሎቹ አዲስ አበባ ያሉት ክለቦች ስለነበሯቸው ከእነሱ ላለማነስ መዘጋጀት ነበረብኝ። ተመርጬ ከሄድኩኝ በኃላ የማልረሳቸው ጊዜያቶችን አሳልፌያለሁ። በዛ ላይም ውጤታማ ነን ብዬ ነበር የማስበው። የምንወዳደራቸው ሀገሮች የእግርኳስ ደረጃ ትልቅ ነው። እኛ ደግሞ እንደጀማሪ አሰልጣኞች የሚሰጡን ሞራል ከዕድሜያችን በላይ ነበር። ከእነሱ ጋር በአካል ብቃት አንገናኝም። በዕድሜም የተወሰነ ልዩነት ነበር። አሰልጣኞቻችን እንደምንችል እየነገሩን ነበር አዕምሯችንን የሚቀርፁን። የመጀመሪያችንም ስለነበር እንደልምድም ሆኖ ብዙም ውጤት አልነበረንም። በሁለኛው ደቡብ አፍሪካ ላይ በነበረው ውድድር ግን የከዋክብት ስብስብ የተባለበት ነበር።”

አማካይዋ ኢትዮጵያ ሁለተኛ ተሳትፎዋ በነበረው የደቡብ አፍሪካው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ እስከ መጨረሻው ተጉዛ በጋና በመለያ ምት 8-5 ተሸንፋ አራተኛ ደረጃን ይዛ ስታጠናቅቅ የታሪካዊው ስብስብ አባል ከመሆን ባለፈ አስደናቂ አቋሟንም ስታሳይ ነበር። ወሳኝ የሆኑ ግቦችን በማስቆጠሩ ረገድም ለሀገሯ ትልቅ አስተዋጽኦን አበርክታለች። በሰዓቱ የአፍሪካ ሚዲያዎች ከብርቱካን ገብረክርስቶስ ጋር በነበራት ድንቅ የመሀል ሜዳ ጥምረት ተገርመው በተደጋጋሚ ስሟን ሲጠሩም ተስተውሏል፡፡

ከክለብ ህይወት ቀድማ ሀገሯን ለማገልገል ዕድሉን ያገኘችው ቱቱ ለብሔራዊ ቡድን ከተጫወተች እና ውድድር ካለቀ በኃላ ዳግም ወደ ትውልድ ሀገሯ ተመልሳ 1996 ክረምት ድረስ ከቆየች በኃላ ከጊዜ ወደ ጊዜ አዲስ አበባ ውስጥ ክለቦች እየተበራከቱ ሲመጡ እሷም በአንድ ክለብ ታቅፎ የመጫወት ህልሟ ዕውን ሆነላት። በዚህም ለብዙ ሴት እግርኳስ ተጫዋቾች መሠረት የሆነው የአለባቸው ተካ (አለቤ ሾው) ክለብን 1997 ላይ ለመቀላቀል በቃች። “ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ እዚህ ከማሊ ጋር እየተጫወትን ነው አለቤ ያየን። በቁጥር ወደ አምስት እንሆናለን። ‘እነዚህ ልጆች እፈልጋቸዋለሁ ፣ ትምህርትም አስምራቸዋለሁ ፣ ቤትም እከራይላችዋለው’ ብሎ በለጥሽን አወራት። ይህን ስትነግረን ከቤተሰብ ጋር ተነጋገርን እና አለቤ ሾው ጋር ገባን። አለቤ ሾው ጋር የነበረው የኳስ ህይወቴም በጣም ደስ የሚል ነበር። በመሀል ግን የእሱ ህይወት መጥፋት በጊዜው በጣም ረብሾን ነበር። ዛሬ ላይ ዕውቅና እንዲኖረኝ እና ወደ ተለያዩ ክለቦች እንዳመራ ያደረገኝ እሱ ነው። በዚህ አጋጣሚም ማመስገን እፈልጋለሁ።”

በመቀጠል ሁለተኛ ቡድኗ ወደሆነው እና በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ይሰለጥን ወደነበረው ኢትዮጵያ ቡና በአሰልጣኙ አማካኝነት ተጠርታ በመሄድ የአንድ ዓመት ቆይታን በቡናማዎቹ ቤት ካደረገች በኃላ 1999 ላይ በአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ተይዞ ወደነበረው ሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተቀላቀለች። ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከተዘዋወረ በኃላም በንግድ ባንክ እስከ 2005 ድረስ ቆይታ በማድረግ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ አንስታለች፡፡ ተጫዋቿ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የለቀቀችበት ቅፅበት ግን ዛሬም ድረስ ከውስጧ የማይጠፋ እንደሆነ ታስታውሳለች።

“ከንግድ ባንክ ጋር ከአቅም ማነስ ወይንም በችሎታ ማነስ ሳይሆን በራሳቸው ስህተት ነው የወጣሁት፡፡ 2004 ፕሪምየር ሊግ ተጀምሮ ደደቢት ዋንጫ አነሳ። በዚህም በጣም አዝነን ነበር። 2005 ላይ በጣም በጥሩ ሁኔታ ተዘጋጀን፤ ቡድናችንም በጣም ደስ የሚል ነበር። በአጋጣሚ ሆኖ በጣም የምወዳት፣ ለእኔ ህይወቴ የነበረች ፣ ኳስ እንድጫወት ብዙ የሆነችልኝ አያቴ ነበረች (እያለቀሰች) እሷ አርፋ ወደ ቤት ሄድኩ። ብዙም አልቆየሁም ስመለስ አቶ ተፈራ የሚባል የባንክ የበላይ አመራር ቃል አስገብቶን ነበር። ‘ሁለት ዋንጫ በዚህ ዓመት ማግኘት አለብን። የፕሪምየር ሊጉንም ሆነ የጥሎ ማለፉንም’ ብዬ ቃል የገባሁት እኔ ነበርኩ። ቤተሰብ ጋር ለቅሶ ሄጄ አራት ቀን ቆይቼ የደወሉልኝ ጓደኞቼም ነበሩ። ከእናቴ ጋርም ተነጋግሬ የገባሁትን ቃል ለማሳካት ተመልሼ ወደ ክለቤ መጣሁ። እንዳልኩትም ፈጣሪ ረድቶን የሊጉን ዋንጫ አሳካን፤ ከዛ ጥሎ ማለፉንም አግኝተን ለአቶ ተፈራ አስረከብን። በዓመቱ መጀመርያ እንደዛ አዝኜ የነበረ ቢሆንም እነዚህ ነገሮች ስለተሳኩልኝ በጣም ደስ አለኝ። ለ2006 የአብዛኛዎቻችን ኮንትራት አልቆ ነበር። ስንነጋገርም ስለጥሩነቴ አንስተው ‘እኛ ጋር እንድትቀጥይ ነው የምንፈልገው’ አሉኝ። እኔም ለራሴ የሚሆነኝን የሚመጥነኝን ገንዘብ ተናገርኩ። ‘እሺ’ አሉ። ምን እንደተፈጠረ አላውቅም፤ ወዲያው የማይመጥነኝን ገንዘብ ነገሩኝ። ነገሩን ግን ከጊዜ በኃላ ስሰማው ነው በጣም ያዘንኩት። ይሄ ብር እኔን አይመጥነኝም ከጓደኞቼ ጋር ለፍቼ ይሄን አድርጌያለሁ እና በቂ አይደለም ብዬ ወጣሁ። ውጪ ላይ ጓደኞቼን አግኝቼ ስነግራቸው አዘኑ። አቶ ተሾመ፣ አስናቀ እና አሰልጣኝ ብርሀኑ ባሉበት ነው ይሄን ያሉኝ። በጣም አዝኛለሁ ፣ ተናድጄያለሁ ስልኬንም አጥፍቼ ነበር። ሰኞ ነበር ይሄ የተፈጠረው። ስልኬን ረቡዕ በአጋጣሚ ስከፍተው ዳሽኖች ደወሉ። ‘በክልሉ ያሉ ሴቶችን ለማውጣት ታስፈልጊናለሽ’ አሉኝ። ባንክ የከለከለኝን ብር እነሱ ሰጡኝ ፤ እና ዳሽን ገባሁ። ከሆነ ጊዜ በኃላ አስናቀ እና ብርሀኑ ሲደውሉልኝ ዳሽን ፈርሜያለሁ አልኳቸው።” በማለት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ለመለያየት የበቃችበት እና ወደ ዳሽን ቢራ ስላመራችበት ሂደት ባዘነ ንግግሯ አውስታናለች፡፡ ወደ ዳሽን ከሄደች በኋላ በንግድ ባንክ ስኬታማ ለነበረው ቡድን ሽልማት ሲሰጥ እሷ ባለመካተቷም የተሰማትን ሀዘን ጨምራ ተናግራለች።

ከንግድ ባንኩ የሁለትዮሽ ዋንጫ በኋላ በዳሽን ቢራ በ2006 እና 2007 በመጫወት ያሳለፈችው ቱቱ በቆይታዋም በመጀመሪያ ዓመቷ ክለቡ አራተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን በሁለተኛ ዓመት ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ ድርሻዋ የጎላ ነበር፡፡ የሰሜኑን ክለብ ለቃ ቅዱስ ጊዮርጊስን 2008 ላይ ተቀላቅላም በአሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ ስብስብ ውስጥ ካሳለፈች በኃላ በ2009 ወደ አዲስ አበባ ከተማ ተዘዋውራ ተጫውታለች። በ2010 በድጋሜ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተመልሳ በመጫወት ላይ እያለችም ለሙከራ ከሎዛ አበራ ጋር ወደ ስዊድን አምርታ ከአምስት ወራት በላይ ቆይታን አድርጋ ተመልሳለች።

በብዙሀኑ የሴት እግር ኳስ ተመልካቾች ዘንድ እንደ መሪ የምትታየው ተጨዋቿ በነበረችባቸው ክለቦች በአብዛኛው የአምበልነት ሚናም ሲሰጣት ይታያል። ይህን አስመልክታም ስትናገር “አምበልነትን የጀመርኩት ለዞን ከምጫወትበት ጊዜ አንስቶ ነው። ልምዱም ስላለ በተከታታይ ዕድሉንም ስላገኘው አልከበደኝም። ብሔራዊ ቡድኑን በአምበልነት አልመራሁም። በክለብ ግን በአምስቱንም ክለቦች አምበል ሆኛለሁ። ሜዳ ላይ ባለኝ ባህሪ መሸነፍን አልፈልግም። የቡድን አጋሮቼን በምችለው አቅሜ ለማነሳሳት እሞክራለሁ። እነሱም ባህሪዬን ያውቁታል። መጥፎ ነገር አይደለም። ያልሸነፍ ባይነት ሆኖ ቡድንህ ይዘህ የምትወጣበት ዓይነት ነው። ከሜዳ ውጪ ባለኝ ባህሪ ግን ተግባቢ ነኝ።” ትላለች።

ከ1995 ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን
ስትጫወት የቆየችው ቱቱ በ2008 በአሰልጣኝ በኃይሏ ዘለቀ የአሰልጣኝነት ዘመን ጀምሮ ግን በብሔራዊ ቡድን ይያላት ተሳትፎ እምብዛም ነበር። ተጫዋቿ በብሔራዊ ቡድን አጠቃላይ ምርጫ ዙሪያ ስትናገር ” ብሔራዊ ቡድን ስትመረጥ ወቅታዊ ብቃት ነው እንጂ ስም አይደለም ሊያስጠራ የሚገባው። ብቃቴ ጥሩ ከሆነ መመረጥ አለብኝ ብዬ ነው የማስበው። እኔን ብቻ አይደለም ሌሎች ጓደኞቼም መመረጥ አለባቸው። ያልተመረጡበት ምክንያት አይጠየቅም። አብዛኛዎቹ ጋዜጠኞችም ትኩረት ሰጥተው ስለማያዩ ውድድሩንም ስለማይከታተሉ ‘እከሊት ለምን አልተመረጠችን ?’ ብለው አይጠይቁም። የአቅም ችግር ኖሮ አይደለም። ብዙ ያልተመረጡ አሉ ፤ ብዙ ዋንጫ ያነሱ እና ዋጋ የከፈሉ። ለምሳሌ ወይንሸት ኦሎምቤን ማየት ይቻላል። በደደቢት በተከታታይ ነው ዋንጫ የወሰደችሁ ግን አልተመረጠችም። ብዙሀንም ባንክ እያለች ጥሩ ነበረች ፣ አምበልም ነበረች ፤ ግን አልተመረጠችም። እኔ እንኳን 2010 ላይ በሰላም ዘርዓይ ጊዜ ተጠርቼ ነበር ፤ ጉዳት ላይ ስለነበርኩኝ አልተጫወትኩም።”

ቱቱ ኮስተር ካለው የብሔራዊ ቡድን ምርጫ አስተያየቷ መለስ ከገጠመኞቿ መሀል ሁለቱን እንዲህ አጫውታናለች። “አንድ ጊዜ ሴንትራል እያለሁኝ ጪስ አባይን ለማየት ሄደን ነበር ፤ አብነት ግርማይ ጋብዞን። በጀልባ ታልፎ ነው ጪስ አባይን ማየት የሚቻለው። ሳየው ደነገጥኩኝ ፤ ውሀ ብዙም አልወድም። ሽታዬ እና ረሂማ ‘መሄድ አለብሽ መግባት አለብሽ’ አሉኝ። እኔ ‘እንቢ’ አልኳቸው። ሲያባሩኝ ሁሉ ያመለጥኳቸው ነገር አይረሳኝም። ሮጬ እየጮሁኩኝ አመለጥኳቸው። በእግር ከሆነ ደግሞ 30 ደቂቃ የሚፈጅ የእግር መንገድ አለው። ሦስት ሆነን በውሀው ላለመሄድ በእግር ሄድን። መጨረሻ ከእነሱ ጋር ተገናኘን። ሌላው ደግሞ ከሎዛ ጋር ስዊዲን እያለን እንደነገ ጨዋታ ካለ እንደዛሬ ይነገረናል። እቃዎቻችንን አስተካክለን ነው የምንሄደው። በአጋጣሚ ሆኖ እኔና ሎዛ መልበሻ ክፍል ውስጥ የመጀመሪያ ተሰላፊዎች መሆናችን ተነገረን። ነገር ግን መጋጫዬን አጣሁት። ካለመጋጫ ደግሞ እዛ ሀገር የማይቻል ነገር ነው ፤ መዋዋስም አይቻልም። ካርቶንም እንኳን ብፈልግ አጣሁ። በአጋጣሚ አንዷ ውሀ እየጠጣች ነበር። እስክትጨርስ ጠብቄ የውሀ ፕላስቲኩን ቁጭ ስታደርግ መፀዳጃ ቤት ገብቼ በመቀስ ቆረጥኩት እና እንደ መጋጫ አድርጌ ተጠቀምኩት። ከውስጥ እንዳይቆርጠኝ ሶፍት አደረኩበት እና በፕላስተር ከውስጥ አስሬ ስወጣ ሎዛ አየቺኝ። ‘የት አገኘሽ ? ‘ ስትለኝ ያደረኩትን ስነግራት በጣም ሳቀች።”

በመጨረሻም እዚህ ለመድረሷ ያገዟትን በዚህ መልኩ አመስግናለች። “ደሴ እያለሁ ከወንዶች ጋር ስጫወት የመጀመሪያ አሰልጣኜ ግደይ ወልደትንሳኤ እንደምችል አቅሙ እንደዳለኝ እየነገረኝ ከወንዶች ጋር አብሮ የሚያጫውተኝ ፣ ከዛን ቀጥሎ ሴቶች ፕሮጀክት ከገባሁ በኃላ አሰልጣኜ መስፍን በላይ ፣ ከዛም የምወደው እና የማከብረው ትዕግስት ይመር ፣ እሸቱ አሊ እና ዮናታን በትረ በግል ልምምድ እንደድሰራ ‘ካሉት ልጆች የተሻልሽ ነሽ ፤ ይሄን ይሄን መስራት አለብሽ’ በማለት ብዙ አግዘውኛል ፤ ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ። በመቀጠልም አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ፣ ጋሽ አዳነ ፣ በለጥሽ ገብረማርያም በጣም ትልቅ ነገርን ነው ያደረጉልኝ። እንዳልፈራ መጫወት ባለብኝ ልክ እንድጫወት የተከላካይ አማካኝነቴን በደንብ እንዳውቀው የረዱኝ ናቸው። በክለብ ደረጃ የመጀመሪያ አሰልጣኜ አስራት አባተም እንደድበረታ ረድቶኛል። በአለቤሾው ቆይታዬ አሰልጣኝ ብርሀኑንም ማመስገን እፈልጋለሁ። ግን በህይወቴ እዚህ እንድደርስ በህይወት የሌለችው አያቴ ከምለው በላይ ብዙ አስተዋጽኦ አድርጋልኛለች። ከሁሉም በላይ ደግሞ እዚህ ላደረሰኝ የድንግል ማርያም ልጅ ክብር ምስጋና ይግባው።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ