“ከባህር ዳር ጋር ለመቆየት የወሰንኩት ለተሻለ ስኬት ነው ” ፍፁም ዓለሙ

የባህር ዳር ከተማ ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን በመጣበት ዓመት ማስመስከር የቻለው አማካዩ ፍፁም ዓለሙ በቀጣይ ዓመት ከጣና ሞገዶቹ ጋር ሰለሚያስበው እቅዱ ይናገራል።

ደሴ ከተማ የተወለደው እና ለጥቁር ዓባይ፣ ደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ እና ፋሲል ከነማ መጫወት የቻለው ይህ አማካይ በያዝነው ዓመት ከፋሲል ከነማ ጉዞውን ወደ ባህር ዳር በማድረግ ድንቅ የሚባል ጊዜን አሳልፏል። በተለይ በተጫወተባቸው አመዛኙ ጨዋታዎች ላይ ከአጥቂ ጀርባ ቦታ በመነሳት በሊጉ ዘጠኝ ጎሎችን አስቆጥሯል፣ ለጎል የሚሆኑ ዕድሎችን በመፍጠር የክለቡ የልብ ምት መሆኑንም አሳይቷል። እንዳሳለፈው መልካም የውድድር ዓመት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምርጫ ውስጥ አለመካተቱ ብዙዎችን ያስገረመ መሆኑም ይታወቃል።

ድንቅ አቋሙን የተመለከቱ የሊጉ ቡድኖች ዓይናቸውን አሳርፈውበት እርሱን ወደ ክለባቸው ለማምጣት ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ሲሆን መቐለ 70 እንደርታ እና ፋሲል ከነማም በይበልጥ ስማቸው ከእርሱ ጋር የተያዙ ክለቦች ነበሩ። ሆኖም ጥሩ የውድድር ዓመት ካሳለፈበት የጣና ሞገዶቹ ጋር ለተጨማሪ ዓመት ለመቆየት ፊርማውን አኑሯል። ይህ ዜና ለባህር ዳር የቡድን አባላት እና ለደጋፊዎቹ እፎይታ ሰጥቷል። ይህ አማካይ ከባህር ዳር ጋር ለመቆየት የወሰነበትን ምክንያት እና በቀጣይ ስለሚያስበው እቅዱ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

” አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሰጠኝ የመጫወት ነፃነት እና የባህር ዳር ደጋፊዎች የሰጡኝ ድጋፍ ከቡድን አባሎቼ ጋር በመሆን እጅግ ጥሩ የሚባል ጊዜ ከባህር ዳር ጋር እንዳሳልፍ አድርጎኛል። አሁን ይህን የተሳካ ቆይታ ማስቀጠል እፈልጋለው። እርግጥ ነው ብዙ ክለቦች እኔን ለማስፈረም ፍላጎት ነበራቸው። ሆኖም ባህር ዳር ጋር ለመቆየት የወሰንኩት ዘንድሮ የነበረኝን አቋም በተሻለ ሁኔታ ለመድገም ነው። ቡድናችን ዘንድሮ ራሱን ለማጠናከር በጣም ጥሩ ተጫዋቾች እያስፈረመ ነው። በቀጣይ ከባህር ዳር ከተማ ጋር የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ለማንሳት ነው የማስበው።” ብሏል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ