ዛሬ በነበረ መርሃግብር ውድድሮች ለመጀመር የሚያስችለው የመነሻ ሰነድ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከቀረበ በኋላ ክለቦች ውይይት አድርገዋል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ፣ የከፍተኛ ሊግ እንዲሁም የሴቶች 1ኛ እና 2ኛ ዲቪዚዮን ክለብ ተወካዮች በተገኙበት ውድድሮች የሚጀመሩበትን የመነሻ ሰነድ አቅርቦ እንደነበረ መዘገባችን ይታወሳል። በአሁኑ ጥንክራችን ደግሞ ሰነዱ ለ40 ደቂቃዎች ያክል ከቀረበ በኋላ የነበረውን ውይይት እና የተቀመጠውን አቅጣጫ ይዘን ቀርበናል።
አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ፣ አቶ ሰለሞን ገብረሥላሴ እና አቶ ሙሉጌታ ምስጋናው በሶስቱ የተለያዩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ካቀረቡት ገለፃ በኋላ በስፍራ ክለቦቻቸውን ወክለው የተገኙ አመራሮች በሰነዱ ዙሪያ ሃሳቦችን ሰንዝረዋል። ለአብነትም:-
“ሰነዱ መቅረቡ በጣም መልካም ነው። ሜዳዎችም ለመነሻ ሃሳብነት መለየታቸው በጣም የሚያበረታታ ነወ። በቀጣይ ግን አፅንኦት ሰጥተን መነጋገር ያለብን ሊጉን በቀረበው መነሻ ሰነድ አማካኝነት እያከናወን ገቢ የምናመነጭበትን መንገድን በተመለከተ ቢሆን ጥሩ ነወ። ጨዋታዎች በዝግ ስለሚከናወኑ የሜዳ ገቢ አይኖረንም። ስለዚህ በቴሌቪዥን እና ሬዲዮ ገቢ ማግኘት አለብን። ከዚህ ውጪ ግን የቀረበውን ሰነድ ክለባችን ይቀበላል።” አቶ ይርጋ (የመቐለ 70 እንደርታ)
“የክለባችንን የቀጣይ ዓመት በጀት መጋቢት ወር ላይ አስይዘናል። በጀቱንም ስናሲዝ የሜዳ ገቢን ታሳቢ አድርገን ነበር። ይባስ ብሎ አሁን ላይ ተጨማሪ የትራንስፖርት፣ የህክምና እና የሆቴል ወጪዎች አለብን። ከዚህ ውጪ የህክማና ባለሙያም በቋሚነት መቅጠር እንዳለብን በሰነዱ ተብራርቷል። ስለዚህ እንዴት ነው ይህንን የምናደርገው? ሃሳቡ ጥሩ ቢሆንም ጉዳዩን በፅሞና ይዘን መምከር አለብን።” አቶ ታፈሰ
“በተሰረዘው የ2012 የውድድር ዘመን በርካታ ክለቦች ለተጫዋቾቻችን ደሞዝ መክፈል ተስኖን ነበር። ይህንን ችግር ሳንፈታ እንዴት ቀጣይ ሊጋቸንን በተጋነነ ወጪ እናከናውናለን? ስለዚህ ውድድሩን በቀረበው መልክ ማድረግ አለብን ወይ የሚለውን በደንብ ማጤን አለብን።” አቶ ዳዊት (ድሬዳዋ ከተማ)
“ከምንም በላይ ክለቦቻቸን ተጨማሪ በጀት በጅተው ውድድሩን የማድረግ ቁመና ላይ ናቸው ወይ? የሚለውን ጥያቄ በደንብ መመርመር አለብን። ከዚህ በተጨማሪ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን የእድገት መጠን ማየት ያስፈልጋል። እኔ በግሌ ውድድር መኖር የለበትም የሚል ጭፍን አስተሳሰብ የለኝም። ግን ጉዳዩን ጊዜ ሰጥተን መምከር አለብን።” አቶ ገዛኸኝ (ኢትዮጵያ ቡና)
እኛ በስራችን 6 ክለቦቸ አሉ። እነሱን ምን ልናደርግ ነው። እርግጥ ክለባቸን የመንግስት ቢሆንም በሰነዱ ላይ በተብራራው ልክ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የሚያስችል የፋይናንስ አቅም የለንም። ለዛውም የሜዳ ገቢ ሳይኖረን። ይህ ከሆነ ግን በስራችን ያሉትን ሌሎች ቡድኖች ለመበተን እንገደዳለን።”አቶ ሆቴሳ (ሃዋሳ ከተማ)
“እኛ በጀት ያስያዝነው በእስካሁኑ አካሄድ ነወ። እርግጥ ደሞዝ ያልከፈልናቸው ተጫዋቾች አሉ። ግን የእነሱንም ደሞዝ በዚህ በጀት ለመክፈል አስበናል። ከዚህ ውጪ ግን ምንም ታሳቢ ያደረግነው ተጨማሪ በጀት የለም። ፌዴሬሽኑ እግርኳስ ለማከናወን በሚያስችል መመሪያ ላይ ሰነዶችን ማዘጋጀቱ እጅግ መልካም ነወ። ግን ክለቦች አሁን ባለን አቅም እና ቁመና ማድረግ የምንችል አይመስለኝም። ውድድር ለማድረግ ከቸኮልን ግን ያሉንን ተጫዋቾች ኮቪድ ለማስያዝ የምንሮጥ ነው የሚያስመስልብን።” አቶ ዮሴፍ (አዳማ ከተማ)
“ሰነዱ ብዙ ቡድኖችን ታሳቢ ያደረገ አደለም። ለምሳሌ እኛ በስራችን ከእግርኳሱ ውጪ እንኳን ብዙ ቡድኖች አሉን። ስለዚህ ይህ ነገር መታሰብ አለበት። አልያም መንግስት የሚደግፍበትን መንገድ ቢመቻች ጥሩ ነው።”የመከላከያ ተወካይ
“ሲጀምር በበቂ ሁኔታ የመመርመር አቅም አለን ወይ? የፀረ ተዋሲ ርጭት የሚያከናውኑ በቂ ተቋማት በብዛት አሉን ወይ? እንዲሁም የምርመራውን ወጪ ክለቦች ይችሉታል ወይ? የሚለውን መመለስ አለብን። “አቶ ተምትም (ኢትዮጵያ መድን)
ከላይ የተጠቀሱት አካላት እና ሌሎች በቦታው የተገኙ የክለብ አመራሮች ሃሳቦችን እና ጥያቄዎችን ወደ መድረኩ ከሰነዘሩ በኋላ ምላሾች እና ገለፃዎች ተደርገዋል። በዚህም የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ በውይይቱ ወቅት የታዘቡትን ነገር ተናግረዋል።
“ዛሬ የተሰባሰብነው መፍትሄ የሚገኝበትን መንገድ ለማየት ነው። ላጋጠመን የራስ ምታት መዳኒት ለመግዛት። ስለዚህ ሃሳቦቻችሁ በጥሩ መንፈስ ቢሰነዘሩ መልካም ነው። በርካታ የዓለማችን ሃገራት ውድድሮችን እየጀመሩ ነው። ጎረቤታችን ሱማሊያን ጨምሮ። ይህንን ስል እነሱ ስለጀመሩ እኛም እንጀምር ማለት አደለም። ቢያንስ ግን መንግስት ጀምሩ ሲለን የምናስጀምርበትን ሂደት ካሁኑ መወያየት አለብን። በተቻላችሁ መጠን በእግርኳሱ የሚተዳደሩትን አካላት ማሰብ አለባችሁ።” ብለዋል።
ከክቡር ፕሬዝዳንቱ ንግግር በኋላ የፕሪምየር ሊጉ አ/ማ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ በቦታው የተገኙትን የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተወካይ ንግግር እንዲያደርጉ ጋብዘዋል። በቦታው የተገኙት ዶ/ር ኢማንም ገለፃ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
“እንደ መንግስት አካል ብዙ ውይይቶችን አድርገናል። ሰነዱንም ከፌዴሬሽኑ ጋር በጋራ አውጥተናል። ግን ምርመራ በመንግስት በኩል ይሁንልን። አቅም የለንም ላላችሁት ነገር አሁን ላይ ቃል መግባት አንችልም። የሃገራችን የምርመራ አቅም በጣም ያነሰ እንደሆነ ይታወቃል። በነፃ የምንመረምረውም በጣም ለሚያስፈልጋቸው ብቻ ነው። ስለዚህ ይህንን ተረዱ። በተቻለ አቅም ግን ወጪዎችን ቀንሳችሁ እንዴት ምርመራ እንደምታደርጉ መምከር እንችላለን። ወጪ ቆጣቢ መርሃ ግብሮችንም ለማውጣት መነጋገር ይቻላል። ከዚህ ውጪ የወረርሽኙ እድገት መቼ ጣራ እንደሚደርስ መገመት ይከብዳል። በያዝነው ወር በተያዘ የዘመቻ የመርመራ መርሃግብር ላይ ምናልባት ያለውን ውጤት ተንተርሰን ግምቶችን ልናስቀምጥ እንችላለን። በተጨማሪም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በድጋሜ ስለሚከለስ ነገሮችን ወደፊት መከታተሉ ይበጃል።” ብለዋል። ዶ/ር ኢማን የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በሚገኙበት የስብሰባ አዳራሽ ይህንን ሃሳብ ከሰጡ በኋላ በሌላኛው አዳራሽ ከጤና ሚኒስቴር የመጣው ሌላ ተወካይ የሰጡትን ማብራሪያ ተከታትለናል።
“አሁን ላይ የመመርመር አቅማችን እየጨመረ ነው። በአምስት ወራቶች ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን መርምረናል። በተጨማሪም 51 የመመርመሪያ ጣቢያዎችን ከፍተናል። ስለመመርመሪያ ዋጋ የተነሳው ጥያቄን በተመለከተ የጤና ሚኒስቴር ላቦራቶሪውን በነፃ ነው ክፍት አድርጎ ምርመራ የሚያከናውነው። የተባለው ክፍያ($20 በሰው) የግል ላቦራቶሪዎች የሚያስከፍሉት ነው። ስለዚህ ምርመራዎች በእኛ በኩል የሚሄዱበትን መንገድ በተመለከተ ከፌደሬሽኑ ጋር የምንወያይ ይሆናል።”
ዶ/ር ይሄነው ሃሳቡን ሲቀጥል “በፕሮፖዛሉ ላይ የተጠቀሱት የመወዳደሪያ ቦታዎች ላይ በቂ ላቦራቶሪዎች አሉ። የክልሉ ከ4-15 የሚደርሱ መመርመሪያ ጣቢያዎች አሉ። ስለዚህ ጨዋታ ሲኖር ለየክለቦቹ ቅድሚያ እንዲሰጥ ማመቻቸት ይቻላል። ነገርግን በ15 ቀን 200 ሺ ሰዎችን መርምን በምናገኘው ውጤት ተንተርሰን ውድድር መጀመሪያ ጊዜው ሊወሰን ይችላል። ከፀረ-ተዋሲ ጋር በተገናኘ ደግሞ የተጋነነ የማፅጃ ቁሶች አያስፈልጉም። በረኪና እና የመሳሰሉትን በመጠቀም ማፅጃውን ማዘጋጀት ይቻላል። በተጨማሪም ከፅዳት ሰራተኛ እስከ ከፍተኛ አመራር ድረስ ስልጠናዎችን እንዲወስዱ እናመቻቻለን።”
ከፍተኛ ሊጉን በተመለከተ የተሰበሰቡት የክለብ አመራሮች የቀረበው ሰነድ ተሰጥቷቸው የማዳበሪያ ተጨማሪ ሃሳቦች ይዘው በቀጣይ እንዲመጡ ወስነው ወጥተዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በተመለከተ ደግሞ የሊግ አ/ማ ውስጥ የተመረጡት የውድድር እና ሥነ ስርዓት ኮሚቴ አባላት መነሻ ሰነዱን ተንተርሰው ተጨማሪ ጥናቶችን ለአክሲዮን ማኅበሩ አባላት እንዲያቀርቡ ተወስኗል። በጥናቱም ውድድሩን ለማስኬት ሰነዱ ላይ የተብራሩት ነጥቦች፣ የምርመራ ወጪ፣ የመጫወቻ ሜዳ እና አጠቃላይ የፋይናንስ ወጪን አጥንተው እንዲቀርቡ ተወስኗል። በዶ/ር ወገኔ ዋልተንጉስ የሚመራው የማኅበሩ የውድድር እና ሥነ ስርዓት ኮሚቴም ጥናቱን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚያዘጋጅ እና ለአባላቶቹ ገለፃ እንደሚደረግ ተነግሯል። በዚህም በመስከረም ወር በሚመጣ የመጀመሪያ ሳምንት ጥናቱ ቀርቦ የሊግ አክሲዮን ማኅበሩ ለፌደሬሽኑ ውድድሩ የሚጀመርበትን ምክረ ሃሳብ እንደሚያቀርብ ተጠቁሟል።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ