አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ከተለያዩ ድረ-ገጾች ያገኛቸውን የእግርኳስ ታክቲክ ንድፈ-ሐሳቦችን የተመለከቱ ጥልቅ ትንተናዎች፣ የሥልጠና መመሪያዎች እና መጻህፍትን ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ በመተርጎም ሌሎች አሰልጣኞችና አንባቢን ይጠቅም ዘንድ ጥቅም ላይ ለማዋል ይሞክራል፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው ፅሁፍም አንዱ አካል ነው፡፡
ጸሃፊ – ማክስ በርግማን
ትርጉም – ደስታ ታደሰ
በእግርኳስ አጨዋወት ስልቶች ላይ የሚቀርቡ በርካታ የመከራከሪያ ሐሳቦች ይኖራሉ፡፡ ያም ሆኖ ሁሉንም አሰልጣኞች የሚያስማማ- ምናልባትም ብቸኛ የሆነ ዘይቤ ቢኖር የመልሶ-ማጥቃት ዘዴ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በእግርኳስ ግብ ማስቆጠር የሚቻልባቸው መንገዶች የተለያዩ ሆነው እናገኛቸዋለን-በኳስ ቁጥጥር የበላይነት በመውሰድ፣ ከቆመ ኳስ፣ አልያም በመልሶ-ማጥቃት ጎሎች ሊገኙ ይችላሉ፡፡ በዚህ ፅሑፍ የመልሶ-ማጥቃት ዘዴን መተግበር ከሚሰጣቸው ጥቅሞች የተወሰኑትን ለማሳየት ተሞክሯል፡፡
ከታች በሚቀርበው ዝርዝር ትንተና የተለያዩ የመልሶ ማጥቃት አተገባበር እና መነሻ ሐሳቦችን በጥልቀት እንቃኛለን፡፡ ዓላማው የዘይቤውን ፋይዳ እና አሉታዊ ገጽታውን መለየት እንዲሁም አጨዋወቱ ከተጫዋቾች ጋር በምን መልኩ እንደሚስማማ ወይም እንደሚዛመድ ማሳየት ይሆናል።
የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ለምን ውጤታማ ሆነ?
” እኛ (ማንችስተር ሲቲ) የመልሶ-ማጥቃት አጨዋወትን እንተገብራለን፡፡ ሥልቱ ጠንካራ መሳሪያ ነው፡፡ ትልልቅ ቡድኖች ሊጠቀሙ የሚገባቸውን ሁሉንም መሳሪዎች ይጠቀማሉ፡፡” ፔፕ ጓርዲዮላ
እግርኳስ ሁሌም ሜዳ ላይ በሚፈጠሩ ክፍት ቦታዎች ላይ የሚወሰን ጨዋታ ነው፡፡ አንድ ቡድን በኳስ ቁጥጥር የበላይነት በወሰደ መጠን የተሻለ ክፍት ቦታዎች ያገኛል፤ የበለጠ ግብ የማስቆጠር ዕድልም ይፈጥራል፡፡ የመልሶ-ማጥቃት አጨዋወት ስልት አዋጭነት የሚመነጨውም ከእንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ይሆናል፡፡ አንድ ቡድን የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ሲያገኝ የጎንዮሽ ስፋትን (Width) እና በሜዳው ቁመት የሚኖር ተለጣጭ ጥልቀትን (Depth) ሙሉ በሙሉ የሚጠቀም ከሆነ ኳስን በተጋጣሚ ቡድን በሚነጠቅበት ቅጽበት በተጫዋቾች መካከል የሚፈጠረውን የጎንዮሽ እና የፊትለፊት ጥግግቱን (Compactness) ያጣል፡፡ ይህም ኳስ የነጠቀው ቡድን ተጫዋች ከኳስ ጋር የሚያሳልፈው በቂ ጊዜ እንዲያገኝ ይረዳዋል፤ ተገቢ ውሳኔ የማሳለፍ አጋጣሚንም ይጨምርለታል፡፡
ብዙውን ጊዜ እግርኳስ ተጫዋቾች ከኳስ ጋር እና ያለኳስ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለየቅል ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህ ማለት ተጫዋቾች በቁጥጥራቸው ሥር የነበረን ኳስ እንዳጡ በቀጥታና በፍጥነት ከማጥቃት ወደ መከላከል በሚደረግ ሽግግር ውስጥ ራሳቸውን ያገኛሉ፡፡ ከታች ባለው ምስል የአር-ቢ-ላይቭዚሽ ተጫዋቾች ከተጋጣሚያቸው የሜይንዝ 05 ተጫዋቾች ኳስን ሲነጥቁ እናያለን፡፡ሜይንዞች ሜዳውን ወደ ጎን ለጥጠው ስለሚጫወቱ በመሃለኛው የሜዳ ክፍል የሚተውት ሰፊ ክፍተት አለ፡፡ ስለዚህም ላይቭዚሾች ይህን ቦታ ለመጠቀም ራሳቸውን ሲያዘጋጁ ይታያሉ፡፡ አልፎም በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ግብ ማስቆጠር እንደቻሉም ይታያል፡፡
ከላይ በምስሉ እንደታየው አንደኛው የላይብዚሾች አጥቂ የተጋጣሚውን ተከላካዮች ተጭኖ ሲጫወት ሌላኛው አጋሩ ደግሞ ከመከላከል ወደ ማጥቃት ለሚደረግ ሽግግር ራሱን አመቺ ቦታ ሲያደርግ ይስተዋላል፡፡ በዚህም ላይቭዚሾች ኳስን ከተጋጣሚያቸው በቀሙበት ቅጽበት ያገኙትን ክፍት ቦታ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ይጠቀሙበታል፡፡
በጨዋታ ወቅት የተጋጣሚ ቡድን በሚገባ የማይደራጅበትን አጭር ቅጽበት በመልሶ ማጥቃት ሥልት ለራስ ቡድን ጥቅም ለማዋል በቂ ጊዜ ማግኘት ስለሚያስቸግር ከተጫዋቾች ፈጣን እና ልከኛ የውሳኔ አሰጣጥ ሒደት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ የቀድሞው የአያክስ አሰልጣኝ ፒተር ቦዝ ይህን የመልሶ-ማጥቃት ዘመናዊ አጨዋወት በማስመልከት በመልሶ-መጫን (Counter-Pressing) መጫወት ‹የአምስት-ሰከንድ› ጉዳይ መሆኑን ያነሳል፡፡ በእርግጥ መልሶ-ማጥቃትን በአግባቡ ለመከወን ስለሚያስፈልገው የጊዜ ገደብ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ፡፡ ይሁን እንጂ አንድ ቡድን ከባላጋራው ቡድን ኳስ ከነጠቀበት ከአምስት እስከ ስምንት ሰከንዶች ባሉት ጊዜ ውስጥ መልሶ-ማጥቃትን መተግበር ከቻለ ተቃራኒ ቡድን በቶሎ የመከላከል ቅርፁን እንዳያገኝ ያደርገዋል፡፡
እንደሚታወቀው የእግርኳስ ጨዋታ በተለይ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በሚያዝበት ጊዜ አያሌ ቅጽበታዊ ለውጦችን የሚያስተናብር ስፖርት በመሆኑ የማጥቃትና የመከላከልን ሒደቶችን ነጣጥሎ ለመመልከት አዳጋች ይሆናል፡፡ ይህ ሃሳብ አንድ ቡድን በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ሆኖም ስለ መከላከል እንዲጤንና እንዲዘጋጅ፥ በመከላከል ሒደት ላይ ሲሆን ደግሞ የማጥቃትን አዕምሮ እንዲላበስ እንደሚያስፈልግ ያሳየናል፡፡ በተጨማሪ የመከላከል አደረጃጀትን በአግባቡና በፍጥነት የሚመልስ ቡድን በትክክለኛ ቦታና ጊዜ ላይ ሆኖ ኳስን መንጠቅ ይቀለዋል፤ ቀጣዩን የማጥቃት ሒደት ለማቀላጠፍም ይመቸዋል፡፡
…ይቀጥላል
የጽሁፉ ተርጓሚ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል፡፡ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፂዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ