ለሀገራችን አሰልጣኞች በተደጋጋሚ እየተሰጠ ያለው የኦንላይን ስልጠና ዛሬም ቀጥሎ በቀድሞው የሼፊልድ ዩናይትድ እና የላቲቪያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ በነበሩት ጎርደን ያንግ ተሰጥቷል፡፡
ዛሬም ማምሻው ከ12:30 ጀምሮ እስከ 2:00 ድረስ በአሰልጣኝ ጎርደን ያንግ አማካኝነት በሀገራችን ላሉ የሊግ አሰልጣኞች የተሰጠው ስልጠና በዋናነት ትኩረት ያደረገው አንድ ቡድን ከጨዋታ በፊት ሊያደርጋቸው የሚገቡ የቅድመ ሁኔታዎች፣ ዝግጅቶች እንዲሁም የተጋጣሚ ቡድንን መረጃ አግኝቶ የራሱን ቡድን አንድ አሰልጣኝ ለጨዋታ ማዘጋጀት እንዴት እንዳለበት፣ የምግብ አመጋገብ እና የእረፍት አወሳሰድ አካተው አሰልጣኙ በትምህርት መልክ ዘርዘር ባለ ሀሳብ ለሰልጣኞች ገለፃን አድርገዋል፡፡
ይህን ስልጠና በዋናነት እየመሩ የሚገኙት ኢንስትራክተር አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደተናገሩት በስልጠናው ተሳታፊ የነበሩ ሰልጣኞች ማብራርያ ሲጠይቁ የነበረ ሲሆን ከአሰልጣኙም በቂ ምላሽ እንደተሰጣቸው ነግረውናል። ከዚህ በተጨማሪ በስልጠናው ተሳታፊ የነበሩ አሰልጣኞች ሰፋ ያለ ጥልቅ ሀሳብን በዛሬው ውይይት እንዳገኙበትም ነግረውናል፡፡ በወጥነት እየተሰጠ ያለው ይህ ስልጠና በቀጣዩ ረቡዕ የሚቀጥል ሲሆን ከባየር ሙኒክ በተጋበዙ አሰልጣኞች እና ባለሙያዎች ይከናወናል። በመቀጠልም ሀገር ውስጥ ባሉ የካፍ ኢንስትራክተሮች ይህ ስልጠና እንደሚሰጥም አሰልጣኝ አብርሀም ጠቁመውናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከኳታር እግር ኳስ ፌድሬሽን ጋር በትብብር ለሀገራችን የሚሰጠውን ሁለተኛ መርሀ ግብርም በቀጣዩ ቀናት በሂደት እንደሚቀጥል ሰምተናል፡፡
እንደ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ገለፃ ከሆነ ለሀገራችን የግብ ጠባቂ አሰልጣኞች በቤልጂየም ከፍተኛ ኤክስፐርቶች እና አሜሪካ ባለው አሰልጣኝ አምሳሉ ፋንታውን በተጋበዘ ባለሙያ ግብ ጠባቂዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ሌላ ስልጠና መሰናዳቱንም ገልፀውልናል፡፡
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ