ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ | ምዕራፍ አስር – ክፍል ስምንት

ጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም ምዕራፍ አስር ላይ ደርሷል። ይህ ምእራፍ በእግርኳስ ታክቲክ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ካገኙ የአጨዋወት አቀራረቦች አንዱ የሆነው ካቴናቺዮን ከስር መሠረቱ ጀምሮ ያለፈባቸውን መንገዶች ይመለከታል። የዛሬው መሰናዶም ካለፈው ሳምንት የቀጠለ ነው።


በ1960ዎቹ መጨረሻ ሄሬራ ጨዋታዎችን የሚቆጣጠርባቸው መደበኛ ልማዶች እንዳዳበረ የሚያወሱ ነገርግን ማስረጃ የማይቀርብባቸው ክሶች ይወጡበት ነበር፡፡ በ1964 በአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ኢንተር ሚላንና የጀርመኑ ቦሩሺያ ዶርትሙንድ በግማሽ ፍጻሜ ከተፋለሙበት ጨዋታ በኋላ የጣልያኑ ክለብ ዳኞችን ይደልል እንደነበር የሚያጠቅሱ ወሬዎች ይናፈሱ ጀመር-በተለይ በአህጉር ዓቀፍ ውድድሮች ላይ፡፡ በመጀመሪያው ዙር ይኸው ጨዋታ በጀርመን 2-2 ተጠናቀቀ፡፡ በመልሱ ፍልሚያ ደግሞ በሳንሴሮ ኢንተሮች 2-0 መርታት ቻሉ፡፡ ጨዋታው ተጀምሮ ጥቂት ደቂቃዎች እንዳለፉ የዶርትሙንዱ ሆላንዳዊ የቀኝ መስመር አማካይ ሆፒ ኩራት በሱአሬዝ በተፈጸመበት አደገኛ አጨዋወት ከባድ ጉዳት ደርሶበት ሜዳ ለቆ ወጣ፡፡ ዩጎዝላቪያዊው የመሃል ዳኛ ብራንኮ ቴሳኒክ የኢንተሩ ተጫዋች ላይ ምንም አይነት የቅጣትም ሆነ የማስጠንቀቂያ እርምጃ አልወሰዱም፡፡ ምናልባት የአርቢትሩ ድርጊት ብዙም ሳይባልበት ታልፎ ሊሆን ቢችልም ከዚያ በኋላ በነበረው ክረምት የበዓል ቀን ሌላ ዩጎዝላቪያዊ ጎብኚ ቴሳኒክን እንዳገኘውና የበዓሉን ሙሉ ወጪ ኢንተሮች እንደሸፈኑለት ገልጾለታል፡፡

በኦስትሪያዋ ቪየና በተካሄደው የፍጻሜው ፍልሚያ ኢንተሮች ሪያል ማድሪዶችን መጋፈጥ ተጠበቀባቸው፡፡ በጨዋታው የኢንተሩ ታኚን ዴስቴፋኖ በተንቀሳቀሰበት ሁሉ በቅርብ ርቀት ሆኖ እንዲከታተለው ዝርዝር ያለ ኃላፊነት ተሰጠውና ተጫዋቹ የተነገረውን ሲተገብር ዋለ፡፡ ጉዋሪንም ፑሽካሽ እንደፈለገው እንዳይንቀሳቀስ አደረገ፡፡ ሁለቱ የሳንድሮ ማዞላ ጎሎች ደግሞ ኢንተሮች ጣፋጩን የ3-1 ድል እንዲቀዳጁ አስቻሏቸው፡፡ ቀደም ብሎ የሞናኮው አጥቂ ይቮን ዶዪስ በውድድሩ ኢንተሮች ይዘውት የቀረቡትን የአጨዋወት ዘይቤ እጅግ አማሮ ነበር፡፡ ከፍጻሜው በኋላም የማድሪዱ ሉሲያን ሙለር በጣልያኑ ክለብ የጨዋታ ዘዴ ተመሳሳይ ቅሬታውን አቀረበ፡፡ ሄሬራ የማንንም አስተያየት ከቁብ ሳይቆጥር ዋንጫውን አነሳ፡፡ 

በቀጣዩ ዓመት ኢንተር ሚላኖች በሴሪአው የተሻለ የማጥቃት ባህርይ ተላብሰው ቀረቡ፡፡ ከጠንካራው የመከላከል አጨዋወታቸው ምንም ሳያጎድሉ በውድድር ዓመቱ ስድሳ አራት ግቦች ማስቆጠር ቻሉ፡፡ በአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና በሩብ ፍጻሜው የመጀመሪያ ዙር  በአይብሮክስ ጨዋታው በተጀመረ በሰባት ደቂቃዎች ውስጥ በሬንጀርሶች ግብ ተቆጥሮባቸውም በአስደናቂ ሁኔታ 3-1 አሸነፉ፡፡ ይህ እንግዲህ ካቴናቺዮ ቅቡል እንዲሆን ከሚያስገድዱ ምክንያቶች አንዱ ነበር፡፡ በግማሽ ፍጻሜው ከሊቨርፑል ጋር ባካሄዱት ጨዋታ ግን እምብዛም አመርቂ እንቅስቃሴ አላሳዩም፡፡ በመልሱ ጨዋታ አንድ ጣልያናዊ ጋዜጠኛ ሻንክሌይን ” በፍጹም ድል እንድታደርጉ አንፈቅድላችሁም፡፡” ብሎ ዛተበት፡፡ የታየውም ይኸው ሆነ፡፡ ሊቨርፑሎች ፍልሚያውን ማሸነፍ ተስኗቸው ታዩ፡፡ በእርግጥ በመጀመሪያው ዙር ሊቨርፑሎች በአንፊልድ 3-1 ረትተው ነበር፡፡ የሁለተኛውን ዙር ጨዋታ ከማካሄዳቸው በፊት በዋዜማው ምሽት የእንግሊዙ ክለብ ተጫዋቾች ባረፉበት ሆቴል አካባቢ የተለመደው የነውጠኛ ደጋፊዎች ጩኸት ለሊቱን እረፍት ነስቷቸው አደሩ፡፡ ለነገሩ የደጋፊዎች ረብሻና ተጋጣሚ ላይ ስነ ልቦናዊ ጫና የማሳደር ድርጊቱ በአውሮፓ እግርኳስ ተደጋግሞ ቅሬታ የሚቀርብበት ጉዳይ በመሆኑ ነገሩን ከቁብ የቆጠረውም አልነበረም፡፡ ይልቁንም ጨዋታው እየተካሄደ መታየት የጀመረው
ነገር ከበስተጀርባ አንዳች የተጠነሰሰ ሴራ መኖሩን አመላካች ሆነ፡፡ ጨዋታው በተጀመረ ስምንተኛው ደቂቃ ኮርሶ የተባለው የኢንተር ተጫዋች ያገኘውን ቅጣት ምት ተገቢ ባልሆነ መንገድ ወደ ሊቨርፑሎች ግብ ላከ- ኳሳ ግብ ጠባቂውን ቶሚ ላውረንስ አልፋ መረቡ ውስጥ አረፈች፡፡ ስፔናዊው የመሃል ዳኛ ኦርቲዝ ደ ሜንደቢል ግቧን አጸደቁ፡፡ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ  የሊቨርፑሉ በረኛ የቡድን አጋሮቹ ቦታ ቦታቸውን ይዘው እስኪዘጋጁ ድረስ ክልሉ ውስጥ ሆኖ ኳሷን ሜዳው ላይ እያነጠረ ሲጠብቅ ዮአኪን ፔይሮ ቀምቶት ጎል አስቆጠረ፡፡ አሁንም ዳኛው ይህችንም ግብ አጸደቁ፡፡ ቆይቶ ፋኬቲ ሶስተኛዋን ድንቅ ጎል አከለ፡፡ ኢንተሮች 3-0 “ድል” አደረጉ፡፡     

ኋላ  ላይ ብሪያን ግላንቪል ይፋ ባወጣው ጨዋታ የማጭበርበር ቅሌት ደ ሜንደቢል ተሳታፊ ሆነው መገኘታቸውን የሚያሳይ መረጃ ወጣ፡፡ በ1974 በ<ሰንደይ ታይምስ> ጋዜጣ ላይ በቀረበው ዘገባ ጁቬንቱሶች በ1973 ከደርቢ ካውንቲ ጋር ላለባቸው የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ለተመደቡት ፖርቹጋላዊው የመሃል ዳኛ ዴዦ ሶልቲ የተባለ ሃንጋሪያዊ ግለሰብ የጣልያኑን ክለብ ይረዱ ዘንድ አምስት ሺህ የአሜሪካ ዶላርና መኪና በመደለያነት እንዳቀረበላቸው ተረጋገጠ፡፡ ግላንቪል እንደሚለው አደራዳሪው ከጁቬንቱስ ክለብ ዋና ጸሃፊ ኢታሎ አሎዲ ጀርባ የነበረ ሰው ነው፡፡ እኚህ የክለቡ አመራር አካል ደግሞ ቀድሞ በኢንተር ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ይህም በአውሮፓ ውድድሮች ላይ የሚካፈሉ የጣልያን ክለቦች በዳኞች እንዲታገዙ የሚያደርጉ አመራሮች እንደነበሩ ያሳያል፡፡ ከዚህ አንጻር በእነዚህ አመራሮች ሥር የሚያልፉ ክለቦች ተጠቃሚዎች የሆኑባቸው ዓመታት ነበሩ፡፡ አንጋፋው ጋዜጠኛ በጭምጭምታ ደረጃ ይነገሩ የነበሩ ሃሜቶችን በመከታተል እውነታው ላይ መድረስ ችሏል፡፡ እውነታው ዳኞቹ ይከፈላቸው ነበር፡፡ ሻንክሌይም ጨጓራው ሲጨስ የነበረውና መቼም ይቅር ሊል ያልፈቀደው ይህንኑ ጸያፍ ተግባር ነበር፡፡

ይቀጥላል...


ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሦስት ዓመታትም አስር መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡