ሲሳይ ዴኔቦ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?

የቀድሞው የኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን አጥቂ እና ላለፉት አምስት ዓመታት በከባድ ጉዳት ከእግር ኳሱ የተገለለው ሲሳይ ዴኔቦ አሁን በምን ሁኔታ ይገኛል?

በእግርኳስ ሕይወቱ ጅማሬ ላይ በበርካቶች ተስፋ ተጥሎበት ነበር፤ እንደተጠበቀውም ጉዳት የእግር ኳስ ሕይወቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፍ ከመጀመሩ በፊት ጥሩ ጊዜያት አሳልፏል። በወንጂ፣ ኢትዮጵያ መድን፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወልዲያ መጫወት የቻለው ሲሳይ ዴኔቦ በታዳጊ ብሄራዊ ቡድን ደረጃም የሀገሩ ማልያ ለብሶ ተጫውቷል። በኢትዮ ኤሌክትሪክ ቆይታው ከባድ ጉዳት አጋጥሞት ብዙም ሳያገለግል ከክለቡ ጋር የተለያየው ሲሳይ ከዛ በኃላ ወደ እምነት ቦታዎች በመሄድ መጠነኛ መሻሻሎች አሳይቶ ድጋሚ እግርኳስ ለመጀመር ወስኖ ለወልዲያ ቢፈርምም ከአምስት ሳምንት በኃላ ጉዳቱ በድጋሚ አገርሽቶበት ከእግር ኳስ ሙሉ ለሙሉ ለመራቅ ተገዷል።

ላለፉት ዓመታት መኪና በማጠብ ሲተዳደር የቆየው ይህ የቀድሞ አጥቂ በዚህ ወቅት ስላለበት ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ያደረገው አጭር ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ስለ ወቅታዊ የጤንነት ሁኔታው

ጤንነቴ እግዚአብሔር ይመስገን ጥሩ ነው ያለው። አልፎ አልፎ ቅዝቃዜ ሲሆን ያመኛል። ከዛ ውጭ ግን ደህና ነኝ ነው የምለው።

ስለ ህክምና ሁኔታው

ህክምና በአንዳንድ ምክንያቶች በቅርብ ክትትል እያደረግኩ አይደለም። ሳገኝ ሲሞላልኝ ግን አልፎ አልፎ እሄዳለሁ፤ ቀላል እንቅስቃሴም አደርጋለው። ባለሞያዎች ፊዝዮቴራፒ እንድከታተል እና ከቀላል እንቅስቃሴዎች እንዳልርቅ ነው የመከሩኝ። ከዛ በተጨማሪ ግን ጉዳቴ ትንሽ ከባድ ስለሆነ አሁን ባለው የሀገራችን የህክምና ደረጃ እዚ ለመታከም የሚከብድ ይመስለኛል።

ስለ ሥራው

ሥራዬን በጤና ባለሞያዎች ምክር ትቼዋለው። ሥራው ከጤናህ ጋር አይሄድም ብለውኝ በአሁኑ ሰዓት መሥራት አቁሜ ከቤተሰብ ጋር ነው ያለሁት። ዳዊት እስጢፋኖስ እና ፍፁም ገብረማርያም ካለሁበት ሁኔታ ጋር የሚሄድ ሥራ ሊያስጀምሩኝ እንቅስቃሴ ጀምረው በቂ ድጋፍ ስላላገኙ ነገሩ ተጓቷል። በቂ ድጋፍ ካገኙ ከፈጣሪ ጋር ሥራ እጀምራለው ብዬ አስባለው። የእግር ኳስ ቤተሰቡም ዳዊት እና ፍፁም ለጀመሩት ነገር ድጋፍ እንዲያደርግ እማፀናለሁ።

ሲሳይ ዴኔቦን ለመርዳት የምትፈልጉ በራሱ በሲሳይ፣ ፍፁም ገብረማርያም እና ዳዊት እስጢፋኖስ ስም በተከፈተው አካውንት ቁጥር መለገስ ትችላላችሁ፡-

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
1000278835999


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ