ሰሞኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የስፖርት ፕሮግራሞች ላይ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራህቱን ጨምሮ ሌሎችም የእግርኳስ ባለሞያዎች ከአፍሪካ ሃገራት የሚመጡና በፕሪምየር ሊጋችን የሚጫወቱ ግብ ጠባቂዎችን አስመልክተው አስተያየት ሲሰጡ ተመልክቻለው፡፡
በዘመናዊ እግርኳስ የግብ ጠባቂዎች ፋይዳ በቀላሉ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ በረኞች ለአንድ ቡድን ውጤታማነት ወይም ውድቀት ቁልፍ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ በእግርኳሳችን በተለይም በታዳጊ ፕሮጀክቶቻችን፣ በማሰልጠኛ ማዕከላት እና በክለቦች የታዳጊና ወጣት ቡድኖች ውስጥ ግብ ጠባቂነት ተገቢው ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ሆኖ አናገኘውም፡፡
የታዳጊዎቻችን ስልጠና በሁሉም መስክ ደካማ እንደሆነ የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ ችግሩን በተናጠል ስናየው ደግሞ የግብ ጠባቂዎች አያያዛችን ነገን ያላሰበ፣ የሩቁን ያልተመለከተና ትኩረት ያልተቸረው ዘርፍ መሆኑን እንመለከታለን፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚን ጨምሮ በሃገራችን የሚገኙ የግል የታዳጊ ማሰልጠኛ ማዕከላት አንዳቸውም የግብ ጠባቂ አሰልጣኞች ስለመቅጠራቸው እጠራጠራለሁ፡፡ ክለቦቻችንም ቢሆኑ አሁን-አሁን ለመዱት እንጂ ቀደም ሲል የበረኞች አሰልጣኞች አልነበሯቸውም፡፡ ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስን በመሳሰሉት አንጋፎቹ ክለቦቻችንም የታዳጊና ወጣት ቡድኖቻቸውን ግብ ጠባቂዎች የሚያሰለጥኑት የዋናው ቡድን የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኞች እንደነበሩ አስታውሳለሁ፡፡ ይህም በቋሚነት ሳይሆን አልፎ አልፎ እንደነበር አይዘነጋኝም፡፡ ለተጫዋቾች ዝውውር በርካታ ሚሊየን ብሮች የሚያፈሱት ክለቦቻችን አንድ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ለታዳጊና ወጣት ቡድኖቻቸው መቅጠር አስፈላጊ መስሎ አይታያቸውም፡፡
በሃገራችን በየክለቡ ተጫውተው ያለፉ ግብ ጠባቂዎችን ዘመናዊ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ፣ ጥሩ ክፍያ በመክፈል እና የስራ ዕድል በመፍጠር ስልጠናውን ማሳደግ እንደሚቻል ግልጽ ቢሆንም ይህን የማድረግ አዝማሚያ የሚያሳይ አመራር ልናገኝ አልቻልንም፡፡ በዚህ አሰራር ብቁ ግብ ጠባቂዎችን ማፍራት መቻላችን ታምኖበት፣ ተነሳሽነት እና ፍላጎት ታክሎበት ወደ ሥራ ሲገባ አይስተዋልም፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም ከውጭ ግብ ጠባቂዎች እንዳይመጡ ማገድ ብቻውን ሁነኛ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል ተገንዝቦ ይልቁንም በተለያዩ የሊግ እርከኖች የሚወዳደሩ ክለቦች በአቅማቸው ልክ በታዳጊና ወጣት ቡድኖቻቸው ውስጥ የግብ ጠባቂ አስልጣኞች እንዲያካትቱ አስገዳጅ ደንብ ቢያወጣ የተሻለ እድገት የሚገኝ ይመስለኛል፡፡
የእግርኳስ ማዘወተሪያ ወይም የማሰልጠኛ ማዕከላት መሰረተ ልማቶቻችንንም ስንመለከት ለግብ ጠባቂዎች ሥልጠና የተመቸ ከባቢ አለመኖሩን እንረዳለን፡፡ እንዲያው ለዓይን እንኳ የሣር ሜዳዎች ማግኘት ብርቅ በሆነበት ሁኔታ የግብ ጠባቂዎች ስልጠና የሚሰጡ ባለሙያዎችም ቢገኙ ከጥቂቶቹ በስተቀር ምቹ የሥልጠና ማካሄጃ ስለሌላቸው ተግቢውን ስልጠና ለመስጠት እጅግ ይቸገራሉ፡፡ ይህ ማነቆ ተስጥኦና ፍላጉት ያላቸው ታዳጊዎችን በስልጠናው ለመሳተፍ ፍላጎት እንዲያጡ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ ጥሩ ተጫዋቾች መሆን የሚችሉ ታዳጊዎች ፊታቸውን ወደሌላ መስክ ሲያዞሩ በርካቶቹ ደግሞ ወደቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ እንደሚታወቀው የግብ ጠባቂ ምልመላ አንዱ መስፈርት አካላዊ ቁመትን መሰረት ያደርጋል፡፡ ባለን ምቹ ያልሆነ ሜዳ እና በተላመድነው ደረጃውን ያልጠበቀ ስልጠና ለዚህ የመጫወቻ ሥፍራ የሚሆኑ ታዳጊዎችን አሳምኖ ለመመልመል በጣም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ብቁ ግብ ጠባቂዎችን የማፍራት ስልጠና በቂ ጊዜ የሚፈልግና ውስብስብ ልምምዶችን ያካተተ እንደመሆኑ ፍላጎት ያላቸውን ታዳጊዎች ቀደም ብሎ በመመልከት፣ ተፈጥሯል ክህሎታቸውን በመለየት፣ የተሻሉትን በመመልመል ተገቢውን ስልጠና መስጠት በጣም አስፈላጊ ሒደት ይሆናል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን እነዚህን ተግባሮች ለመከወን ምንም የተመቻቸ ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡
በዚህ ርዕስ ላይ ሌላ ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ ግብ ጠባቂዎች በስነ-ልቦና በጣም ጠንካራ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሃገራችን ያሉ ግብ ጠባቂዎች ደግሞ በተለይም-በታችኛው እርከን የሚገኙት በቂ ስልጠና ብቻ ሳይሆን በቂ የጨዋታ ጊዜም አያገኙም፡፡ በታዳጊዎች ውድድሮቻችን አንድ ግብ ጠባቂ በዓመት በአማካኝ ከአስር ጨዋታ በላይ የመጫወት ዕድል አይመቻችላቸውም፡፡ ይህም ተጫዋቾቹ ወደ ላይኛው እርከን ከፍ እያሉ ሲመጡ የውድድሩን፣ የአሰልጣኙን፣ የቡድን አጋሮቹን፣ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾችን፣ የደጋፊዎችን፣ የብዙሃን መገናኛዎችን እና የመሳሰሉትን የእግርኳስ ባለ ድርሻ አካላት ጫና መቋቋም እያቃተው ይመጣል፡፡ በዚህም ጠንካራ ጎናቸውን ማሳደግና ስህተታቸውን ማረም ተስኖአቸው እምቅ አቅም እያላቸው ብዙም ሳያገለግሉ ከእግርኳስ ይገለላሉ፡፡
ምንም እንኳን በየትኛውም እርከን ላይ ያሉ ግብ ጠባቂዎችን የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ማሰልጠን እንዳለበት ብስማማም ያን ማድረግ ካልተቻለ የሜዳ ላይ ተጫዋቾችን የሚያሰለጥነው ዋናው አሰልጣኝ አልያም ረዳት አሰልጣኝ መሰረታዊውን የግብ ጠባቂ ስልጠና መረዳት እንዲችሉ የሚያግዝ በአማርኛ ቋንቋ በራሳችን አንጋፋ የእግርኳሱ ባለሙያዎች የተዘጋጀ የማሰልጠኛ መመሪያ አለመኖሩም ሌላኛው ችግር ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ዓይነት ግብዓት አለመኖሩ በታዳጊና ወጣት ቡድኖች ላይ የሚሰሩ የሃገራችን አሰልጣኞች በግብ ጠባቂ ስልጠና እና ዝግጅት ላይ በቂና መጣኝ እውቀት እንዳይኖራቸው አድርጓል፡፡ በሌላ በኩል አሁን በስራ ላይ ያሉ አሰልጣኞችም ቢሆኑ በዚህ መስክ እራሳቸውን ለማሳደግ ሲቸገሩ እያየን ነው ፡፡
በታዳጊዎች የግብ ጠባቂ ስልጠና ላይ ችግር ተደርጎ ሊነሳ የሚችለው ሌላው ነገር የምልመላ ጉዳይ ነው፡፡ በአብዛኛው በታዳጊ ፕሮጀክት ለግብ ጠባቂነት የምንመርጣቸው ተጫዋቾ ለቦታው ካለን ዝቅተኛ ገምት የተነሳ በእግር በመጫወት ምቾት የማይሰማቸውን ነው፡፡ በዚህም ተጫዋቹ እያደገ ሲሄድና በሙሉ ሜዳ ጨዋታዎች መሳተፍ ሲጀምር በእግሩ ለመጫወት የሚፈራና ምቾት የማይሰማው ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ሁሉም ባይሆኑም አንዳንዶቹ አካላዊ ቁመትንም ለምልመላ መሰረት ሲያደርጉ አይታይም፡፡
በአጠቃላይ ግብ ጠባቂነት በኢትዮጵያ እግርኳስ ትኩረት የተነፈገው ዘርፍ ነው፡፡ ሲያጠፋ ከመውቀስ ውጪ ተገቢውን ምስጋናና ክብር ሲያገኙ አይሰተዋልም፡፡ ወቀሳው ደግሞ በዋናው ብሔራዊ ቡድናችንም ጭምር የተስተዋለ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ (አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ብሔራዊ ቡድኑን በያዙበት ወቅት በአቤል ማሞ ላይ በሚዲያ ያቀረቡት ትችት አይዘነጋም፡፡) እንደዚህ ዓይነት በብዙሃን መገናኛዎች ግብ ጠባቂዎቻችን ላይ የሚቀርበው ቅጣ ያጣ ወቀሳና አንገት የሚያስደፋ ትችት ታዳጊዎች ተግተው እንዲሰሩ የሚያበረታታ አይደለም፡፡ ግብ ጠባቂነት የተለያዩ የሥልጠና ዘዴዎችን መጠቀም የሚያስፈልገው ዘርፍ ነው፡፡በእግርኳሳችን ታዳጊ በረኞችን በቀላሉ ወደኋላ ሔደው በቋሚዎቹ መካከል የማቆም ትዕዛዝ መስጠት ብቻ ሳይሆን የቡድን አባልነት ስሜት እንዲሰማቸውና በሙሉ ቡድኑ ዝግጅት ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም በታዳጊና ወጣት ቡድኖች ግብ ጠባቂዎች የቡድን አባል እስካይመስሉ ድረስ ይዘነጋሉ፡፡ ይህን አጉል ባሕል ማስቀረት የቻልን አልመሰለኝም፤ ይህም ሌላኛው የዘርፉ ተግዳሮታችን ነው፡፡
እነዚህና ሌሎችንም ችግሮቻችን ሳንፈታ የውጪዎቹን ግብ ጠባቂዎች በማስቀረት ብቻ “የብቁ ግብ ጠባቂዎች ጉድለታችንን እንፈታለን፤ ውጤታማ ግብ ጠባቂዎችንም እናፈራለን፡፡” ብሎ ማሰብ “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” እንደሚባለው ከንቱ ድካም ነው፡፡ በእርግጥ ከውጪ ሃገራት የሚመጡ ግብ ጠባቂዎችን ማስቀረት ጠቃሚ ስለመሆኑ ባምንበትም ምርጦቹን ግብ ጠባቂዎች ለማፍራት ግን ምንም የተለየ ስራ በእግርኳሳችን ላይ እየተሰራ እንዳልሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡
ስለ ፀሐፊው
የአስተያየቱ ፀሐፊ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል ፡፡ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፅዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ