አጭር በሆነው የእግርኳስ ዘመናቸው እጅግ ከተዋጣላቸው የዘጠናዎቹ ስኬታማ ተጫዋቾች መካከል የሚመደበው እና ያለውን አቅም ሁሉ ሜዳ ውስጥ በመስጠት የሚታወቀው የኃላ ደጀን ከፍያለው ተስፋዬ (ዲላ) ማነው?
ጣዕም ባለው የቡና ምርቷ ብቻ ትታወቅ የነበረችው የዲላ ከተማ በሌላ ዘርፍ የከተማዋን ስም የሚያስጠሩ የእግርኳሱ አብዮተኛ ትውልድ ተፈጥረዋል። ለአብነት ያህል ገብረክርስቶስ ቢራራ፣ ቶሬ ማሞ፣ እዮቤ፣ ዮናስ ተፈራ፣ ሁሴን አብደላ፣ ጀማል አብደላ ይጠቀሳሉ። እነዚህን ስመጥር ተጫዋቾችን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እየተመለከተ በእነርሱ እየተሳበ ከፍያለው ተስፋዬ ወደ እግርኳሱ ብቅ ማለት ጀመረ።
ተወልዶ ባደገበት ዲላ ከተማ የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው ከፍያለው በትምህርት ቤቶች ጨዋታ በአጥቂ ሥፍራ ላይ ባሳየው መልካም እንቅስቃሴ የደቡብ ክልልን በመወከል ለውድድር አዲስ አበባ ይመጣል። በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት በወቅቱ ለነበሩት ለበርካታ ድንቅ ተጫዋቾች መፈጠር እንደ ድልድይ (ምክንያት) በመሆን የሚታወቁት አመለ ሸጋው የሙያ አባት ጋሽ ታደሰም ከፍያለው ዲላ ሲጫወት ያገኙትና በእንቅስቃሴው ተደንቀው ለቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲጫወት ይጠይቁታል። ሆኖም ልጅነት ስለነበረ በወቅቱም በክለብ ለመጫወት ምንም ዓይነት ሀሳብ ስላልነበረው ወደ ዲላ አምርቷል።
ለአንድ ዓመት ያህል ለዲላ ከተማ የተጫወተው ከፍያለው ሁልጊዜም ቢሆን የስልክ ጥሪ ይደርሰው ነበር። ‘አዲስ አበባ ና ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫወት’ የሚል። ከብዙ ጉትጎታ በኋላ ከፍያለው ለቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን ለሙከራ በ1989 መጥቶ የተሳካ ሙከራ በማድረግ የ”ቢ” ቡድን አባል ሆነ። ለሁለት ዓመት በታዳጊ ቡድን ውስጥ ሲጫወት ቆይቶ በ1991 ወደ ዋናው ቡድን መቀላቀል የቻለው ከፍያለው አስቀድሞ በተስፋ ቡድን ውስጥ በአጥቂ ቦታ ይጫወት የነበረ ቢሆንም በወቅቱ የተስፋ ቡድኑ አሰልጣኝ የነበሩት ሥዩም ከበደ በተከላካይ ቦታ የሚጫወቱ ልጆች በመቅረታቸው የተነሳ ቦታውን ለመሸፈን አስበው ከፍያለውን ወደኋላ መልሰው አጫውተውት በዛው ቦታው ሆኖ እንደቀረ ይነገራል።
አንድ ለአንድ ለማለፍ አዳጋች የሆነ፣ የሚያቋርጡ ኳሶችን አጠገቡ ካሉ ተከላካዮች ፈጥኖ በመሄድ የመንጠቅ የማቋረጥ እና የመቆጣጠር አቅም የነበረው ተጫዋች እንደነበረ የሚነገርለት ከፍያለው በፈረሰኞቹ ቤት አገልግሎቱ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ማንሳት ችሏል። ከፍያለውን ወደ ዋናው ቡድን እንዲያድግ በማድረግ ትልቁን ሚና የተወጡት አሰልጣኝ ጋሽ አሥራት ኃይሌ ስለ ዲላ ሲናገሩ “ዲላ ለኔ አንበሳ የሆነ ተጫዋች ነው። ፍጥነቱ፣ እልሁ፣ ድፍረቱ እና የሚሰጠውን የሚቀበል ተጫዋች ነው። ሜዳ ውስጥ ሁሉን ነገር የሚያደርግ፣ ስፖርታዊ ዲሲፕሊን ያለው፣ ለሙያው ታማኝ የሆነ ተጫዋች ነው። እኔ ቅዱስ ጊዮርጊስ እስከ ነበርኩበት ጊዜ ድረስ የነበረው የመጫወት ፍላጎቱ ፣ ታዛዥነቱ የተለየ ተጫዋች ነበር።” ይላሉ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከታዳጊ እስከ ዋናው ቡድን የተጫወተው ከፍያለው ተስፋዬ በተለይ አርጀንቲና በተካሄደው የዓለም ወጣቶች ዋንጫ ላይ በምድቡ ከተካሄዱ ሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ ሲጫወት፣ በመጀመርያው ጨዋታ ቀይ ካርድ መመልከቱ ይታወቃል። ወደ ቤልጅየም ሀገር በማቅናትም ለአስራ አንድ ወራት ያህል ሙከራ እያደረገ ባለበት ወቅት በአቶ አብነት ገብረመስቀል ጥሪ በድጋሚ በ1996 ፈረሰኞችን ተቀላቅሏል።
ብዙ መጫወት የሚችልበት አቅሙ እያለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወንጂ ስኳር ጋር በነበረው የአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታ ባጋጠመው የጉልበት ጉዳት ምክንያት ለወራት ከሜዳ ቢርቅም ዳግመኛ በቅዱስ ጊዮርጊስ የመጫወት እድል በማጣቱ ወደ ሐረር ቢራ በማምራት ከተጫወተ በኃላ በ1998 ራሱን ከእግርኳስ ዓለም አገልግሏል።
በታዳጊነት እድሜው ያሰለጥኑት የነበሩት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ስለ ከፍያለው ሲናገሩ “ቴክኒካል የሆነ፣ በመስመር የሚጫወት፣ ፈጣን፣ ድሪብል አድርጎ ወደ ፊት የሚሄድ አጥቂ ነበር። ከመስመር የሚያሻግራቸው ኳሶቹ በጣም ትክክለኛ የነበሩ፣ በሁሉ ነገሩ የተሟላ ተጫዋች ነበር። ከፍያለው ለቡድኑ ያለውን አቅም ሁሉ አውጥቶ የሚጫወት ተጫዋች ነው። ሜዳ ውስጥ አደጋ፣ ጉዳት አይልም ቡድኑ አሸንፎ እንዲወጣ ሁሉን ነገር የሚሰጥ ነው። ይሄም ነው ለጉዳት ዳርጎት ብዙ እንዳይጫወት ያደረገው። ሜዳ ላይ ጉዳት ቢያጋጥመው እንኳ ቶሎ ብሎ ተነስቶ የሚጫወት ነው። ይህ የሚያሳየው ለቡድኑ ያለውን ፍቅር የሚያሳይ ነው።” በማለት ይናገራሉ።
በአሁኑ ወቅት በግል የንግድ ሥራ ላይ የሚገኘው የዘጠናዎቹ ድንቅ ተከላካይ ከፍያለው ተስፋዬ (ዲላ) ከረጅም ዓመት በኃላ ሶከር ኢትዮጵያ ከብዙ ጥረት በኃላ አግኝታው ተከታዩን ሀሳብ አጋርቶናል።
“በእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመኔ የማስበውን ሁሎ ሆኛለው ማለት ይከብደኛል። ሆኖም ግን በጉዳት ከእግርኳስ እስከተገለልኩበት ጊዜ ድረስ ለምወደው ክለቤ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ለሀገሬ የምችለውን ሁሉ ሜዳ ውስጥ አድርጌአለው። በዚህ ስኬታማ እንደሆንኩ አስባለው። ያው መጨረሻ ላይ ስሜቴ ተጎድቶ ከእግርኳስ ህይወት ብወጣም። በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ማውራትም ሆነ ማሰብ አልፈልግም።
” ቅዱስ ጊዮርጊስ ለሙከራ ስመጣ አጥቂ ሆኜ ለመጫወት ነበር። ሙከራውንም ያለፍኩት በአጥቂ ቦታ ነው። “ቢ” ቡድን እየተጫወትኩ አብዛኛውን ጊዜ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ነበርኩ። አጋጣሚ ሆኖ አንድ ቀን ጃን ሜዳ ጨዋታ ኖሮን በተከላካይ ቦታ የሚጫወቱት ተጫዋቾች ያረፍዳሉ። አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ‘ከኋላ ዲላ ተከላካይ ሆነህ ዛሬ ትጫወታለህ’ ብሎ መከረኝ። እኔ ደግሞ በወቅቱ የመጫወት ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረኝ አሰልጣኙ ያለኝን አደረኩ። ጥሩ ተንቀሳቀስኩ መሰለኝ በዛው ተከላካይ ሆኜ ቀረሁ። አሰልጣኝ አሥራት ኃይሌም ይሄን ሰማና አጨዋወቴንም ወደደው። በዋናው ቡድን ሲጫውተኝ ተከላካይ አድርጎ አጫወተኝ። ለመጫወት ካለኝ ከፍተኛ ፍላጎት እና አሰልጣኞቼ የሚሉኝን የመስማት ግዴታ አለብኝ። በኃላ ላይ ተጎድቼ እግርኳስን ሳቆምኩነት ጊዜ ድረስ ተከላካይ ሆንኩኝ።
“አጥቂ ሆኜ ብጫወት ይሻል እንደነበረ በኃላ ነው የገባኝ። የሚገርምህ ጋሽ መንግሥቱ ወርቁ ነፍሱን ይማረውና ለሴካፋ የክለብ ዋንጫ ኬንያ ሄደን ያለውን አስታውሳለሁ። ‘ከፍያለውን ተከላካይ አድርጎ ማጫወት ተገቢ አይደለም። አጥቂ ነው መሆን ያለበት። የግንባር ኳስ ይችላል፣ ፈጣን ነው፣ ቴክኒካል ክህሎቱ ጥሩ ነው። እንዴት ነው ይሄንን ኃይል አምቆ ይዞ ከኋላ የሚጫወተው ብሎ ሀሳብ ያቀርባል። ሆኖም ሀሳቡን ሳይቀበሉ ቀርተዋል። በኋላ እኔ ስረዳ የመንግሥቱ ሀሳብ ትክክል እንደሆነ ነው የገባኝ። እኔ አጥቂ ቦታ ሆኜ ብጫወት የተሻለ ነገር አሳይ ነበር። ረጅም ዓመት የመጫወት አቅሙ ይኖረኝ ነበር። ምክንያቱም በጊዜ ከእግርኳስ እንድርቅ ምክንያት የሆነኝ በተከላካይ ቦታ ሆኜ መጫወቴ ነው።
“የአርጄንቲና የዓለም ዋንጫ ትልቅ ለውጥ የምናመጣበት እንደሆነ እገምት ነበር። ወቅቱ ጥሩ ነበር። ፌዴሬሽኑም ረዘም ላለ ጊዜ ዝግጅት እንድናደርግ ፈቅዶ ነበር። በጣም ጥሩ ጥሩ ልጆች ነበሩ። አሰልጣኝ ጋርዝያቶም ጥሩ አሰልጣኝ ነበር። ተጫዋች ብቻ ሆኜ መቅረትን ሳይሆን አሰልጣኝ እንድሆን ጭምር ጭንቅላቴን ቀርፆት የነበረ አሪፍ አሰልጣኝ ነበር። ምንም እንኳን ውጤቱ ጥሩ የማይባል ቢሆንም አሰልጣኝ ጋርዚያቶ ከዛ በኋላ ቢቆይ ኖሮ ብዙ መሠረታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ አስባለው። ጊዜ ሊሰጠው ይገባ ነበር። ለአሰልጣኝ ጊዜ ካልተሰጠ በአንዴ ዋንጫ እንዲያመጣ ከተፈለገ አስቸጋሪ ነው። ከአሰልጣኝ ጋርዝያቶ ጋር በመሆን አርጄንቲና የነበረን ቆይታ በጣም አሪፍ ነበር። በደንብ ተዘጋጅተንበት ነበር። ሆኖም በመሀከላችን ብዙ ክፍተት እንዲኖር የፈለጉ ብዙ ሰዎች ስለነበሩ እና ኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ ያሰልጥን በሚል ተጫዋቾቹን ከፋፍለው ስለነበረ ሀሳባችን ሳይሳካ ቀርቷል።
“ቤልጄም ወደ አስራ አንድ ወራት ያህል ቆይቻለው። በታዳጊ የአፍሪካ ዋንጫ እና በዓለም ዋንጫ ላይ ባሳየሁት ጥሩ እንቅስቃሴ ነበር ለሙከራ የሄድኩት። ያው ኑሮውን ለመልመድ ትንሽ ብቸገርም የተሳካ የሙከራ ጊዜ እያደረኩ ባለበት ወቅት ቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ እጥረት ያጋጠመዋል መሰለኝ ጋሽ አብነት ገብረመስቀል ደውለውልኝ መጥቼ እንድጫወት ጠየቁኝ። ጥሪውን አክብሬም ወደ አዲስ አበባ መጣሁ። ለአንድ ወር ያህል ትንሽ አየሩን እስክለመድ ትንሽ ተቸግሬ ነበር። በኃላ ወደ ትክከኛው እንቅስቃሴ ስገባ አስታውሳለው ከወንጂ ስኳር ጋር የመጀመርያ ጨዋታዬን ለማድረግ ወደ ሜዳ ገብቼ እየተጫወትኩ ሳለው በካታንጋ አቅጣጫ እግሬ የማይሆን ቦታ አረፈ እና ጉልበቴ ተናግቶ ከፍተኛ ጉዳት ያስተናገድኩት።
” የጉዳቴ ሁኔታ ትንሽ ከበድ ያለ በመሆኑ ለአንድ ዓመት ከሜዳ አርቆኛል። በወቅቱ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት አለመግባባት ተፈጥሮ ስለነበረ በቂ ህክምና ሊሰጠኝ አልቻለም። ጊዮርጊስ እንደሚታወቀው የቲፎዞ ቤት ነው። ቲፎዞ ያላቸው ልጆች ህክምና ያገኛሉ። ለእነርሱ ጥሩ አመለካከት ከሌለህ ህክምናውን ልታገኝ አትችልም። በኋላ በደጋፊዎች ጩኸት ነው ወደ ህክምናው እንድሄድ የተደረገው። ህክምናዬን ጨርሼ ለመጫወት ስመለስ የሚገርምህ ሊያዩኝ እና ሊሞክሩኝ እንኳን አልቻሉም። እኔም እግርኳስን አቁሜ ባለሁበት ሰዓት ሐረሮች እንድጫወት ጠየቁኝ። እዛም ሄጄ ለዘጠኝ ወራት በቋሚ ተሰላፊነት እና በአንበልነት ቡድኑን እየመራው ተጫወትኩ። ሐረርም የሄድኩት በእልህ፣ እንዳይቆጨኝ መጫወት እንደምችል ለእነርሱ ለማሳየት ነበር። መጫወት እንደምችል አሳይቼ እግርኳስን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በምንም መንገድ ዞር ብዬ ላለማየት ወስኜ ጫማ በመስቀል ወደ ሌላ ሥራ ገባሁ።
“አሁን የምገኝበት ሁኔታ ከዲላ ከተማ እስከ ቡሌ ሆራ (ቀድሞ አጠራሯ ሀገረ ማርያም) ድረሰ የዳሽን ቢራ ወኪል ነኝ። ሌላው የራሴ የሆቴል የኮንስትራክሽን ግንባታ ነው ያለሁት። ፈጣሪ ይመስገን።
“በእግርኳስ ህይወቴ በጣም የምቆጭበት ነገር ከኢትዮጵያ ውጭ የመጫወት ከፍተኛ ፍላጎት ነበርኝ። ውስጤም ወጥቼ የመጫወት አቅም እንዳለኝ ይነግረኝ ነበር። ደግሞም ይቻል ነበር። እኔ በግሌ ይህን ለማሳካት እጥር ነበር። ከልቤ ነው የምጫወተው፣ አሰልጣኝ የሚለኝን በጣም ነው የምሰማው። ጋርዝያቶ ይወደዋል ሲባል፣ አሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ ሲወደኝ ዝም ብሎ አይደለም የሚወዱኝ አሰልጣኞቼ የሚሉኝን አክብሬ ሜዳ ላይ ስለምተገብር ነው። ቤልጅየም ሆኜ መቀጠል እፈልግ ነበር። ሆኖም እዚህ ጋር ጋሽ አብነት ሲጠራህ ትጓጓለህ እጅግ የማከብረው፣ ትልቅ ሰው ነው የጠራኝ። እንዲሁም የተሻለ ነገር ሲያቀርብልህ እዛ ደግሞ ትንሽ ኑሮ እየከበደ መጥቶ ስለነበር ወደ ሀገሬ ተመልሼ መጣው እንጂ በዛው ታግዬ ብቀጥል ኖሮ ወደ ኳሱ ህይወት ላደላ እችል ነበር። በኃላ የሚሆነውን ፈጣሪ ነበር የሚያቀው።
” የኢትዮጵያ እግርኳስን ፈፅሞ አልከታተልም። ምክንያቱም በእግርኳስ ህይወቴ ጊዮርጊሶች በጣም ነው የጎዱኝ። ምክንያቱም በዛን ዘመን የነበርን ተጫዋቾች የገንዘብ ተጠቃሚ አልነበርንም። ከፍተኛ የሆነ የማልያ ፍቅር ነበረን። ዝም ብለህ ስታይ ብርሃኑ (ፈየራ)፣ አሸናፊ ሲሳይ፣ ፀጋዬ ባቲ፣ ጌትነት ሞት ባይኖር፣ ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ፣ ታዲዮስ ጌታቸው፣ ተስፋዬ ኡርጌቾ እያንዳንዱ ተጫዋቾች ስማቸውን የጠራሁልህ እና ሌሎችም የሚገባን ክብር አልተሰጠንም፤ ትዝም ያለው ሰውም የለም። ትዝ ሲለኝ ስሜቴ ይረበሻል። ያው ሁሉም አልፎ በፈጣሪ ፍቃድ እዚህ ደርሰናል። ለወደፊት ግን ጊዮርጊስ ባለ ውለታዎቹን ማክበር አለበት የሚል መልዕክት አስተላልፋለሁ።
“በቤተሰብ ህይወቴ ባለ ትዳር ነኝ የአንድ ሴት እና የሁለት ወንድ ልጆች አባት ነኝ። የመጀመርያው ወንድ ልጄ ከፍተኛ የሆነ የእግርኳስ ፍቅር አለው። እግርኳስ ይወዳል። አንዳንዴ አብሬው ለመጫወት እሞክራለው። ወደ ፊት እግርኳስ ተጫዋች እንዲሆን እቅድ አለኝ።
” በመጨረሻም ማመስገን የምፈልጋቸው አካላት አሉ። የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች፣ ለኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ትልቅ ክብር ነው ያለኝ። የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች ብሆንም ለቡና ደጋፊዎች ትልቅ አድናቆት አለኝ። ምክንያቱም ጊዮርጊስ ያለ ቡና፣ ቡና ያለ ጊዮርጊስ ባዶ ነው። በዚህ አጋጣሚ የሁለቱም ደጋፊዎች ለኔ ትልቅ አክብሮት ያላቸው በመሆኑ በጣም ነው የማከብራቸው። ለጋሽ ታዴ ትልቅ ክብር አለኝ። አዲስ አበባ መጥቼ እጫወታለው የሚል ሀሳብ አልነበረኝም። በእርሳቸው ትልቅ ልፋት ነው እዚህ የደረስኩት፤ በጣም አመሰግናለው። ደሳለኝ ገብረ ጊዮርጊስ በጣም የማከብረው ሰው ነው። ተጫዋቾች አንድ ነገር ሆኑ ሲባል ፈጥኖ በመድረስ በማስተባበር የሚያደርገው ነገር በጣም እንዳከብረው አድርጎኛል። እናተም አክብራችሁ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለው።
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!