ዕለተ ሀሙስ በምናቀርበው “ይህንን ያውቁ ኖሯል?” አምዳችን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን የተመለከቱ እውነታዎቸን በተከታታይ ወደ እናንተ ስናደርስ ሰንብተናል። በዛሬው የክፍል 10 ጥንክራችንም ሊጉን እና ኮከቦችን የተመለከቱ እውነታዎችን አዘጋጅተን ቀርበናል።
1- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በ1990 በአዲስ መልክ እና መዋቅር እንደተጀመረ ይታወቃል። በዚህም ዓመት የመጀመሪያው ኮከብ ተብሎ የተመረጠው ተጫዋች አንዋር ያሲን ነው። ተጫዋቹ በመብራት ኃይል ባሳለፈው ድንቅ ጊዜ ነበር ኮከብ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠው። ከአንዋር በተጨማሪ በኢትዮጵያ መድን የነበረው ሀሰን በሽር 9 ግቦችን አስቆጥሮ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተብሎ ተሸልሟል።
2- በሊጉ ታሪክ በርካታ ጊዜ ኮከብ ተጫዋች ተብለው የተመረጡ ተጫዋቾች 3 ናቸው። እነሱም አሸናፊ ግርማ (1993 እና 1994 በኢትዮጵያ ቡና)፣ ጌታነህ ከበደ (2001 እና 2005 በደቡብ ፖሊስና ደደቢት) እንዲሁም አስቻለው ታመነ (2008 እና 2009 በቅዱስ ጊዮርጊስ) ናቸው።
3- ከ1990 በፊት በነበረው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና እና ከ1990 በኋላ እየተደረገ ባለው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ክብሮችን ያገኘው ብቸኛ ተጫዋች የቀድሞው የኤሌክትሪክ ጠንካራ ተከላካይ አንዋር ሲራጅ ነው። አንዋር በ1989 የኮከብነትን ክብር ካገኘ በኋላ በአዲሱ የሊጉ ቅርፅም በ1992 ሽልማቱን በድጋሚ የግሉ አድርጓል።
4- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠ የውጪ ዜጋ ተጫዋች የለም።
5- የኮከብ ተጫዋችነት ሽልማት ብዙ ጊዜ እንደ ማካካሻነት ይወሰዳል የሚል ቅሬታ ሲነሳበት ይሰማል። በተለይ ከ90’ዎቹ እስከ 2000ዎቹ አጋማሽ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ካላጠናቀቀ ወይም ቡድኑ ሻምፒዮን ካልሆነ ክለብ እንደ ማፅናኛ ተጫዋች ተመርጦ ሽልማቱ ይሰጣል በሚል በወቅቱ ጋዜጦች እና ተመልካቾች ትችት ሲሰነዘርበት ይሰማል ።
6- በሊጉ ታሪክ ብቸኛው ኮከብ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠው ግብ ጠባቂ ጀማል ጣሰው ነው። ጀማል በ2002 በደደቢት ማሊያ ባሳየው ድንቅ ብቃት ነበር የኮከብ ተጫዋችነትን ክብር በግብ ጠባቂነት ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ ያገኘው።
7- በመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት በስታዲየም ውስጥ ብቻ በሚኖር ፕሮግራም ሲሰጥ የነበረው ይህ የኮከቦች ሽልማት ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ከተለምዷዊው አሰራር ወጥቶ በሆቴል በሚዘጋጅ “የተሻለ” መርሐ-ግብር ለተጫዋቾቹ ሽልማቱን መስጠት ተጀምሯል።
8- በ22 ዓመት የሊጉ ጉዞ 16 ተጫዋቾች ኮከብ ተጫዋች ተብለው ከተለያዩ ክለቦች ተመርጠዋል። ከእነዚህ 16 ተጫዋቾች ውስጥ አንድ ግብ ጠባቂ (ጀማል ጣሰው) አራቱ ተከላካዮች (አንዋር ሲራጅ፣ ደጉ ደበበ፣ አስቻለው ታመነ እና አብዱልከሪም መሐመድ)፣ ሥድስቱ አማካዮች (አንዋር ያሲን፣ አሸናፊ ግርማ ፣ ሙሉዓለም ረጋሳ፣ ሙሉጌታ ምህረት፣ በኃይሉ አሰፋ እና ሱራፌል ዳኛቸው) እንዲሁም በተመሳሳይ ሥድስት አጥቂዎች (አህመድ ጁንዲ፣ ቢኒያም አሰፋ፣ ታፈሰ ተስፋዬ፣ ጌታነህ ከበደ፣ አዳነ ግርማ እና ዑመድ ኡኩሪ) ነበሩ።
9- ከተሰረዘው የዘንድሮ የውድድር ዘመን ውጪ የኮከብ አሰልጣኝ፣ ኮከብ ተጫዋች እና ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሽልማት ያልተሰጠበት ብቸኛ ዓመት 1999 ነው። በዚህ ዓመት ክለቦች እና የውድድር አዘጋጁ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በገቡበት ሰጣ ገባ የሊጉ መርሐ-ግብር በተያዘለት መልክ ሳይከናወን መቅረቱ ይታወሳል። እርግጥ በዓመቱ የሊጉ አሸናፊ እንዲኖር ቢደረግም የኮከቦች ሽልማት ግን በወቅቱ ሳይኖር ቀርቷል።
10- እስካሁን ባለው የሊጉ ታሪክ ለበርካታ ጊዜያት ተጫዋቾችን በኮከብነት ያስመረጠው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው። ክለቡ እስካሁን በተለያዩ 10 ጊዜያት 8 ተጫዋቾችን አስመርጧል። ደጉ ደበበ*2፣ አስቻለው ታመነ*2፣ ዑመድ ኡኩሪ፣ አዳነ ግርማ፣ ቢኒያም አሰፋ፣ በኃይሉ አሰፋ፣ አብዱልከሪም መሐመድ እና ሙሉዓለም ረጋሳ በቅዱስ ጊዮርጊስ ማልያ ኮከብ ተጫዋችነት ክብርን ያሳኩ ናቸው።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ