ክለቦች ከተጫዋቾች ጋር እያደረጓቸው ያሉት የቅጥር ስምምነቶች ምን ያህል ከፌዴሬሽኑ አዲስ ረቂቅ ደንብ ጋር ይጣጣማሉ ? የሚለውን ጥያቄ ለፌዴሬሽኑ ሕዝብ ግንኙነት አቶ ባህሩ ጥላሁን አቅርበን ምላሾችን አግኝተናል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አጠቃላይ የተጫዋቾች ዝውውርን በተመለከተ በቅርቡ ያወጣውን ረቂቅ ደንብ ለውይይት አቅርቦ ለማፀደቅ በሒደት ላይ ይገኛል። አዲሱ ደንብ በግብ ጠባቂዎች፣ በውጪ ሀገር ተጫዋቾች ቁጥር፣ በወጣት ተጫዋቾች አጠቃቀም እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ አዳዲስ ነጥቦች የተንፀባረቁበት ከመሆኑ አንፃር የእስካሁን የዝውውር መንገድ ሊቀይር ይችላል ተብሎ ይጠበቃል። ነገር ግን የደንቡ ጉዳይ ሳይለይለት ክለቦች ከተጫዋቾች ጋር እየተስማሙ ያሉበት መንገድ በኋላ ላይ ከደንቡ ጋር የሚጋጩ ሆነው ንትርኮችን እንዳያስነሱ ያሰጋል።
“አሁን ክለቦች እያስፈረሙ ያሉት በፌዴሬሽኑ እውቅና የለውም። እኛ ጋር ግን አንዴ ከፀደቀ ተጫዋቾቹ ወደ የትም አይነቀሳቀሱም። ስለዚህ እኛ በአዲሱ የዝውውር መመሪያ መሠረት በቀጣይ በምናፀድቀው መሠረት ክለቦች በጠቅላላ በሚግባቡበት መንገድ ነው ዝውውሩን የምናፀድቀው፡፡” የሚሉት የፌዴሬሽኑ ህዝብ ግንኙነት አቶ ባህሩ ጥላሁን ግን ገና ያልፀደቀውን ደንብ ፌዴሬሽኑ ለክለቦች ቢልክም በቂ ምላሽ ያላገኘ መሆኑን ያስረዳሉ።
“ከአንደኛ ሊግ ጀምሮ እስከ ፕሪምየር ሊግ ድረስ ላሉ ክለቦች በጠቅላላ የዝውውር መመሪያ ደንብ ድራፍት ልከናል። በቀጣይ ወደ ዝውውር መስኮቱ ሲገባ ክለቦች በየትኛው መመሪያ ይስተናገዳሉ የሚለውን እንዲያውቁ ፣ አዲሱ መመሪያ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ እና እንዲተቹ ፣ በኃላ ላይ እኛ ምንም ሀሳብ አልሰጠንም እንዳይሉ የክለቦች ተሳትፎ አንዲኖረው ተብሎ ተልኳል። እስከ ነሀሴ 7 ድረስ አስተያየታችሁን ላኩ ብለን የተሰጡትን አስተያየቶችን መቀመር ላይ ነን። ነገር ግን የመጡትም ምላሾች በሚፈለገው ልክ ከሁሉም ክለቦች አይደለም። እኛ ግን ለእያንዳንዱ ክለብ ልከናል ፤ ያልደረሰው ክለብ የለም። በኢ-ሜይል ከዛም ደግሞ በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት በፈጣን መልዕክት ለእያንዳንዱ ክለብ በሀርድ ኮፒ እንዲደርሳቸውም አድርገናል። እንዳረጋገጥነውም ሁሉም ደርሷቸዋል፡፡ ስለዚህ በላክነው ልክ ደግሞ ግብዓት እንፈልጋለን። አሁን የተቀመረውን ሀሳብ እንይዝና በቅርቡ አንድ መድረክ ይኖራል፡፡ በዚህ መሠረት ነው በቀጣይ የሚስተናገዱት የሚለውን ይዘን እንቀርባለን። የሥራ አስፈፃሚውም እንዲያፀድቀው ይደረጋል። ከፀደቀ በኃላ ግን አሁን ክለቦች ሪስክ እየወሰዱ ነው ያሉት። እያስፈረሙ ያሉት ኃላፊነት ወስደው ነው። የሚመጣውንም ዳፋ የመቀበል ግዴታ አለባቸው ማለት ነው፡፡ ሪስክ ካለው መጀመሪያ መጠንቀቅ አለባቸው ብዬ ነው የማስበው እና የዝውውር መስኮቱ ሲከፈት የምናስተናግደው በአዲሱ የዝውውር መመሪያ መሠረት ነው፡፡”
አቶ ባህሩ የውጪ ግብ ጠባቂዎችን መጠቀም የሚከለክለው የረቂቅ ደንቡ ሀሳብ ላይ ያላቸውን አስተያየት ሲሰጡም ” ቅድም ባልኩት መሠረት በቀጣይ በሚኖረን መድረክ ክለቦችም አስተያየት ይሰጡበታል፡፡ የሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂ ገበያው ላይ አለ ወይ ? የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል። በዚህ ሀሳብ መስጠት ማንሳት ያለባቸው ክለቦቹ ናቸው። ” ብለዋል።
በመጨረሻም ጠቅላላ ጉባዔውን መስከረም ወይም ጥቅምት ላይ ለማድረግ የታሰበ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ባህሩ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የመንግስት ቀጣይ ውሳኔን እንደሚጠብቁ አስረድተው ጉዳዩ በሥራ አስፈፃሚው ሊታይ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተው ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀዋል። ” አንዳንድ አስቸኳይ ጉዳዮች ሲኖሩ ሥራ አስፈፃሚው የማፅደቅ መብት አለው። ሆኖም ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ሂደቱን መጠበቅ አለበት። ክለቦችን አወያይቶ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የዝውውር ደንቡን ማፅደቅ ይችላል፡፡”
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!