ለኢትዮጵያ መድን፣ ደቡብ ፖሊስ፣ ኦሜድላ እና ለብሔራዊ ቡድኑ በግብጠባቂነት ያገለገለው ይልማ ከበደ (ጃሬ) የስፖርት ቤተሰቡን ድጋፍ ጠይቋል።
ከ1974-1996 ድረስ ለሃያ አራት ዓመታት በኢትዮጵያ እግርኳስ የግብጠባቂዎች ታሪክ ትልቅ አበርክቶ የነበረው ይልማ ከበደ በ2009 የውድድር ዘመን ወልዲያን ለቅድመ ዝቅጅት ሀዋሳ ላይ የደቡብ ካስቴል ጨዋታ ቡድኑን እየመራ ባለበት ወቅት በሆቴል ውስጥ ተዝለፍልፎ በመውደቅ ግራ እጁ እና ግራ እግሩ ሙሉ ለሙሉ ፓራላይዝድ ሆኖ በፀና መታመሙ ይታወቃል። ያለፉትን ሦስት ዓመታት የስፖርት ቤተሰቡ እና በተለይ ረዥም ዓመት የተጫወተበት ኢትዮጵያ መድን ድርጅት እና ክለቡ ተረባርበው አሳክመውታል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የተጫወተበት ክለብ መድን ባደረገለት ድጋፍ ወጪ እያደረገ የፊዚዮቴራፒ ህክምናውን ሲከታተል ቢቆይም ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅሙ እያነሰ ህክምናውን መከታተል እስከማይችልበት ደረጃ ለይ ደርሷል። ያለበትን አስቸጋሪ ሁኔታ አስመልክቶ ሶከር ኢትዮጵያ ከይልማ ከበደ ጃሬ ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች።
” አሁን ሁለቱም ግራ እጄ እና እግሬ አይንቀሳቀስም፤ በከዘራ ነው እንደምንም ብዬ በአካባቢዬ ከቤት ወደ ውጭ እየተንቀሳቀስኩ ያለሁት። ህክምና ወጪዬን ኢትዮጵያ መድን ድርጅት እና ክለቡ ለህክምና ወጪዬ እየሸፈነልኝ የፊዚዮትራፒ ህክምና እየተከታተልኩ መቆየት ችዬ ነበር። ሆኖም አሁን ገንዘቡ አልቆ ፊዚዮትራፒ ማድረግ አልቻልኩም። ህመሙም ወደ ቀድሞ ባህሪው እንዳይመለስ እሰጋለው። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የአቅም ውስንነት እንዳለብኝ ተረድቶ ድጋፍ እንዲደርግልኝ ለፌዴሬኑ ፀሐፊ ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ደብዳቤ ካስገባው ከአስራ አምስት ቀን ሆኖኛል፤ እስካሁን ግን ምላሽ አላገኘሁም። በዚህ አጋጣሚም ሶከር ኢትዮጵያ ካላት ሰፊ ተከታይ አንፃር የስፖርት ቤተሰቡ ያለሁበትን ችግር ተረድተው የሚችሉትን ድጋፍ እንዲያደርጉልኝ ጥሪ እንድታስተላልፉልኝ ጥሪዬን አቀርባለው።” ብሏል።
ይልማ ከበደ (ጃሬ)ን መደገፍ እና መርዳት የምትፈልጉ አካላት ከታች ባሉት የባንክ አካውንት በመጠቀም ድጋፍ እንድታደርጉለት ጥሪውን አቅርቧል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥላሴ ቅርንጫፍ – 1000243534864
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!