የ2012 ውድድር ዘመን እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ይመራ የነበረ ሙጂብ ቃሲም ከፋሲል ከነማ ጋር ስላለው ወቅታዊ ጉዳይ ይናገራል።
በፋሲል ከነማ የሁለት ዓመት ቆይታ በማድረግ በተከላካይነት እና በአጥቂነት የተሳካ ጊዜ ያሳለፈው እና በዘንድሮ የውድድር ዓመት በ14 ጎሎች ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን እየመራ የነበረው ሙጂብ ቃሲም ለተጨማሪ ዓመት በዐፄዎቹ ቤት ለመቆየት ሲደራደር መቆየቱ ይታወሳል። የድርድሩ ሁኔታ በምን ይገኛል በሚል በተደጋጋሚ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ጥያቄ ነበር። ሶከር ኢትዮጵያም ይህን መሠረት አድርጋ የሙጂብ እና የፋሲል ከነማ የድርድር በምን ሁኔታ እንደሚገኝ እና የሙጂብ ቃሲም ሀሳብ ምን እንደሆነ ከሙጂብ ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች።
” ከፋሲል ከነማ ጋር ኃላፊዎች ረጅም ጊዜ የፈጀ ድርድር አድርገናል። ሆኖም በአንዳንድ ነገሮች ልንስማማ አልቻልንም። በዚህ ምክንያት ከፋሲል ጋር ለተጨማሪ ጊዜ መቆየት ብፈልግም ሳይሳካ በመቅረቱ ወደ ሌላ ክለብ ለመሄድ ወስኛለው። በቅርብ ቀናትም ቀጣይ ክለቤን አሳውቃለው። ፋሲል ከነማ በነበረኝ ጥሩ ጊዜ የክለቡን አመራሮች ከምንም በላይ ደጋፊዎችን በዚሁ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለው።” ብሏል።
ሙጂብ ቃሲም በግብጠባቂነት ለደቂቃዎች ያህል ከመጫወት አንስቶ በተከላካይነት እና በአጥቂነት በሲዳማ ቡና ፣ በሀዋሳ ከተማ፣ አዳማ ከተማ እና በፋሲል ከነማ መጫወቱ ይታወቃል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!