ጥቂት የማይባሉ የሃገራችን እግርኳስ ባለሞያዎች ጎራ ለይተው በአንድ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ ውዝግብ ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል፡፡ መቼም- ገና ሃሳቡን ሳልጀምረው ስለምን ልጽፍ እንደተነሳሁ የምትገምቱ ብዙዎች ናችሁ፡፡ ክርክሩን የሚያጦፉት ወገኖች “የተጫወተ ያሰልጠን!” ወይስ “የተማረ ያሰልጥን!” በሚል ትርጉም የለሽ ንትርክ ውስጥ ከተዘፈቁ ከራረሙ፡፡ በመሠረቱ እኔ የየትኛውም ጎራ ደጋፊ አይደለሁም፡፡ አንዱን ደግፎ ሌላውን ነቅፎ የመሟገት ፍላጎትም-ሃሳብም የለኝም፡፡ ርዕሱ በራሱ ፋይዳ ያለው እና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ሆኖም አይደለም ይህንንም የምፅፈው፡፡ እንዲሁ- አንዳንዶች በግል ሆነው ከሚያደርጉት ክርክር አልፈው ብዙሃን መገናኛዎችን እየተጠቀሙ ብርቱ አጀንዳ የያዙ ይመስል ውሃ በማያነሳ ሐሳብ መነታረካቸውን ሳይ ስለምናደድ ይህንን አስተያየት ለመፃፍ ተነሳስቻለሁ፡፡
እነዚህ በንትርክ ውስጥ የሚሳተፉት ግለሰቦች መሠረታዊ ዓላማቸው ምን እንደሆነ ባይገባኝም ለሃገራችን እግርኳስ የረባ አስተዋፅኦ አለማበርከታቸውን ሳስተውል ያንገበግበኛል፡፡ ዘርፈ-ብዙ እውቀት በሚሻው የእግርኳስ ማዕቀፍ ውስጥ አዕምሯዊ አድማሳችንን አስፍተን፣ ሳይንሳዊ ተመክሯችንን አሳድገን፣ የሚያንጽ ልምድ አካብተን፣ በሚያግባባን-ተግባብተን፣ በምንረዳዳው-ተደጋግፈን፣ ባለን እውቀት እና ተጨባጭ አበርክቶ ተከባብረን፣ በልዩነት አምነን፣ በጠቃሚ ሃሳቦች ተስማምተን፣ ሥርዓት ባለው አካሄድ ተወያይተን እና ሁላችንም የአቅማችንን ጥረን ለቀጣዩ ትውልድ መሰረት ያለው የእግርኳስ ከባቢ ማስረከብ ሲገባን አሁንም ከዘመናዊ አስተሳሰብ ብዙ ሺህ ማይሎች ርቀን “ታች” ወርደን መገኘታችን ያሳዝነኛል፡፡ ቁጭ ብለን ብዙ የምንተነትንለት የአውሮፓ እግር ኳስ የእድገት ከፍታው ጣሪያ በነካበት በዚህ ዘመን እኛ “እግርኳስ -Art- ነው? ወይስ -Science- ነው?”ብለን ሳናፍር መከራከራችን የሚያስተዛዝበን ነው።
በዓለም አቀፍ የእግርኳስ መድረኮች በትልቅ ደረጃ እግርኳስን ተጫውተው ያሳለፉ፣ በዚሁ ተወዳጅ ስፖርት በተጫዋችነት ዘመናቸው አኩሪ ታሪክ የጻፉ፣ ውጤታማ የሆኑና ታላቅ ለውጥ ያመጡ ተጫዋቾች ኋላ ላይ ደግሞ በአሰልጣኝነቱ መስክ ተሰማርተው የታክቲክ አብዮት ያመጡ፣ በእግርኳስ አጨዋወት ፍልስፍና የተራቀቁ፣ ጨዋታውን ከየዘመኑ ታክቲካዊ ግኝቶች ጋር ያጣመሩ በርካቶች ናቸው፡፡ ጥቂቶቹን እንጥቀስ፦ ጂሚ ሆጋን፣ ኸርበርት ቻፕማን፣ ሑጎ ሜይዝል፣ ካርል ራፕን፣ ቤላ ጉትማን፣ ፍሌይታስ ሶሊች፣ ፍላቪዮ ኮስታ፣ ስታን ኩሊስ፣ አልፍ ራምሴይ፣ ቦሪስ አርካዲዬቭ፣ ቪክቶር ማስሎቭ፣ ሄሌኒዮ ሄሬራ፣ ኦዝቫልዶ ዙቤልዲያ፣ ሩኑስ ሚቼልስ፣ ቫለሪ ሌቫኖቭስኪ፣ ሉዊስ ሴዛር ሜኖቲ፣ ዮሃን ክሩይፍ፣ ሰር አሌክስ ፌርጉሰን፣ አርሰን ዌንገር፣ ማርሴሎ ቢዬልሳ፣… የመሳሰሉትን አሰልጣኞች ቅድመ- ታሪክ ስናይ በተለያዩ የልህቀት ደረጃ እግርኳስን ተጫውተው ስለማለፋቸው እንገነዘባለን፡፡ የአንዳንዶቹ የአሰልጣኝነት ውጤት ከተጫዋችነት ገድላቸው የሚልቅ ሆኖ ይታያል፡፡ የሌሎቹ ደግሞ የተጫዋችነት ጊዜያቸው ይበልጡን ደማቅና በስኬት ያሸበረቀ ሆኖ አልፏል፡፡ ጥቂቶቹ የተለዩ ናቸው – በእግርኳስ ባሳለፉት የተጫዋችነትም ሆነ የአሰልጣኝነት ሥራቸው የስኬትን ማማ የተቆናጠጡ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ሆላንዳዊው ዮሃን ክራይፍ ከሦስተኛው ጎራ ይቀላቀላል፡፡ የእግርኳሱ ዓለም ሁሌም ታላላቅ አሰልጣኞችን ያገኛል፡፡ ባለፈው ሩብ ምዕተ ዓመትም ካርሎ አንቼሎቲ፣ ራፋኤል ቤኒቴዝ፣ ጆዜ ሞውሪንሆ፣ ፔፕ ጓርዲዮላ፣ የርገን ክሎፕ፣ ዚነዲን ዚዳን፣ ዲዬጎ ሲሞኒ እና የመሳሰሉት አሰልጣኞች በስልጠናው ዘርፍ ትልቅ ልዩነት ፈጥረዋል፡፡
እግርኳስን ማሰልጠን የምልከታ ልህቀት ይሻል፤ ጥልቅ እሳቤም ይፈልጋል፡፡ የእግርኳስ መሰረታዊውያን በሆኑት ዝርዝር ጉዳዮች ላይ በቂ እውቀት ማካበት እና የሚሻሻል ተመክሮ ማጎልበትም የዘርፉ ዋነኛ ግብዓቶች ይሆናሉ፡፡ ይህ በተግባራዊ ልምድ፣ በጽንሰ ሐሳብ ግንዛቤ፣ በንባብ፣ በትምህርት ሊገኝ ይችላል፡፡ ከሁሉ በላይ ግን ከፍተኛ ፍላጎት፣ የጋለ ውስጣዊ ሥሜት፣ ቁርጠኝነት፣ ጥረት እንዲሁም ለረጅም ጊዜ አብሮ የሚኖር ዝንባሌ በጨዋታው አልያም በሙያው ተሽሎ ለመገኘት የግድ ይላል፡፡ ስለ ዕውነት ለመናገር በእግርኳስ በተጫዋችነት ዘመናቸው ነግሰው በአሰልጣኝነት ሥራቸው ግን አመርቂ ስኬት ወይም በጨዋታው አቀራረብ ዙሪያ አዎንታዊ ተጽዕኖ ማሳረፍ ያልቻሉ አሰልጣኞች በርካቶች ናቸው፡፡ ይህንን እውነት መዘንጋት አይቻልም፡፡
ከላይ ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት በሰለጠነው የእግርኳስ ዓለም ወደ አሰልጣኝት ሙያ ለመግባት ተጫዋች ሆኖ ማለፍ ብቻ በቂ መስፈርት አይደለም፡፡ በእርግጥ አሰልጣኝ ከመሆን በፊት በ”ፕሮፌሽን” ደረጃ ተጫዋች ሆኖ ማለፍ እግርኳስና ሙያውን በቅርበት ለማወቅ፣ ሥሜቱን ጠንቅቆ ለመረዳት፣ ጫናውን በአግባቡ ለመገንዘብ፣ ተግዳሮቶችን አቅልሎ ለማየት፣ አጠቃላይ የእግርኳሱን አካባቢ ለመረዳት ትልቅ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ጥሩ አሰልጣኝ የመሆን ብቸኛው መንገድ እንደሆነ እንድናስብ ሊያደርገን አይገባም፡፡ ዓለም ዓቀፋዊ ተመክሮዎችም የሚያሳዩት ይህንኑ እውነታ ነው፡፡ እግርኳስን ለአጭር ጊዜ እንኳ በ”ፕሮፌሽናልነት” ሳይጫወቱ ወደ አሰልጣኝነት ሙያ ገብተው ውጤታማ የሆኑና ለበርካታ ዓመታት በትልቅ ደረጃ ሲያሰለጥኑ የሚታወቁ አሰልጣኞች አሉ፡፡ ጥቂቶቹን ለአብነት ብናነሳ፦ ዩሊያን ኔይግልስማን፣ አንድሬ ቪያስ ቦአስ፣ ሊዮናርዶ ያርዲም፣ ኦቭራም ግራንት፣ ሮይ ሆጅሰን፣ ካርሎስ አልበርቶ ፔሬይራ፣ ራልፍ ራግኒክ፣ ቢል ስትረዝ፣ ዤራር ሁዬ፣ አሪጎ ሳኪን እና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሌሎች ደግሞ በዝቅተኛ ደረጃና ሊጎች ለተለያዩ ክለቦች እጅግ ውስን ጨዋታዎች አከናውነው፥ በጉዳት፣ በብቃት ማነስና በሌሎችም ምክንያቶች ከሜዳ በጊዜ የተገለሉ ሆነውም ትልቅ አሰልጣኝ መሆን ችለዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የተወሰኑትን እናስታውስ፡፡ ስቬን ዮራን ኤሪክሰን፣ ማውሪዝዮ ሳሪ፣ ጆዜ ሞሪኒሆ እና ራፋኤል ቤኒቴዝ፡፡
በመሰረቱ በየትኛው ሃገር አብዛኞቹ አሰልጣኞች እግርኳስን ተጫውተው ያለፉ ናቸው፡፡ ይህ መሆኑም ተገቢ መሆኑ የሚያጠያይቅም አይደለም፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስም በሃገራችን ያለው ልማድ ይኸው ነው፡፡ አሰልጣኝ ሆነው ሠርተው ያለፉትም ሆነ እስከአሁን በመሥራት ላይ ያሉት አብዛኞቹ እግርኳስን በተለያዩ ሊጎች ተጫውተው ያለፉ ናቸው፡፡ በጣት የሚቆጠሩቱ ጥቂቶች እግርኳስ ሳይጫወቱ ስፖርት ሳይንስ ተምረው ብቻ በሃገሪቱ ከነበሩት ውድድሮች በአንጻራዊ ልኬት ከፍ ባሉት ደረጃዎች አሰልጥነዋል፡፡ በተጨማሪም- በተለይ የስፖርት ኮሚሽን የፕሮጀክት ስልጠና በየትምህርት ቤቶች በጀመረ ጊዜ አብዛኞቹ አሰልጣኞች በየትምህርት ቤቶች ያስተምሩ የነበሩ የስፖርት ሳይንስ ምሩቃን እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ” ማን ተጫውቶ አሳልፏል? ማንስ ተምሯል?” በሚል እርባና-ቢስ ክርክር ጊዜ እናጠፋለን እንጂ መሠረታዊ ጥያቄ መሆን የሚገባው “በማሰልጠን ሙያ ተሰማርተው ሲሰሩ የቆዩ እና ያቆሙትም ሆኑ አሁንም በመስራት ያሉት አሰልጣኞች ለአትዮጵያ እግርኳስ ምን አበረከቱ?” የሚለው ነበር፡፡
ብዙውን ጊዜ የመርሕ ያህል ሲነገር የምንሰማው ሐቅ የአንድ ሃገር እግርኳስ ዕድገት የሚወሰነው በሃገሪቱ ውስጥ ባሉት ብቃት ያላቸው አሰልጣኞች መጠን ነው፡፡ ከጥንትም ጎራ በመለየት አባዜና በመቧደን ባህል የሚታወቁት አሰልጣኞቻችን ከዚያ ተግባር ወጥተው ከእነርሱ የሚጠበቀውን ሥራ ብቻ አለመስራታቸው ለእግርኳሳችን የንፉቅቅ ጉዞ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፏል፡፡ እርግጥ ስፖርቱን ውስን ባለሙያዎች ብቻ በሚሰሩት ሥራ ማሳደግ አይቻልም፡፡ መሰረት ልማት፣ አስተዳዳራዊ መዋቅሮች፣ የባለ ድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ፣ የአሰልጣኞች ስልጠና ጥራት እና ሌሎችም ጉዳዮች አስፈላጊ ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ እነዚህ ችግሮች እንዳሉ ሆነውም ባለን አቅም እንኳ ተገቢው ሥራ ተስርቷል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ለዚህ ሃሳቤ የተወሰኑ ማሳያዎችን ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ ባላፉት ሃያ ዓመታት በየሊጎቻችን እርከኖች ተመሳሳይ የአጨዋወት ዘይቤ እየተከተለ ዋንጫ ደጋግሞ ያነሳና በኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ የሚሰለጥን ቡድን አላየሁም፡፡ የዋንጫ አሸናፊ መሆን ቢያቅታቸው እንኳ በአጨዋው ሥልት የብዙዎችን ቀልብ የሳበ፣ ወጣት ወይም ጀማሪ አሰልጣኞች አርአያ ልናደርገው እና ልንማርበት የምንችል በታክቲክ አረዳድ የጎለበተ ቡድን አላየሁም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አሰልጣኞች ከአንድ ክለብ ወደ ሌላ ክለብ ዝውውር ቶሎ-ቶሎ ስለሚፈጽሙ በክለቦቹ ዋና ቡድን፣ ወጣት ቡድን እና ታዳጊ ቡድን የጨዋታ አቀራረብ ተመሳስሎ አይታይም፡፡ በዚህም ሳቢያ አሰልጣኞቹ ለክለቡ የአጨዋወት መሰረት በመጣልና ዘላቂ ቡድን በመገንባት ለሌሎች ተምሳሌት የመሆን እድል አልኖራቸውም፡፡ በጽሑፍም ቢሆን የሥልጠና መመሪያም ይሁን የህይወት ታሪካቸውን ፅፈው ለቀጣይ ትውልድ ሲያስቀምጡ አይታዩም፡፡ ይህንን የምለው ጥቂቶች የተሻለ ስራ ለመስራት አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ እንደሚደክሙ ሳልነጋ ነው፡፡
እግርኳስ በጣም ሰፊ ማዕቀፍ ያለው ስፖርት እንደመሆኑ አሰልጣኞችም መመዘን ያለባቸው በሚሠሩት ቡድንና በውጤታቸው ነው፡፡ ጎራ ለይቶ “እኔ አውቃለሁ-እኔ አውቃለሁ!” እያሉ ተመልካችን ግራ ከማጋባት፣ በማይረባና ከንቱ ንትርክ ጊዜ ከማባከን አዎንታዊ በሆኑና እግርኳሳችንን ሊለውጡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ እግርኳስ ወዳዱ ኅብረተሰብ ህልም የሆነበትን የአፍረካ ዋንጫ ተሳትፎ በቋሚነት ማሳካት፣ ክለቦቻችንን በአህጉራዊ ውድድር ውጤታማ ማድረግና የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ አጽዕኖት መስጠት ተገቢ ነው፡፡ ለምን እንደምናሰለጥንና ለቀጣዩ ትውልድ ምን ውርስ ትተን እንደምንሄድ በደንብ ማሰብ ይገባናል፡፡
ይቀጥላል…
*በቀጣዮቹ ሳምንታት በዚሁ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ ከዚህ ቀደምም ባለሙያዎቻችን ሲነታረኩባቸው የከረሙባቸውን ሃሳቦች ይዤ እቀርባለሁ፡፡
ስለ ፀሐፊው
የአስተያየቱ ፀሐፊ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል ፡፡ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፅዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ