የCovid-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ብዙ የሚባሉ የሕይወታችን አካላት ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል። እግርኳስም በዚህ ተፅዕኖ ሥር ከወደቁ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው። ምንም እንኳ በአውሮፓ የሚገኙ ታላላቅ ውድድሮች ከጥቂት ወራት ቆይታ በኋላ ቢመለሱም በሀገራችንም ሆነ በአፍሪካ አብዛኛው ቦታዎች እግር ኳስ ውድድሮች እየተካሄዱ አይደለም።
ሀገራት ውድድሮችን ተመልካቾች በማይገኙበት ሁኔታ በዝግ ስቴዲየም ሲያካሂዱ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው። በቅርቡ ውድድሮችን ለመመለስ በዝግጅት ላይ ለሚገኘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጨዋታዎችን በስኬት እና ጤናን ባስጠበቀ መልኩ ማከናወን የቻሉትን ሀገራት ልምድ መመልከት እና ከዛም ተነስቶ የሀገሪቷን አቅም ባገናዘበ ሁኔታ ውድድሮችን ለመመለስ መጣር ይገባል ። ለመመለስ መቸኮል ሳይሆን እንዴት የሚለው ጥያቄ የበለጠ ወሳኝ ነው።
እንደ እግርኳስ ቤተሰብ የውድድሮች መመለስ ለሁላችንም የደስታ ምንጭ ቢሆንም በተቻለ መጠን ግን ጤናን ማስቀደም፣ ስለጤና ማሰብ እና ተገቢውን ጥንቃቄ መውሰድ ግድ ይላል።
እስራኤል በጣም ጥቂት የሚባሉ ሰዎች ብቻ በቫይረሱ የተጠቁባት ሀገር ነበረች። ይህ ያዘናጋቸው አመራራሮች ዜጎቻቸው ወደ ዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እንዲመለሱ ፈቅደው ነበር። ነገር ግን ይህ ውሳኔ ዋጋ አስከፍሏቸዋል። በቀን ከ5000 በላይ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች እንዳሉ የተረዳችው እስራኤል በድጋሚ ሀገሪቷን ለመዝጋት (second lockdown) ተገዳለች። እንደ ፈረንሳይ እና ጀርመን ያሉ ሀገራት ከ10-20% በሚደርስ አናሳ ቁጥር ደጋፊዎች እንዲመለሱ ፈቅደዋል። ነገር ግን ጥብቅ የሆነ ህጎችን ማክበር ይጠበቃል።
አርቢ ላይፕዚሽ ደጋፊዎች ወደ ስቴዲየም እንዲመለሱ በፈቀዱበት ወቅት ጥብቅ የሆኑ ማኅበራዊ መራራቅ እና የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግን እንደ ግዴታ አስፍረው ነበር። መግባት የተፈቀደላቸው የባለሜዳ ክለብ ደጋፊዎች ብቻ ሲሆኑ በ15 ቦታ በተከፋፈለው ስታዲየም ውስጥ ከ6 በላይ በመሆን አንድ መደዳ ላይ መቀመጥ እንደማይቻል እና ተመሳሳይ የመመሪያ ደንቦች የሰፈሩበት መፅሐፍ ለደጋፊዎች ታድሏል።
ወደ ሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለስ አቅማችን ከሚችለው በላይ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ እንደዚሁም የሟቾች ቁጥር በሁለት አሀዝ እየቀጠለ ነው። በዚህን ወቅት የድንገተኛ አደጋ አዋጁ ባለመታደሱ ምክንያት በርከት ያሉ የቀድሞ ተግባራት ተመልሰዎል። ይህን የተመለከተው ፌደሬሽን ደጋፊዎች ወደ ሜዳዎች እንዲመጡ እንዳይፈቅድ ያሳስባል።
እውነቱን ለመናገር ነገሮችን በጥንቃቄ እናድርግ ቢባል እንኳን የሰው ሆነ የገንዘብ አቅም የለንም። ከዚህ በተጨማሪ የሚወጡ መመሪያዎችን በአግባቡ የሚተገብር ደጋፊ እና በጥብቅ የሚከታተል ብሎም የሚያስፈፅም አካል መኖሩ ሌላ ትልቅ ጥያቄ ነው።
ዋናው ነገር ጤና ነው!
የCovid-19 አንዱ ከባድ እንዲሆን ያደረገው ጉዳይ በቀላሉ ይህ ሰው ቶሎ ያገገማል ያ ደግሞ ሊብስበት ይችላል ብለን መናገር አለማስቻሉ ነው። ከዚህ በፊት የሰማናቸው እድሜያቸው የገፉ ሰዎች እና ተጓዳኝ በሽታዎች ላይ ቫይረሱ መበርታቱ መረጃ እንዳለ ሆኖ ተጨማሪ ምክንያቶች ግን በወጣቱ እና አንፃራዊ ጤነኛ በሚባል ማህበረሰብ ላይ እራሱ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ነው ።
ከላይ ከተጠቀሱ እግር ኳሳዊ ውሳኔዎች የተያያዙ ነገሮች በጤና ባለሙያዎች ምክር እና ተሳታፊነት ብቻ ሊወሰኑ ይገባል። ምንም እንኳን እግር ኳስን ብንወድም እና ቢናፍቀንም አንዳችም የሰው ህይወት በዚህ ምክንያት አደጋ ላይ ሊወድቅ አይገባም ።
– ርቀታችንን እንጠብቅ
– የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛዎችን እንጠቀም
– የእጆቻችንን ንፅህና እንጠብቅ
– ምልክቶች ሲታዩብን በአፋጣኝ ራሳችንን እናግልል። በስልክ አስቀድመን በመደወል የሐኪም ምክር እንቀበል።
© ሶከር ኢትዮጵያ