የፌዴሬሽኑ የአሰልጣኝ ቅጥር እንቆቅልሽ ይፈታ ይሆን?

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ቅጥርን በተመለከተ ቴክኒክ ኮሚቴው ምክረ ሀሳብ እንዲሰጥበት በመራው መሠረት ኮሚቴው ቀጣዩን አሰልጣኝ ማን መሆን እንዳለበት ዛሬ ሀሳብ ስለማቅረቡ ተነግሯል።

ድንገተኛ የካፍ የውድድር መርሐ ግብር መላኩን ተከትሎ በድምፅ ብልጫ አሰልጣኝ ካሰናበተ በኋላ ዳግመኛ አሰልጣኝ የመቅጠር ግዴታ ውስጥ የገባው ፌደሬሽኑ ለሳምንታት አሰልጣኙን ለመቅጠር የመንግሥትን ውሳኔ እየተጠባበቀ መቆየቱን ሲገልፅ እንደሰነበተ ይታወቃል። በመላው ሀገሪቱ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲካሄዱ መንግሥት ፍቃድ መስጠቱን ተከትሎ ባሳለፍነው ሰኞ ስብሰባ የተቀመጠው የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ቀጣዩ የዋልያዎቹ አሰልጣኝን ለመቅጠር የቴክኒክ ኮሚቴው ምክረ ሀሳብ ይዞ እንዲቀርብ ለዛሬ (ረቡዕ) ቀጠሮ ሰጥተው መለያየታቸውም ይታወሳል።

ዛሬ አመሻሽ ላይ የቴክኒክ ኮሚቴው በቃለ ጉባዔ ተፈራርሞ ያቀረበውን ባለ ዘጠኝ ነጥብ ሰነድ ከመረመረ በኃላ ቀጣዩ አሰልጣኝ ማን መሆን እንዳለበት ከውሳኔ ላይ መድረሱ ታውቋል፤ ፌዴሬሽኑ እስካሁን አሰልጣኙ ማን እንደሆነ ይፋ አያድርገው እንጂ። አሁን የሚጠበቀው ምናልባትም በነገው ዕለት አሰልጣኙ ማን እንደሆነ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ነው። ፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ኮሚቴውን ምክረ ሀሳብ ተቀብሎ አሰልጣኙን ይቀጥራል? ወይስ ሥራ አስፈፃሚው በራሱ መንገድ በድምፅ ብልጫ አሰልጣኙን ይመርጣል የሚለው ጉዳይም አጓጊ ሆኖ የሚጠበቅ ይሆናል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!