ጸሀፊ፦ ቶቢያስ ኻን
ትርጉም፦ ደስታ ታደሰ
… ካለፈው ሳምንት የቀጠለ
“የሦስተኛው ተጫዋች” ስትራቴጂያዊ አጠቃቀም ንድፈ-ሐሳብን በተቀናጀ መልኩ በተግባር ለማዋል በቅድመ-ሁኔታ ደረጃ ሊተኮርባቸው የሚገቡ መስፈርቶች ይኖራሉ፡፡ ይህን ለመከወን በጎነ-ሶሥት ምስል (Triangle) እና በተዛነፈ ጎነ-አራት ምስል (Diamond) የሚወከሉ ተለዋዋጭ የተጫዋቾች እንቅስቃሴያዊ አቋቋሞች (Positions) ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡ እንደሚታወቀው እነዚህ ምስሎች ብዙ የመቀባበያ አማራጭ መስመሮችን መፍጠር ስለሚያስችሉ ተከታታይ ቅብብሎችን ለማድረግ የሚያግዙ ሰያፍ-የአግድሞሽ መቀባበያ መስመሮች (Diagonal Passing Lanes) ያስገኛሉ፡፡ ሐሳቡን ጠቅለልና ቀለል አድርገን ለመግለጽ ያህል ኳስ ያዘው ቡድን ተጫዋቾች በሜዳው ቁመት እና ስፋት የተለያዩ ቦታዎች ላይ ሆነው ቅብብሎች መከወን ይችላሉ፡፡ተጫዋቾቹ የተሻለ የቦታ አያያዝ በኖራቸው መጠን የ”ሶስተኛው ተጫዋች” ታክቲክን ለመተግበር ሁኔታዎች አመቺ ይሆናሉ፡፡
ለምሳሌ፦ የ”ሶስተኛው ተጫዋች” መርህን በመጠቀም የተጋጣሚ ቡድን የመከላከል መስመርን ለማለፍ ብንፈልግ ሶሥተኛው ተጫዋች እንቅስቃሴያዊ ቦታ አያያዙን ከተጋጣሚው ተከላካዮች አንጻር እና ኳሱን የሚያቀብለው የቡድን አጋሩ የበለጠ ነጻ እንዲሆን ይበልጡን ወደ ተጋጣሚው የሜዳ ክልል መጠጋት ይኖርበታል፡፡የመሃል ተካላካይ- የመስመር አማካይ-የተከላካይ አማካይ ጥምረት ከተለመዱ የሜዳ ላይ ጥምረት ከንዱ ነው፡፡ በተጫዋቾች የቦታ አያያዝ ሳቢያ እነዚህን መሰል ጥምረቶች በጨዋታ ወቅት ሜዳ ላይ በርካታ የስፋት መስመሮች (Horizontal Lines) ያስገኛሉ፡፡ የስፋት አልያም የጎንዮሽ መስመሮችን መጠን ብቻ ማሳደግ በቂ አይደለም፤ ተጫዋቾቹ በሚሰለፉባቸው “ዲፓርትመንቶች” በሚኖራቸው የኋላ-ፊት እንቅስቃሴያዊ ግንኙነት በሜዳው ቁመት የሚፈጠሩ መስመሮችም (Vertical Lines) አስፈላጊ ናቸው፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያት ደግሞ በሰያፍ የመቀባበያ መስመሮች የሚደረጉ ቅብብሎች (Diagonal Passes) በሜዳው ቁመትም ሆነ ስፋት ከሚደረጉ ቅብብሎች በላቀ ለመከላከል አስቸጋሪ ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት ከአንድ በሜዳው ቁመት ብቻ ከሚኖር የመቀባበያ መስመር (Vertical Passing Lane) እና በሜዳው ቁመት-በሰያፍ አኳኋን ከሚኖር የመቀባበያ መስመር (Diagonal Passing Lane) ይልቅ ሁለት ሰያፍ የመቀባበያ መስመሮችን መስራት ይህን የሶስተኛ ተጫዋች ንድፈ-ሐሳብ በጥሩ ግንዛቤ በተግባር ለመረዳት በጣም ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ “ሶስተኛው ተጫዋች” ሁሌም ኳሱን ለተወሰኑ ሰከንዶች ይዞ የመረጋጋት ዕድል ይኖረዋል፡፡ በተለይ የተጋጣሚ ቡድን ተከላካይ የቅብብሉን መዳረሻ ለመገመትና ኳስ ተቀባዩን ብቻ የመቆጣጠር አዝማሚያ ካሳ “ሶስተኛው ተጫዋች” አማራጮችን የመፈለግ፣ የጨዋታውን ግለት የመምራት እና ጥሩ የመጨረሻ ውሳኔዎችን ለመወሰን የሚያመች ቦታ ላይ የመገኘት አጋጣሚዎች ይፈጠሩለታል፡፡
ምስል፦
ከላይ በምስሉ እንደሚታየው አንዴ ቀዳሚውን ቅብብል በሜዳው ቁመት ካደረግን “ሦስተኛው ተጫዋች” በዚሁ አቅጣጫ ኳስን ይዞ ለመንቀሳቀስ ይቸገራል፡፡ ስለዚህም ተጫዋቹ ብቸኛ አማራጩ ኳስን የመልቀቅ ውሳኔ ይሆናል፡፡ ያልታሰበበትና በተጋጣሚ ቡድን ተጫዋች ጫና የሚደረግ ቅብብል ደግሞ ለሥህተት ይዳርጋል፡፡ ከዚህም በላይ ቅብብሉን በሚያካሂዱት ተጫዋቾች መካከል የሚኖረው ጥግግትም ይጨምርና ክፍተቱ ይጠባል፤ እናም የተሳካና አመቺ የቅብብል ሒደት እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ የመሃል ተከላካዩ ላይ ጫና የሚያደርገው ተጫዋች ምናልባትም ወደ መሃል አማካዩ የሚላከውን ኳስ ሊያቋርጠው ይችላል፡፡ የመሃል አማካዩ የቦታ አያያዝ በጥቂቱ ወደ ኋላ የሚመላለስ ተደጋጋሚ ቅብብልን ብቻ ከመፍቀድ ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ በሜዳው የሚገኙ ሌሎቹ አቅጣጫዎች ከፍ ያለ የተጫዋች እና የኳስ ቁጥጥር ይፈልጋሉ፡፡
ምስል፦
ከላይ በቀረበው ተቃራኒ ማዕዘናት ላይ ባሉ ተጫዋቾች በሚፈጠር የመቀባበያ መስመር የመሃል አማካዩ ከመሃል ተከላካዩ ኳስ ማቀበል ፣ በተከላካይ አማካዩ ቦታ አያያዝ እና በሌሎቹ ተከላካዮች ባሕሪ ላይ በመመርኮዝ የተለያዩ አማራጮች ይኖሩታል፡፡ ለምሳሌ፦የኳስ ቅብብሉ ለመሃል አማካዩ የቀኝ እግር ቢደርስ ወደ ቀኝ ትከሻው በሚያመለክተው አቅጣጫ መዞር ይችላል፡፡ ተከላካዩ የቅብብሉን ድግግሞሽ ገምቶ አልያም ቀድሞ የነበረበት ቦታ የሜዳው መሃለኛው ክፍል መሆኑን ተረድቶ እንቅስቃሴውን ከሚያደርግበት ቦታ አንጻር በተቃራኒ ማዕዘናት ከተንቀሳቀሰ (በምስሉ በቀይ ከተቀለሙት-አማካዩ ) የመሃል አማካዩ በተከላካዩ አጨዋወት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳርፍ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል የመሃል ተከላካዩ ለመሃል አማካዩ በስተግራው ኳስን ካቀበለ ተጫዋቹ እንቅስቃሴያዊ አቋቋሙን በትንሹ በማስተካከል ቅብብሉን ማስቀጠል ይመርጣል፡፡ ይህ ቅብብል በሜዳው ስፋት በቀላሉ የሚከወን በመሆኑ የተከላካይ አማካዩን ወደፊት እንዲያመራ ያስገድደዋል፡፡
በዚህ ናሙና የመሃል አማካዩ ሌላም ሦስተኛው አማራጭ ይኖረዋል፡፡ ይህም አማካዩ ትከሻውን ወደግራ በማዞር (በጥቁር በተቀለሙት – ተከላካዮች) ጀርባ የሚገኘውን ክፍት ቦታ ማጥቃት ነው፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው ግን ተከላካዩ አንድ ጊዜ ከነበረበት ቦታ በተቃራኒ ማዕዘን ተንቀሳቅሶ የመሃል አማካዩ ጋር ሊቀርብ ካልቻለ ነው፡፡ ተከላካዩ በተለያዩ አቅጣጫዎች ሊከላከል ከመቻሉ አንጻር የመሃል ተከላካዩ በምላሹ ለመሃል አማካዩ ግራ እግር ጠንከር ያለ ቅብብል ሊፈጽምለት ይችላል፡፡ ይህም አማካዩ ወደ ግራው እንዲዞር የሚጠቁም ምልክት ይሆንለታል፡፡
ተጫዋቾች ቅብብሎችን የሚከውኑበት ሒደት አፋዊ ላልሆነ ተግባቦት ምርጡ ምሳሌ ነው ፡፡በማውሪዝዮ ሳሪ የሚሰለጥው የናፓሊ ቡድን ውስጥ ይህንን ተግባቦት በመደበኛነት መታዘብ ይቻላል፡፡ ይህ ደግሞ በተለይ አላማ ያላቸው ሁሉም ቅብብሎች ላይ ይታያል፡፡ ስለዚህ የ”ሶሥተኛው ተጫዋች” ሃሳብ ከላይ በተገለጹት የናፓሊ መንገዶች ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አቀራረቦች ጥቅም ላይ ማዋል ይችላል፡፡
በእኔ አስተያየት የ”ሶሥተኛው ተጫዋች” ሃሳብን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ማንኛውም ቡድን ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ አምስት ነጥቦች አሉ፡፡
1) ተጫዋቾች በሜዳው ቁመት እና ስፋት የሚኖራቸው እንቅስቃሴያዊ የቦታ አያያዝ
2) የተለያዩ አማራጮች ሊያስገኙ የሚያስችሉ የመቀባበያ ማዕዘናትን ለመፍጠር መጣር
3) ቅብብሎችን በሚከውኑ ተጫዋቾች መካካል ያለውን ርቀት ሚዛናዊ ማድረግ
4) የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋች በሚፈጥረው ጫና ሳቢያ የቅብብሎች ስኬት ኳስ ለመጫወት የሶሥተኛው ተጫዋች አቋቋም ትክክለኛ መሆን ይኖርበታል፡፡
5) የመጀመሪያው ቅብብል በተቻለ አቅም መሬት የያዘ መሆን አለበት፡፡
በተራ ቁጥር (3) ላይ የተነሳው ሐሳብ ጠቃሚ የኳስ መቀባበያ ማዕዘናትን ከመፍጠር ጋር አብሮ የሚሄድ ነው ፡፡ ሁሌም ተጫዋቾች የእነርሱ እንቅስቃሴያዊ ቦታ አጠባበቅ የ”ሶሥተኛው ተጫዋች”ን ታክቲካዊ አተገባበር ውጤታማ ማድረግ ወይም ያለማድረጉን እንደሚወስን መገንዘብ አለባቸው፡፡ እዚህ ላይ እንደ አሰልጣኝ በሜዳ ላይ ተጫዋቾችን በቀላሉ አቅጣጫ ለማስያዝ የሚያስችሉ መመሪያዎችን መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡ ለምሉዕነት የተጠጋ ቦታ አያያዝ ማለት በእንቅስቃሴ ውስጥ ካሉ ሦስት ተጫዋቾች የተጋጣሚ ቡድን አንድ ተከላካይ ሁለት ተጫዋቾችን በተመሳሳይ ጊዜ እንዳይቆጣጠር በሚያስችል በቂ ርቀት ላይ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ የማጥቃት ሒደትን ለማቀላጠፍ እና በቀላል የሚከወኑ የኳስ ቅብብሎችን የተሳኩ ለማድረግ የመቀባበያ መስመሩ ርዝመት በአንጻራዊ መጠን አጠር ማለት አለበት፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!