በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት በተለይ በቀደመው ዘመን በሜዳም ከሜዳም ውጭ አይረሴ አሳዛኝ፣ አስቂኝ ገጠመኞች ተስተናግደው አልፈውበታል። ለዛሬው አንበጣ ስለተመገበው ብሔራዊ ቡድን በትውስታ አምዳችን ልናስቃኛችሁ ወደድን።
መቼም በብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተነግሮ የማያልቅ ብዙ አስገራሚ ገጠመኞችን እንዳለፉ አንባቢያንም፣ በወቅቱም የነበራቹ ተጫዋቾችም፣ አሰልጣኞችም እንዲሁም የስፖርቱ የአመራር አካላት የምታውቁት እውነታ ነው። በየዘመኑ የተከሰቱትን አሳዛኝ እና አስቂኝ ገጠመኞችን እኛም በምናገኘው አጋጣሚ ሁሉ በወፍ በረር ስናስቃኛቹ መቆየታችን ይታወሳል። በተለይ በሰማንያዎቹ እና በዘጠናዎቹ ዓመታት ውስጥ እጅግ ፈገግ የሚያስብሉ፤ በተቃራኒው ልብን የሚሰብሩ ትውስታዎች አልፈዋል። አሰለጥናለው ብሎ ሄዶ ተጫውቶ የሚመለስ አሰልጣኝ፣ ከቋንቋ ጋር ተያይዞ የሚፈጠር አለመግባባት፣ በወቅቱ ከነበረው የመንግስት አስተዳደር (አገዛዝ) እና ከአቅም ማነስ ጋር ተያይዞ ከሀገር ለመጥፋት በሚደረግ ጥረት ውስጥ የሚፈጠሩ ገጠመኞች አልፈው ኖረዋል። በዛሬው ዕለትም ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ዩጋንዳ ሄዶ አንበጣ በልቶ ስለተመለሰው ስብስብ በትውስታ አምዳችን ከአሸናፊ በጋሻው እና ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ ጋር ያደረግነውን አስቂኝ ቆይታ እነሆ ጀባ ብለናል።
አሸናፊ በጋሻው…
“ለሴካፋ ጨዋታ ሰማንያዎቹ ውስጥ ይመስለኛል ወደ ዩጋንዳ ሄደናል። ውድድሩ በሁለት ምድብ ተከፍሎ ነበር የሚካሄደው። ለእኛ የደረሰን ከዋናው ከተማ ካምፓላ ራቅ ብላ የምትገኝ ሁለተኛ ከተማ የሆነችው ጂንጆ የምትባል ነው። በመኪና ሆነን ወደ ከተማዋ ስንሄድ መሽቶብን ያረፍንበት ሆቴል በጣም አምሽተን ነው የገባነው። በጣም ደክሞን ርቦን ስለነበር ሆቴሉ የሚያቀርበው ምግብ ስለመሸ አልቋል፤ አልተዘጋጀም በማለት ከሌላ ሆቴል ምግብ ይምጣላቹ ተብለን ፓስታ፣ ሩዝ ምናምን ይመጣል። ለካ በዩጋንዳውያን ዘንድ እንደ ባህላዊ ምግብ አንበጣ ማጣፈጫ ናት። እኛ ይሄን አላየንም መሽቷል፣ በዛ ላይ ርቦናል ሁላችንም በሩዝ እና በፓስታ ውስጥ እንደ እርድ ቅመም ተቀላቅሎ የተሰጠንን አንበጣ ግጥም አድርገን በልተን ገብተን ተኝተናል። በነጋታው ወደ ልምምድ ሜዳ ስንሄድ በላስቲክ፣ በላስቲክ ታሽጎ የሚሸጥ ምግብ አለ አይደል? እንደዛ አይተን በመኪናችን መስኮት ምንድነው ይሄ ብለን ስንጠይቃቸው አንበጣ ነው አሉን። እንዴ ! አንበጣ እንዴት ይበላል ስንል አንድ ሀበሻ አስተርጓሚ ሰርቪስ ውስጥ ነበር እና ይሄ ምን ይገርማቹሀል ማታ እራት የበላችሁት አንበጣ እኮ ነው። ልክ እንደኛ ሀገር አይነት። አንበጣ እኮ ቅመም ነው ብሎ ነገረን። ከዚህ በኃላ ነው አንበጣ መብላታችንን ያወቅነው። ከዛ በኃላ ሩዙን ያለምንም ቅይጥ በነጩ መብላት ጀምረናል። በጣም የሚገርምህ ግን ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ እስክንመጣ ድረስ በልቷል።”
ይሄ ነገር እውነት ነው ወይ ስንል አንበጣውን እስኪመለስ ድረስ በላ ስለተባለው አንጋፋው ግብጠባቂ ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ ጋር ደውለን ጠይቀነው ይሄን ብሎናል።
“(በጣም እየሳቀ…) ውሸታም በለው፤ ይህ ተንኮለኛ፤ ተው ተው በለው። ልክ በላስቲክ ታሽጎ እንደሚሸጥ ለውዝ ወይም ቆሎ መስሎት ተሸውዶ ግጥም አድርጎ እየበላ የከረመው ራሱ ነው። እኔ አልበላሁም ይሄ ውሸታም። አጣጥሞ፣ በደንብ አድርጎ ከመንገድ እየገዛ የበለው ራሱ ነው። (በጣም እየሳቀ …) እኔን በላ እያለ ያጭበረብረኛል። ይህ የሆነው 1988 ጂንጃ ከተማ ነው።”
*የፅሁፉ አዘጋጅ ከጨዋታ አዋቂው የቀድሞ ድንቅ ተጫዋች አሸናፊ በጋሻው ጋር ይህን ቃለ መጠይቅ ለማድረግ በደወለለት ወቅት ያለውን ታሪክ ነግሮት ሲያበቃ ይህ አንበጣ የበላችሁበት ዘመን መቼ ነው ብሎ በሚጠይቀው በኛ 2003 ነው አለ። እንዴ! እንዴት? ይህ ይሆናል ብሎ ሲመልስለት ወድያውኑ በፈረጆች ነው ብሎ እየሳቀ መልሷል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!