ትውስታ | ከአንጋፋው ጋዜጠኛ ከገነነ መኩርያ (ሊብሮ) ጋር

በኢትዮጵያ እግርኳስ ከተፈጠሩ ብርቅዬ የእግርኳስ ጋዜጠኞች አንዱ ነው። ከታሪክ አዋቂነቱ የተነሳ “እሱ የማያውቀው ምንድነው?” የተባለለትም ነው። በተለይ የ60 ዎቹ፣ የ70ዎቹ፣ የ80ዎቹ እና የዘጠናዎቹ የእግርኳሱ ዐበይት ክንውኖችን በሚገባ ጠንቅቆ ያውቃል። በህትመት ሚዲያው ሊብሮ የተሰኙ መሠረቱን የሀገር ውስጥ እግርኳስ ላይ ያደረገ ረጅም ዓመት ያገለገለ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በመሆን መሥራቱ ይታወቃል። ወደ ራዲዮ ብቅ በማለትም በውስጡ ያስቀመጣቸውን ከጠጅ ቤት እስከ ኤርትራ፣ ከቀይ ሽብር እስከ ነጭ ሽብር፣ ከብሔራዊ ውትድር እስከ አይረሴ ወጎች የዳሰሱ የእግርኳስ ታሪኮችን በብስራት ኤፍኤም ለአድማጮቹ ሲያስኮሞክም ቆይቶ በመፅሐፍት በመልክ ለአንባቢው ማቅረቡ ይታወሳል። በአሁን ሰዓት ወደ ቲቪ መስኮት ብቅ ብሎ የማይጠገቡ ታሪኮቹን በአሻም ቲቪ እያስመለከተን የሚገኘው ገነነ በካፍ የOrder of Merit ሽልማት በእግርኳሱ ላበረከተው አስተዋፅኦ ተበርክቶለታል። ያለፉት ሠላሳ ዓመት በላይ በቆየበት በዚህ ሙያ ውስጥ ያጋጠመውን አስቂኝ የጋዜጠኝነት ህይወት አስመልክቶ በዛሬው የትውስታ አምዳችን ሀሳቡን እንዲህ አጋርቶናል። መልካም ቆይታ!

አጥር ያዘለለው ቃለ መጠይቅ

ወቅቱ 1986 ነበር። አሁን ስማቸውን ዘንግቸዋለው፤ የኢትዮ ኤሌትሪክ ክለብ ኃላፊ ነበሩ። ክለቡ ውስጥ የሆነ አጨቃጫቂ ችግር ተፈጥሮ ይህን አጣርቼ ቃለ መጠይቅ ለመሥራት በተደጋጋሚ ቢሯቸው ብሄድ ሊናግሩኝ ፍቃደኛ አልሆኑም። በቃ እርሳቸው ይገኛሉ ብዬ በማስብበት ቦታ ሁሉ ብሄድ ላገኛቸው አልቻልኩም። በመጨረሻ ቤታቸው አፈላልጌ ሄድኩ። እኔ መሆኔን ሲያውቁ ለጥበቃ እንዳልገባ በመንገር የለም እያሉ ያመላልሱኝ ጀምር። በኃላ ያን ጊዜ የወጣትነቱ ድፍረት ስላለ ሆን ብዬ የቤታቸውን ትልቅ አጥር ዘልዬ እንደ ሌባ ገባሁ። ሲያዩኝ በጣም ገረማቸውና ቃለ መጠይቁን አድርጌ ወጣው እልሀለው

የሙሉጌታ ከበደ ቤቢ ፊያት

ይህ ገጠመኝ የተከሰተው በ1976 ነው። ሙሉጌታ ከበደ የሦስት መቶ ብር ደሞዝተኛ ነው። በተጫዋችነቱ ሳይሆን የቢራ ፋብሪካ የሽያጭ ክፍል ሠራተኛ ሆኖ የሚያገኘው ደሞዝ ነው። በተጫዋችነቱ ሃምሳ ብር ተብሎ ለትራንስፖርት ነው የሚሰጠው። ታዲያ የሁለት ሺህ ብር ቤቢ ፊያት መኪና የገዛ የመጀመርያ ተጫዋች ይሆናል። ሁሉም ሰው ጊዮርጊስ ቤት እግረኛ ነበር። አሰልጣኙ ሳይቀር መኪና የለውም። ሙሉጌታ የመጀመርያ ነው። በኃላ ነው ዳኛቸው ደምሴ እና አንበሉ ሰለሞን መኮንን (ሉቾ) ቤቢ ፊያት መኪና የገዙት። እኔ የዛን ጊዜ ተጫዋች ስለነበርኩ ገነት ሆቴል ነበር የማርፈው። ገነት ሆቴል ከሜኪሲኮ ወደ ሳር ቤት በሚወስደው መንገድ ነው የሚገኘው። ከሜክሲኮ ወደ ገነት ሆቴል ስትሄድ መንገዱ ቁልቁለት ነው። ከገነት ሆቴል ወደ ሜክሲኮ ለመሄድ ደግሞ መንገዱ ዳገት ነው። ታዲያ ሙሉጌታ ተንኮለኛ ነው። ሁሌ ወደ ሜክሲኮ (ቢራ ፋብሪካ)፣ መርካቶ ሲሄድ ና እያለ ይዞኝ ይሄዳል። ሁልጊዜ መኪናዋ ዳገት ስትወጣ ከብዷት መንገድ ላይ ትቆማለች እኔም እየወጣው እንድትነሳ እገፋለው መኪናዋም ትነሳለች። ለካ በኃላ ነው የገባኝ። ይዞኝ የሚሄድ መኪናውን እንድገፋለት አስቦ ነው። (እየሳቀ) የሚገርምህ ይህን ያወቁ ሌሎች ተጫዋቾች ከእርሱ ጋር አይሄዱም። እኔ ብቻ ነበርኩ የምሄድለት። በኃላ ሲገባኝ እኔም አለመሄዱን መርጫለው። አንድ ቀን የሆነውን ሌላ ገጠመኝ ላጫውትህ። አንድ ቀን እየሄድን በቤቢ ፊያቷ የሆነ ልጅ ትገጫለች። ሰዎች ተሰበሰቡና ልጁ ከወደቀበት ተነስቶ ሲያየው ለካ ሙሉጌታ ከበደ ነው። “ዘንድሮ ዋንጫ ትበላላችሁ” አለው። ሙሉጌታም “አዎ” አለው። “በቃ ሂድ ምንም አልሆንኩም” አለው። የተሰበሰበውም ሰው እየሳቀ ተገርሞ ሄዷል።

ቦረና ለሚገኝ ተጫዋች ጅግጅጋ… አራባና ቆቦ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመርያው ግብጠባቂ ነው። ባላንባራስ በርሄ ይባላል። ወጌሻም ጭምር ነው። ወደ ሜዳ ሲመጣ ቅቤ፣ ጣውላ እና የተለያዩ የህክምና እቃዎችን ይዞ ይመጣል። ሜዳ ላይ ተጫዋች ሲጎዱ ጎሉን ትቶ በቅቤ እየቀባ ያክም ነበር። አንድ ሁለት ጥያቄ ልጠይቀው እኮ ነው ይሄን ያህል ብዙ ጥያቄ አልነበረኝም። ስደውልለት እህቱ አንስታ ጅግጅጋ ነው ያለው አለችኝ። ተነስቼ ሁለት ቀን ይሁን ሦስት ቀን ፈጅቶብኝ ጅግጅጋ ከተማ ገባው። ከዛም እዚህ የለም ቦረና ነው ያለው አሉኝ (…እየሳቀ) አስበው እንግዲህ ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ያውም ለሁለት ጥያቄ ጅግጅጋ ሄደህ ቦረና ነው ያለው ስትባል። ጅግጅጋ ወደ ሀረር መንገድ ቦረና ወደ ሲዳማ ወደ ክብረ መንግሥት መንገድ ነው። እንደዛሬው የመገናኛ መንገዱ ቀላል አልነበረም። አድራሻ የላቸውም። የምታገኝበት መንገድም ከባድ ነበር።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!