ትውስታ| በአራቱም ማዕዘን ኢትዮጵያውያንን ያስተሳሰረችው ልዩ ዕለት – በደጉ ደበበ አንደበት

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሦስት አሥርት ዓመታት በኃላ የሰማይ ያህል ርቆ የቆየውን አፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ያሳካበት ታሪካዊ ቀን ዛሬ ስምንት ዓመት ደፍኗል። ሁኔታውም በወቅቱ አንበል ደጉ ደበበ አንደበት እንዲህ ይገለፃል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሱዳን ላይ የደረሰበትን የ5-3 ሽንፈት ቀልብሶ ወደ 2013 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ አዲስ አበባ ላይ ህዝቡ እና ብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት ላይ ነው። ተመልካቹ እሁድ ጥቅምት 4 ቀን 2005 በጉጉት የሚጠበቀውን ይህንን ጨዋታ ለመመልከት አላስችል ቢለው እሑድ ለሚካሔድ ጨዋታ ዕለተ ቅዳሜን ስታዲየም ዙሪያ ሰልፍ ይዞ ብርድ ላይ ማደርን ምርጫው አድርጓል።

ጨዋታው ተጀምሮ የመጀመርያው አጋማሽ ያለ ጎል መጠናቀቁ እና ቡድኑ ግልፅ የጎል ማስቆጠር አጋጣሚ ለመፍጠር መቸገሩ በስታዲየሙ የተገኘው እና በቤቱ ሆኖ በቴሌቭዥን የሚከታለው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተመልካችን አስጨንቋል። በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው በመግባት ተጋድሎ ያደረጉት ዋልያዎቹ በአዳነ ግርማ ጎል ቀዳሚ መሆን ቻሉ። በዚህች ጎል የተነቃቁት ዋልያዎቹ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የግድ አንድ ተጨማሪ ጎል ያስፈልጋቸው ነበር። በዚህ ሰዓት ነበር ወርቃማ ጎሏን ሳላዲን ሰዒድ ያስቆጠረው። ከሁለተኛዋ ግብ መቆጠር በኋላ ተመልካቹ ደስታውን የገለፀበትን መንገድ በፅሁፍ መግለፅ በጣም ከባድ ነበር። በደስታ ማዕበል እየተናጠ በሚገኘው ተመልካች ውስጥ ወደ ጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ የግብጠባቂው የጀማል ጣሰው መጎዳት እና የአዲስ ህንፃ እርሱን ተክቶ መግባት የነፍስ ግቢ ውጭ የምጥ ሰዓት ሆነ። የመሐል ዳኛው የጨዋታውን መጠናቀቅ በፊሽካ ድምፃቸው ሲያበስሩ፣ በድምር ውጤት 5-5 በሆኖ ከሜዳ ውጭ ብዙ ባስቀጠረ ሕግ ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት ጥበቃ በኋላ ወደመሰረተችው አፍሪካ ዋንጫ ለ10ኛ ጊዜ በመሳተፍ ዳግም መመለስ ቻለች።

ይህች ዕለት የኢትዮጵያ እግርኳስን በብዙ መንገድ አነቃቅታለች፣ ከሜዳ የራቀውን ተመልካች ወደ ሜዳ መልሳለች፣ ለኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በውጪ ሀገራት የመጫወት ዕድል እንዲያገኙ አስችላለች፣ እግርኳሱም ትኩረት እንዲያገኝ አግዛለች። ይህችን አይረሴ ገጠመኝን በትውስታ አምዳችን የወቅቱ የቡድኑ አንበል የነበረው ደጉ ደበበ ወደኃላ ተመልሶ ጊዜውን እንዲህ ያስታውሰዋል።

የኦምዱርማኑ ጨዋታ…

በታሪክ አጋጣሚ ከረጅም ዓመት በፊት ካልሆነ በቀር ለአፍሪካ ዋንጫ ጫፍ የድሰ ቡድን በእኔ ዕድሜ አላየሁም። ይሄን ጫፍ የደረስንበትን ጉዞ አሳክተን ታሪክ ለመስራት ሁላችንም የቡድን አባላት ከፍተኛ ተነሳሽነት ይዘን ነው ሱዳን የሄድነው። ጥሩ ተንቀሳቅሰን ጎሎችንም አስቆጥረን ጨዋታውን ተቆጣጥረን ነበር። ሆኖም ሁሌም በብሔራዊ ቡድንም፣ በክለቦቻቸውም በሚታወቁበት መንገድ ዳኞች ይይዛሉ። ለዚህም የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ይከፍላሉ። አይደለም ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በሜዳቸው ወሳኝ ጨዋታ ለማድረግ እንዲሁም በሴራ ይታወቃሉ። ያው የፈራነው ደርሶ በሚያሳዝን ሁኔታ በመጨረሻ ደቂቃ ሁለት ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው 5-3 አሸንፈውን ተመለስን።

ሽንፈቱ ቡድኑ ላይ ለመልሱ ጨዋታ ምን የፈጠረው ቁጭት…

በሆነው ነገር ወደኃላ ማብሰልሰል አልፈለግንም። አስራ አንድ ለአስራ አንድ ተጫውተን ከሆነ ከሜዳ ውጭ በተፈፀሙ ሥራዎች እንዳሸነፉን እናውቃለን። ስለዚህ በሜዳችን ይህን ውጤት ቀልብሰን አንድ ታሪክ መስራት እንደምንችል አምነን የመሥራት አቅሙ፣ ቁጭቱ፣ ከፍተኛ ፍላጎቱ እና የህዝቡን ጉጉት ይዘን ለጨዋታው ስንዘጋጅ ቆይተናል።

ከጨዋታው በፊት የነበረው የቡድኑ ስሜት…

የጨዋታው ዕለት ወደ ጠዋት አካባቢ ቅድመ ጨዋታ ስብሰባ እያደረግን ሁላችንም ላይ ጭንቀት ይታያል። ስታዲየም ሞልቶ የተመለሱ ደጋፊዎች በሆቴሉ ዙርያ ተሰብስበው እየጨፈሩ እያበረታቱን ነው። ይህ የበለጠ ኃላፊነቱ እየጨመረ ጭንቀት ውስጥ ከቶናል። አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ስለ ጨዋታ አቀራረብ ሊያስረዳን እጁን ጥቁር ሰሌዳ ላይ አድርጎ መፃፍ ሊጀምር ሲል እጁ ይንቀጠቀጥና መፃፍ ያቅተዋል። በዚህ ሰዓት መቼም የማልረሳውን አንድ ንግግር ተናገረ “ልጆች ቢቸግራችሁ እንኳን አሰልጣኝ እንዳትሆኑ” አለ። ይህን ያለው ከራሱ ስሜት አንፃር አይደለም፤ የህዝቡን ስሜት አይቶ ነው።

ጉዞ ከዋቢ ሸበሌ ሆቴል ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም…

በጣም የሚገርም ነበር። ከሸበሌ እስከ አዲስ አበባ ስታዲየም በምናደርገው ጉዞ ውስጥ መንገዱ በደጋፊዎች ተጨናንቆ “አታሳፍሩንም” እያለ ይጨፍራል። በብዙ ጥረት ነው ስታዲየም የደረስነው። ይህን ስታይ የሚሰማህ ስሜት እና ጭንቀት በምንም ቃላት የሚገለፅ አይደለም። ከመላው ኢትዮጵያ ከአራቱም ማዕዘን ነው ሰዉ የወጣው፤ ከፍተኛ ጉጉት አለ። ስታዲየም ደርሰን መልበሻ ክፍል ስንገባ ምን እንደሆነ አናውቅም ሁሉም ጥግ ይዞ ያለቅሳል። እኔ አሁን ለምን እንዳለቀስን ብትጠይቀኝ አላቀውም። የሆነ ሆድ የሚበላህ ነገር አለ አይደል። በቃ እናለቅስ ነበር። ፈጣሪ ረድቶን ይህን ህዝብ የምናስደስትበትን መንገድ እያሰብን ወደ ሜዳ ገባን።

በመጀመርያው አጋማሽ ጎል ባለመቆጠሩ የተፈጠረባቸው ጫና…

ከነበረን ከፍተኛ ጉጉት የተነሳ በመጀመርያው አጋማሽ ጎል ለማስቆጠር ተቸግረናል። ሰዓቱ እየገፋ በሄደ ቁጥር ደግሞ የበለጠ ጭንቀቱ ከፍ እያለ መጣ፤ ተመልካቹም በዝምታ ተውጧል። እረፍት ደርሶ መልበሻ ክፍል እንደገባን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እየተቆጣ በከፍተኛ ድምፅ እየጮኸ “ጨዋታው አልቆ ከምንቆጭ ከሜዳ ውጭ ያለውን ነገር ትተን ወደ ራሳችን ወደ ቀልባችን ተመልሰን ታሪክ መስራት ካለብን አሁን ነው።” እያለ ነገረን። እኛም የምንችለውን እንድርገን ህዝቡን ለማስደሰት ተነጋግረን ወደ ሜዳ ተመለስን።

ሳላዲን ሁለተኛውን ጎል ሲያስቆጠር …

ኡ…! ወዴት እንደሄድኩ አላውቀውም፤ በጣም ከባድ ጥያቄ ነው። ምንም የማቀው ነገር የለም። የማስታውሰው አንድ የውስጥ ስሜቴን ልንገርህ። በቃ የሳላዲን ጎል በተቆጠረበት ቅፅበት ጨዋታው ቢጠናቀቅ ብዬ አስቤ ነበር። (…እየሳቀ)

የጨዋታው ቀሪ ደቂቃ የግብጠባቂው ጀማል ጣሰው ጉዳት እና የአዲስ ህንፃ ግብጠባቂ መሆን…

እንዴ…! የሳላ ጎል ከተቆጠረ በኃላ ጨዋታው ሊጠናቀቅ አስራ ምናምን ደቂቃ የቀረው ሳይሆን ሁለት ሰዓት የቀረው ነበር የመሰለኝ። እንዴ በጣም ከባድ እኮ ነው። ብርድ እንደመታው ሰው እግራችን ይንቀጠቀጥ ነበር። ፍርሀቱ ጭንቀቱ ቀላል አልነበረም። አሁን ሁሉ ነገር አልፎ ስናወራው ቀላል ይመስላል። እንኳን እኛ በመላው ዓለም ይህን ጨዋታ የሚከታተለው ህዝብ እንዴት ይቁነጠነጥ እንደነበረ መገመት ከባድ አይደለም። አስበው ሸክሙን የተሸከምነው እኛ ደግሞ ምን እንደምንሆን። ፈጣሪ ፈቅዶልን ሁሉ ነገር በድል አለቀ።

የዳኛው የጨዋታ መጠናቀቂያ ፊሽካ ሲሰማ…

ኡ ፍ ፍ…! (እየሳቀ) እኔ ወንድ ነኝ፤ የእናቶቻችንን ምጥ አላውቅም። ባለቤቴ ግን ምጥ ምን እንደሆነ ስትነግረኝ አውቃለው። በቃ በሆዳችን የነበረውን ነገር አምጦ የመውለድ ያህል ነው የነበረው ስሜት። ይህ የግል ስሜት፣ ፍላጎት ቢሆን ችግር የለውም ቀላል ነው። ምክንያቱም ብቻህን ነው ጭንቀቱን የምትወጣው፤ ይህ ግን ሀገር ነው። ህዝቡ እንዴት እያበደ እንዳለ ይታወቃል። ያ ሁሉ ኃላፊነት እና ከባዱ ፈተና አልፎ ይህ በመሆኑ ደሰታዬን ለመግለፅ ከባድ ነው። በእግርኳስ ህይወቴ ሁሌም ደስተኛ ነኝ። ይህ ቀን ግን እጅግ በጣም የተለየ ቀን ነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!