በኅዳር ወር አጋማሽ ይጀምራል ተብሎ የተነገረው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ መራዘሙ ሲሰማ ውድድሩ የሚደረግበትም ስታዲየም ታውቋል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከሳምንት በፊት የሴቶች ፕሪምየር ሊግ በኅዳር ወር አጋማሽ እንደሚጀመር ለክለቦች በላከው ደብዳቤ አስታውቆ ነበር። ይህንን የፌዴሬሽኑን መልዕክት ተከትሎም በርካታ ክለቦች ጊዜው መቅረቡን ተንተርሶ ጥያቄዎችን ፌዴሬሽኑ ላይ ሲያቀርቡ ሲሰማ ነበር። በሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ የሊጉን ጅማሮ በተመለከተ ውይይት ያደረገው የሴቶች ልማት እና ውድድር ኮሚቴ የመጨረሻ ውሳኔ ማሳለፉን የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ጌታቸው የማነብርሃን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።
“ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የሴቶች የልማት እና የውድድር ኮሚቴ ኅዳር ወር አጋማሽ ሊጉ ይጀምራል አላለም። ሊጉ ይጀመራል ተብሎ በተነገረበት መንገድ ላይም እኛ ተሳታፊዎች አልነበርንም። እኛ ገና በኮሚቴ ደረጃ ተነጋግረን ውሳኔ ያሳለፍነው ባሳለፍነው ሳምንት ነው። በውይይታችንም የተለያዩ ነገሮችን ከግንዛቤ አድርገን በሰፊው ተነጋግረናል። በዚህም ውድድሩ ታኅሣሥ 10 እንዲጀመር ወስነናል። ታኅሣሥ 10 የሚጀመረው ዋናው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ብቻ ሳይሆን ሁለተኛ ዲቪዚዮን ውድድሩም ነው። ውሳኔያችንንም ክለቦች እንዲያቁ ዛሬ ደብዳቤ እንዲደርሳቸው እናደርጋለን።”
አቶ ጌታቸው አክለውም ውድድሮቹ ሊደረግባቸው የታሰበባቸውን ስታዲየሞች ኮሚቴው መምረጡን አስረድተዋለወ።
“የውድድር ቦታዎች ገና አልተገለፁም። ግን እኛ እንደኮሚቴ የአንደኛ እና ሁለተኛ ዲቪዚዮን ውድድሮች የሚደረጉበትን ቦታ እንደ ሃሳብ ለይተናል። በዚህም ዋና የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ ላይ እንዲደረግ ሁለተኛው ዲቪዚዮን ደግሞ አዳማ ላይ እንዲከወን ወስነናል። እርግጥ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ላይ የሚወዳደሩት ክለቦች የመጀመሪያውን ዙር አዲስ አበባ ላይ ሁለተኛውን ዙር ደግሞ አዳማ ላይ ለማድረግ መርጠው ነበር። ግን አሁን ላይ በአዲስ አበባ የሚገኘው ሜዳ የአበበ ቢቂላ ስታዲየም መሆኑን ብቻ ታሳቢ አድርገን ምርጫቸውን ገልብጠነዋል። ስለዚህ የመጀመሪያ ዙሩ አዳማ ላይ ይከወናል።”
ምክትል ሰብሳቢው አያይዘው የፕሪምየር ሊጉ ሁለተኛ ዙር ውድድር የሚደረግበትን ቦታ ክለቦች እጣ ለማውጣት ጥቅምት 30 ሲጠሩ እንደሚመርጡ ገልፀዋል።
በተያያዘ ዜና የተመረጡ የሊጉን ጨዋታዎች በቴሌቪዥን ለማስተላለፍ ኮሚቴው ስራዎችን እየከወነ እንደሚገኝ ተጠቁሟል። መልካም ፍቃድ ካሳዩ የቴሌቪዥን ተቋማት ጋር ንግግሮችም እየተከናወኑ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!