ሶከር ሜዲካል | ቆይታ ከሽመልስ ደሳለኝ ጋር በኢትዮጵያ እግርኳስ በሚያጋጥሙ ጉዳቶች ዙርያ … (ክፍል አንድ)

የፋሲል ከነማው ፊዚዮቴራፒስት ሽመልስ ደሳለኝ በኢትዮጵያ እግርኳስ የተጫዋቾች ጉዳት እና ህክምናው ዙርያ ያለውን ልምድ ከከሳይንሱ ጋር በማስደገፍ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

በፕሪምየር ሊግ ደረጃ በፊዚዮትራፒስትነት ለሰባት ዓመታት ያገለገለው ሽመለስ ደሳለኝ የህክምና ሙያውን በጎንደር መምህራን ኮሌጅ በጤና እና ሰውነት መጎልመሻ (Health and Physical education ) ዲፕሎማ ከተማረ በኋላ ጎንደር ዩኒቨርስቲ በፊዚዮቴራፒ ዲፓርትመንት ባለሙያነት ሠርቷል። ሽመልስ ከውጭ በመጡ ባለሙያዎች በዩኒቨርሲቲው የፊዚዮቴራፒ ትምህርቱን የተከታተለ ሲሆን በመቀጠል ወደ አዲስ አባባ በመሄድ አሮማ ማሳጅ እና ባዮ ጄኒክ በተባሉ ተቋማት በመምህርነት እንዲሁም ፈርስት ካይሮ ፕራክቲክ የሚባል ተቋም ለተወሰነ ዓመት ከሠራ በኋላ ወደ ጎንደር ተመልሶ በዳሽን ቢራ ሴቶች ቡድን ለአጭር ጊዜ እንዲሁም በወንዶች ቡድን ላይ ለሦስት ዓመታት ማገልገል ችሏል። ዳሽን ሲወርድም ወደ ፋሲል ከነማ ያመራ ሲሆን ያለፉትን አራት ዓመታት ከክለቡ ጋር እየሠራ ይገኛል። ካለው የሥራ ልምድ እና ከሳይንሱ አንፃር እግርኳሱ ላይ የምናያቸውን ችግሮች በተጨማሪ በግሉ እንዴት ተጫዋቾችን እንደሚያክም ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ሰፋ ያለ ቆይታ አድርጓል።

ኢትዮጵያ እግርኳስ በሥራ ላይ በቆየህባቸው ወቅቶች ያጋጠሙህ ከባድ ጉዳቶች እና እንዴት እንዳከምካቸው አጫወተኝ?

እግርኳስ የንክኪ ስፖርት ስለሆነ ግጭቶች ይኖራሉ። ከነዛ ግጭቶች በተጨማሪ ተጫዋቾች ሰውነታቸውን በግባቡ ካለማሟሟቅ ከባድም ሆነ ቀላል ጉዳቶች ያጋጥማቸዋል። ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ የሚጋጥሙህ አብዛኞቹ ተመሳሳይ ናቸው። ለምሳሌ የቁርጭምጭሚት፣ የጉልበት፣ የወገብ እና ጅማት ጉዳቶች ያጋጥሙሃል። እኔ በሥራ ላይ እያለሁ ያጋጠመኝ ከባዱ ጉዳት ወልድያ ከፋሲል በነበረው ጨዋታ ነው። ጨዋታው ላይ ግርግር ተነስቶ የወልዲያ አሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደ ጊዮርጊስን ጨምሮ ዳኞች ተመትተው ሰው ከተጠለለበት ቦታ ለመውጣት ከባድ በነበረበት ሁኔታ የወልዲያው ዳንኤል ደምሱ ተጎድቶ ይወድቃል። በዚህ ሰዓት ግርግርም ቢሆን የህክምና ሙያ ላይ ስትሆን ለራስህ ህይዎት ሳታስብ የሰው ህይወት ለማትረፍ ወደ ሜዳ መግባት ግድ ነበር። ወደ ሜዳ ስደርስ ተጫዋቹ ምላሱ ወደ ኋላ በመመለሱ የመተንፈሻ አካላቱን ዘግቶ ነበር ያገኘሁት። በዛ ቀውጢ ሰዓት ምላሱን አውጥቼለት የተወሰነ የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ ከሰጠሁት በኋላ ራሱን ከሳተበት ከብዙ ድካም በኋላ ተጫዋቹ መንቃት ችሏል። ድንጋጤ ስለነበር ከተረጋጋ በኋላ ደግሞ ይበልጥ ተጎድቶ የነበረው ዳኛውን ሆስፒታል ሄደን ከዶክተሮች ጋር በመተባባር ያዳንበትን አጋጣሚ አስታውሳለሁ።

በጉልበት እና በቁርጭምጭሚት ጉዳት አብዛኞች የሀገራችን ተጫዋቾች ይጠቃሉ። ይህን ከልምድ እና ከሳይንሱ ጋር እንዴት ታስታሙታላችሁ ?

ብዙ ጊዜ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ የሚያጋጥሙ ጉዳቶች ናቸው። እዛ ቦታ ላይ ያሉ ጅማቶች ወይ ይጠማዝዛሉ ወይ ደግሞ በጣም ይለጠጣሉ። እነዛም ሦስት ደረጃ አላቸው። የመጀመሪ ደረጃ፣ ሁለተኛ ደረጃ እና ሦስተኛ ደረጃ ብለን እንከፋፍላቸዋለን። ቁርጭምጭሚት ላይ ያለው ጅማት በተወሰነ ደረጃ ሳብ ሲል የመጀመሪያ ደረጃ ጉዳት ያጋጥማል። ሁለተኛ ደረጃው ደግሞ በግማሽ ይቆረጣል ማለትም የመጀመሪያው ምንም አይነት መቆረጥ አይኖረውም። ሁለተኛው ትንሽ በከፊል ሲቆረጥ ነው። ሙሉ ለሙሉ ሲቆረጥ ወይም ሲዞር ያ ከባዱ የቁርጭምጭሚት ጉዳት ስለሚሆን ሦስተኛ ደረጃ ነው። በቀዶ ጥገናም ነው የሚስተካከለው። የመጀመሪያ ደረጃ  እና ሁለተኛ ደረጃን RICE treatment በሚባለው ስልት ነው ህክምና የምናደርጋቸው። ህክምናው በረዥም ጊዜ እረፍት እና በበረዶ ነው። በረዶ የምንጠቀመው በ48 ሰዓት ውስጥ ነው። ምንም አይነት መታሸት ሳይኖረው በበረዶ ብቻ ነው። እንደዛ ስናደርገው ውስጥ ላይ ያለው የመድማት ሁኔታ ይቆማል። እብጠትም ይቀንሳል። ሌላኛው የተጎዳውን አካል በባንዴጅ መጠቅላል ነው። እሱም እብጠቱ እንዳይጨምር ይረዳዋል። የተጎዳውን አካል ደግፎ ይይዛል። የመጨረሻው እግራችን ወንበር ላይ ሊሆን ይችላል አልጋ ላይ በትራስ ወይ በሌላ ነገር የተጎዳውን እግር ብቻ ከፍ አድርጎ መተኛት ነው። ይሄ ግን በሚሆንበት ሰዓት 45 ዲግሪ መሆን አለበት። ከዛ ከፍም ዝቅም ማለት የለበትም ማለት ነው። ይሄን ለ48 ሰዓታት ከሰጠን በኋላ በሞቀ ውሃ ሊሆን ይችላል በሌላ ሂት ቴራፒ በመጠቀም ቴክኒካል ማሳጆችን በመስጠት እንዲሁም አንዳንድ ጥንካሬን የሚጨምሩ እንቅስቃሴዎች በማሰራት አመጋገቡን በማስተካከል ወደ ነበረበት አቋም ወደሚወደው ስፖርት እንዲመለስ እናደርገዋለን። ሦስተኛ ደረጃውን መታሻም ምንም ነገር አናደርግም። በቀዶ ጥገና ሆስፒታል ላይ ነው የሚደረግላቸው። እኛ የመጀመሪያ ደረጃ ነው ሁለተኛ ደረጃውን ሦስተኛ ነው የሚለውን አይተን ሦስተኛው ከሆነ ወደ ሆስፒታል በፍጥነት ይዘን እንሄዳለን። ይሄ ክለቦች እንዳላቸው ባለሙያ ባላቸው እውቀት ልክ ይለያያል። አብዛኞቹ ግን ይሄን ነው የሚጠቀሙት።

እዚህ ላይ ምን አለ መሰለህ አንድ አንድ ተጫዋቾቾ ጨዋዎች ናቸው። ባለሙያ ያከብራሉ፣ የሚባሉትን ይሰማሉ። አንድ አንድ ተጫዋቾች ደግሞ ለመጫወት ካለቸው ጉጉት የተነሳ የባለሙያ ምክር ካለመስማት የከፋ ችግር ያጋጥማቸዋል። የመጀመሪያ ደረጃ አጋጥሟቸው ካላሸኸኝ ብለው ያስቸግራሉ። ብዙ ባለሙያ ሲያሻቸው የመጀመሪያው ወደ ሁለተኛ ይሄዳል። ሁለተውም እንዲሁ ወደ ሦስተኛው ይሄዳል። ቶሎ ማገገም እየተቻለ ጉዳቱን ለረዥም ጊዜ ያደርጉታል። እና በተጎዱ ወቅት ተጫዋቾች የባለሙያን ምክር መስማት አለባቸው ።

ካሉት ጉዳቶች ሁሉ ከበድ ይላል ከሚባሉት ውስጥ የጉልበት ጉዳት ነው። ጉልበት በጣም ውስብስብ እና ከባድ ነው። የጅማት ጉዳት ከሆነ ተመሳሳይ ነው ትሪትመንቱ። የጉልበት ጉዳት ሲገጥማቸው እስከ ዘጠኝ ወር ድረስ የሚደርስ እረፍት ያስፈልጋቸዋል። ከጅማት ጉዳት ውጭ የሆኑ የጉልበት ጉዳቶች በራጅ ከታዩ በኋላ እኛ ማከም የምንችለውን እናክማለን። የራጅ ውጤቱን አይተን ከባድ ከሆነ ሆስፒታል ላይ ትሪት ይደረጋሉ።

የጉልበት ጉዳት በብዛት የሚያጋጥማቸው ተጫዋቾች በአብዛኛው ከሜዳ ችግር ነው። ጉርብጥብጥ ያለ ምንም የማይመች ሜዳ ያላቸው ክለቦች አሉ። ያ በጣም አስቸጋሪ ነው። የሚጠቀሙት ጫማ የሚሰራው ለምቹ የሳር ሜዳ ነው። አስቸጋሪ ሜዳ ላይ በዛ ጫማ ሲጫወቱ የመታጠፍ እድላቸው ሰፊ ነው። ጅማት መቆረጥ ከመጠን በላይ መለጠጥ የሚያጋጥማቸው ከነዚህ አንፃር ነው። በግጭትም የጉልበት ጉዳት ይፈጠራል። ግን ለአብዛኞቹ የሀገራችን ተጫዋቾች ጉዳት መንስኤው ይበልጡን የሜዳ ችግር ነው።

ብዙ ጊዜ ተጫዋቾች ወደ ልምምድ ወይም ወደ ጨዋታ ሲገቡ ሰውነታቸው እንዲሞቅ በሜንዛ አይስ የመታሸት ነገር አለ። ይህንን ከሙያ አንፃር እንዴት ታየዋለህ ?

እንደ ባለሙያ አልቀበለውም። ተጫዋቾች እንደሚያስቡት በነሱ መንገድ ትክክል ነው። እንደ ባለሙያ ግን ልክ አይደለም። ምክንያቱም እነሱ በሜንዛ የሚታሹት ጡንቻቸው እንዲሞቅ ብለው በማሰብ ነው። አሁን ፋሲል ከነማ ላይ እንደዛ አናደርግም። ምክንያቱም በባለፈው ዓመት ይታገሱ የሚባል የአካል ብቃት አሰልጣኝ ነበር። አሁንም ሙሉቀን አቡሃይ የተባለ የአካል ብቃት አሰልጣኞች ስላሉ ተጫዋቾች በደንብ ሙቋቸው ነው የሚገቡት። ስለዚህ እንደዛ አናደርገም። ያም ሆንህ ሰውነት በአርቲፊሻል ነገር መሞቅ የለበትም። ተገቢውን እንቅስቃሴ በማድረግ ነው መሞቅ ያለበት። ሌሎችም ክለቦች ይህንን ቢጠቀሙ መልካም ነው።

ፊዚዮቴራፒ እና ማስጅቴራፒ ልዩነትቻው ምንድነው? እንዴት ነው የምታስኬዱት?

በፊዚዮቴራፒ እና በማሳጅ ቴራፒ መሐል ያለው ልዩነት ፊዚዮቴራፒ መሳሪያዎች እና ማሽኖችን በመጠቀም እንዲሁም የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በመጠቀም የምታክምበት የህክምና ስልት ነው። ለምሳሌ ኢንፍራሪድ እና ኤሌክትሮ ቴራፒ የሚባሉ እጅግ ዘመናዊ መሳሪያዎች አሉ። ሀገር ውስጥ አብዛኞቹ አንድ አንድ ቦታ ላይ ነው የሚገኙት። ማሳጅ ቴራፒ ማለት ያለምንም መድሃኒት ያለምንም መርፌ ማሽኖችን ሳትጠቀም በእጅ ብቻ በሚደረግ የህክምና ጥበብ እና ዘዴ ሰዎችን ፈውስ የምትሰጥበት ሰዎችን ድካማቸውን የምታላቅቅበት ነው። ለአንድ ክለብ ደግሞ ማሳጅ ቴራፒ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ተጫዋቾች ከጨዋታ በፊት፣ ከጨዋታ በኋላ፣ ከልምምድ መልስ ጡንቻቸው እንዲፍታታ ከጨዋታ በኋላ ድካማቸው እንዲለቃቸው፣ አንዳንዴ እረፍት አድርገህ እንኳን በእረፍት የማይወጣ ድካም አለ። እሱ በማሳጅ በደንብ ነው የሚለቀው። ቆንጆ ማሳጅ ሲያገኙ ከፍተኛ የሆነው የድካም ስሜት ይለቃቸዋል ።

በአንድ እግር ኳስ ክለብ ውስጥ አንድ የህክምና ባለሙያ ብቻ በቂ ነው ብለህ ታምናልህ ?

እኔ አንድ ክለብ ውስጥ አንድ ባለሙያ ብቻ መኖር አለብት ብዬ አላምንም። የውጭ ክለቦች አይተህ ከሆነ በርካታ የህክምና ባለሙያ ነው የሚኖራቸው። እኛ ጋር ደግሞ አንድ ባለሙያ ነው የሚኖረው። በርግጥ ሁለት ባለሙያ ያላቸው አሉ። እኔም አንድ ክለብ ቢያንስ ሁለት ባለሙያ ቢኖረው ጥሩ ነው እላለሁ። የህክምና ቡድን ሰፊ ነው መሆን ያለበት። አንድ የማሳጅ ቴራፒ እንዲሁም የፊዚዮትራፒ ባለሙያ ያስፈልጋል።

ከሴቶች ከወንድ ተጫዋቾች የትኛው ጋር ጉዳት ያስቸግራል? ከሴቶች ጋር መሥራት እና ከወንዶች ጋር መሥራቱ የቱ ነው ከባድ ?

ተፈጥሮም ይናገራል፤ ሴቶቹ ይጎዳሉ። የወንድን ያህል ጥንካሬ ስለማይኖራቸው ማለት ነው። በተክለ ሰውነት ጥንካሬ ከወንድ ጋር አይነፃፀሩም። በተጨማሪ ሴቶቹ ጉዳት የሚበዛባቸው ልምምድ የሚሰሩበት ቦታ እንደ ወንዶች ምቹ ባለመሆኑ ነው። በአጠቃላይ የወንዶችን ያህል ክብር አልተሰጠውም። የሴቶች እግርኳስ በአብዛኞቹ ክለቦች ደሞዝ ዝቅተኛ ነው። ሲጎዱ ራሳቸውን ለመጠበቅ አይሆናቸውም። እንደ ወንዶች እግርኳስ ትኩረት ቢሰጠው ጥሩ ነው። ምክንያቱም ለጉዳት ከፍተኛ ተጋላጭ ከመሆናቸው በላይ በቂ ትኩረት ካላገኙ እግርኳሱ እድገት አይኖረውም። ሌላው የሙያ ሥራ እስከሆነ ድረስ ከወንድም ጋር ሆነ ከሴት ጋር ህፃናትም አዛውንትም ቢሆን ሙያው በሚያዘው መሥራት ነው። በፋሲል ከነማ ሴቶች እና ታዳጊዎች ሲጎዱ ከሁሉም ጋር በግልም ካምፕ ድረስ ሄጀ ሴቶችን አክማቸዋለሁ። ከሁሉም ጋር ደስተኛ ሆኜ ነው የምሰራው። ባለሙያ እስከሰሙ እና እስከታዘዙ ድረስ ከየትኛውም ተጫዋች ጋር  መስራት ቀላል ነው። የሚከብድ ነገር አይኖረውም ።

የራስህ የህክምና ፌስቡክ ገፅ አለህ። ሰዎች ምን ያህል ይከታተሉታል? ምን ያህል ጊዜ ሆነህ? ለመጀመር ምን አነሳሳህ ? ፔጁ ላይ አይተው የደወሉልህ ተጫዋቾች ወይም የህክምና ባለሙያስ አሉ ?

አዎ። ያንን ፔጅ የከፈትኩት ዳሽን ቢራ እያለሁ ነው። አሁን ስሙን ቀይሬ ሽሜ የፋሲል ከነማው ፊዚዮትራፒ ነው የሚለው። ስከፍተው ገንዘብ አገኝበታለሁ ብዬ ወይም ሌላ ነገር አስቤ ሳይሆን ያለኝን እውቀት ለሰዎች ለማካፈል ነው። ለብዙሃን ህክምና ማግኘት ለማይችሉ ሰዎች በራሳቸው ከቤታቸው ሆነው እንዲያክሙ አስቤ ነው። ከከፈትኩት በኋላም በጣም ብዙ ሰዎች ያበረታቱኛል። ለምን የራስህን ተቋም ከፍተህ አትሰራም ይሉኛል። እየደወሉልኝ ሄጄ በግል ያከምኳቸውም አሉ። ቤትም መጥተው የከተማው ሰዎች አንዳንድ አገልግሎቶችን በበጎ ፍቃደኝነት እሰጣቸዋለሁ። ሰፈር ላይ የተጎዱ ሰዎችም ከደወሉልኝ ሄጀ ድጋፍ አደርጋለሁ።

ፔጁን ባለሙያዎች ያዩታል። የሌላ ክለብ ወጌሻዎች የሲዳማ ቡና ለምሳሌ ያወራኛል አይዞህ በርታ እያለ ያበረታታኛል። እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡና እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወጌሻ ይስሐቅ ሽፈራው በጣም ያበረታታኛል። አቅም ያለህ ልጅ ነህ በግልህ ለምን አትሰራም። የግልህን ክፈትና እኔም ቢሆን ለተወሰነ ጊዜ ጎንደር መጥቼ አግዝሀለሁ። የምትፅፈውንም አነባለሁ ይለኛል። ለወደፊቱ የራሴን ከፍቼ እሰራለሁ። እኔም የሶከር ሜዲካልን አምድ እከታተላለሁ። በርካታ ልምዶችን ጠቃሚ ምክሮችን በተለይ እግርኳሱ ላይ ያሉ ጉዳቶችን ስለምትዳስሱ የናንተን ገፅ እከታተላለሁ። ለእግር ኳሱ እድገት በየትኛውም መስክ የምታደርጉትን እንቅሰቃሴ ሳላደንቅ አላልፍም።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!