አሰልጣኝ ምንተስኖት ጌጡ የት ይገኛል ?

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከዕይታ የራቁ የእግርኳሱ ሰዎችን በምናቀርብበት ”የት ይገኛሉ” ዓምዳችን በርካታ ተጫዋቾችን ስናቀርብ መቆየታችን የሚታወቅ ሲሆን በቀጣይ ደግሞ ከተጫዋቾች በተጨማሪ አሰልጣኞች እና ሌሎች በእግርኳሱ ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦችን የምናቀርብ ይሆናል። ለዛሬም ከምንተስኖት ጌጡ ጋር ቆይታ አድርገናል።

በጎንደር ከተማ በቀበሌ 09 ተወልዶ ያደገው አሰልጣኝ ምንተስኖት ጌጡ እግርኳስን በሰፈር ውስጥ የሚገኙ ታዳጊ ቡድኖች የጀመረ ሲሆን በትምህርት ቤት ወድድሮች እና በ1990 በተጀመረው የፕሮጀክት ውድድር ላይ በመመረጥ ለዞን እንዲሁም ለክልል በድሬድዋ እና በአዳማ ውድድሮች ተጫውቶ አሳልፏል። አሰልጣኙ ለአንድ ዓመት ለፋሲል የተጫወተውን ጨምሮ ለሰባት ዓመታት እግርኳስን ከተጫወተ በኋላ በፋሲል ከነማ ከታችኛው የሊግ እርከን እስከ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ድረስ በዋና አሰልጣኝነት እና በምክትል አሰልጣኝነት ለበርካታ ዓመታት አሳልፏል። አሰልጣኝነትን በ1997 የጀመረው ምንተስኖት ጌጡ የካፍ ኤ ላይሰንስ ያለው ሲሆን በስፖርት ሳይንስ ዲፕሎማውን ይዟል። በ2010 ዓ.ም ከፋሲል ከነማ ጋር ከተለያየ በኋላ ከዕይታ የራቀው አሰልጣኙ አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እና ስለ ቀጣይ እቅዱ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጓል።

አሰልጣኝ ምንተስኖት ጌጡ አሁን በምን ሁኔታ ትገኛለህ ?

ከፋሲል ከነማ ከተለያየሁ በኋላ ያለፉትን ሁለት ዓመታት እግርኳስ ውጪ በግል ሥራዎችን እየሰራሁ ነው ያሳለፍኩት። በተጨማሪም ከማስተር ተዋበ ጋር ኤሮቢክስ በሳምንት ሦስት ጊዜ እናሰራለን። እግርኳሱ ላይም የማቀውን ነገር ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት ነው ይህን ሁለት ዓመት ያሳለፍኩት ።

በምን ሥራ ተሰማርተህ ትገኛለህ ? ከእግርኳስ ጋር ሲነፃፀርስ እንዴት ነው?

እንደነገርኩህ በርካታ ሥራዎችን ነው በግሌ ስሠራ የነበረው። ከእግርኳስ ውጭ የሆኑ ስራዎችን ነው ስሰራ የነበረው። ያለፉትን ሁለት አመታት እግዛብሔር የተመሰገነ ይሁን ጥሩ ነበር ።

የግል ሥራ ሰዓት ተመድቦለት የምትሰራው አይደለም። ሳትጨናንቅ ምትሰራው ስራ ነው። ኤሮቢክሱ እንደ ነገርኩህ በሳምንት ሶስት ቀን ነው። አራት ቀን እረፍት ነኝ። ኤሮቢክስ መስራቱም ከጤና አንፃር እና ከስፖርቱ ላለመራቅ ጠቃሚ ነው።

ከአሰልጣኝነት የራቅክበት ምክንያት ምንድነው?

ከአሰልጣኝነት የራኩበት ምክንያት አንደኛ ያለንበት ወቅታዊ ሁኔታ ወጥተህ እንድትሰራ አይጋብዝህም። በተጨማሪም ትንሽ የተመሰቃቀለ ስለሆነ ወጥተህ ለመስራት ከባድ ነው። እዚህ ደግሞ ፋሲል ከነማ ብቻ ነው ያለው። ዋና አሰልጣኝ አለ ክለቡ ላይ የኛ ልጆች የሆኑ ምክትሎች አሉ። የግድ በውስን ሰዎች ስለሚመራ እዚህ መስራት አልቻልኩም። ለዛ ነው የራቅኩት ።

ከአሰልጣኝነት ለመራቅ እንዴት ወሰንክ ?

ከአሰልጣኝነት ሙያ መቸም ቢሆን የምርቅ አይመስለኝም። ሲጀመር አሰልጣኝነት ስለፈለከው የምትሆነው ሳይሆን ከፈጣሪ የሚሰጥህ ነገር ነው። እና ብዙ ፈተናዎች ይኖራሉ። እነዛን ፈተናዎች መቋቋም እና መወጣት ነው ። ስለዚህ ይሄም ጊዜ ከፈተናዎች መሃል አንዱ ነው። አቅም ደግሞ ፈጣሪ ሰጥቶኛል ብዬ ስለማምን ነገ ትልቅ ስራ እንደምሰራ አምናለሁ። ጠንካራ ፈላጎት እና ተነሳሽነት ስላለኝ ምንም አይነት ወሳኔ አልወሰንኩም ።

ስለዚህ ወደ አሰልጣኝነት ለመመልስ ታስባለህ?

አዎ የስራ እድሉን ባገኝ እመለሳለሁ፤ እየተንቀሳቀስኩም ነው። ቁጭ አላልኩም ራሴን ለማሳደግ ጥረቶችን በማድርግ ላይ ነኝ። አነባለሁ፣ ኮርሶችን ስልጠናዎችን በመውሰድ ላይ ነበርኩ። ለምሳሌ ከጀርመን የመጡ አሰልጣኞች የሰጡን ስልጠና ተካፍያለሁ። ከእግርኳሱ በቀጥተኛ መንገድ ባልገናኝም ራሴን ለማሻሻል ጥረት ሳደርግ እና ትላልቅ አሰልጣኞች ጋርም በመጠየቅ ልምድ ስወስድ ነበር። ወደ አሰልጣኝነት ብመለስ እቸገራለሁ ብዬ አላስብም። ይበልጥ የተሻለ ነገር እሰራለሁ።

ባለፉት ዓመታት የማሰልጠን ዕድል ገጥሞህ ነበር?

አዎ አጋጥሞኝ ነበር። አብሮኝ የአሰልጣኞች ኮርስ የወሰደ ልጅ ወደ ደቡብ ክልል ተጉዘን አብረን እንድሰራ ጠይቆኝ ነበር። በአንዳንድ ምክንያቶች አልተሳካም። እንዲሁም አዳማ አንድ ጓደኛዬ ጋር አውርተን ወደዛ ለመሄድ አስቤ ነበር። ነገር ግን አንዳንዴ ነገሮችን አንተ ብቻህን አትወስንም። ቤተሰብ አማክሬ ይህን ዓመት እዚሁ መቆየት የተሻለ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ለልጁ ጥሩ መልስ መልሼለት እዚሁ ቀርቻለሁ፤ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር።

ወደ አሰልጣኝነት ስትመለስ ማሳካት የምትፈልገው የአጭር እና የረዥም ጊዜ ግብህ ምንድነው?

እቅዶች አሉኝ። ግን እንደምይዘው ክለብ ይወሰናል። ከታች ያለ ክለብ ከሆነ ወደ ላይ የማምጣት ሊሆን ይችላል። የተለያዩ ግቦች ይኖሩሃል። በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ከሆነ ደግሞ እንደ ክለቡ ፋይናንስ ይወሰናል። ቢሆንም ግን ለዋንጫ የሚጫወት ቡድን ነው መስራት የምፈልገው። ፋሲል ከነማን ብረከብ ሁለተኛ እወጣለሁ ሶስተኛ እወጣለሁ ሳይሆን ዋንጫ ለማምጣት ነው የመጀመሪያ አላማዬ።

በእግርኳስ የማትረሳው አጋጣሚ ?

በእግርኳስ የማልረሳው አጋጣሚ ሀምሌ 13 ቀን 2008 ነው። ፕሪምየር ሊግ የገባንበት አጋጣሚ ነበር። ያን ጊዜ በእግርኳስ አልረሳውም።

ኢትዮጵያ ውስጥ የምታደንቀው አሰልጣኝ ?

ኢትዮጵያ ውስጥ የማደንቀው ለኔ እንደ ሞዴል የምወስደው በእውቀትም በስብዕናም ጥሩ አሰልጣኝም እንዲሁም ከ ሲ ላይሰንስ አንስቶ እስከ ኤ ላይሰንስ ያሰለጠነኝ ኢሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ነው። ከውጭ ሃገር በጣም የምከታተለው በርካታ ነገሮችን የምወስደው ፔፕ ጓርዲዮላ ነው። የፔፕ አድናቂ ነኝ ።

በመጨረሻ…

በርካታ ማመስገን የምፈልጋቸው አሉ። በመጀመሪያ ፋሲል ከነማን ማመስገን እፈልጋለሁ። በርካታ ነገር አድርጎልኛል፣ አስተምሮኛል፣ ለዚህም ያበቃኝ ክለቤ ነው። ሞሮኮ ድረስ ሄጀ ስልጠና ወስጃለሁ። ከመጀመሪያ ጀምሮ ያሳደገኝ ክለቤ ነው። በመቀጠል ኢሊት ኢንስትራክተር አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱን ማመስገን እፈልጋለሁ። በመቀጠል አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ቀርበን ባንነጋገርም ለፋሲል ከነማ አድርጎት በሄደው ነገር እሱንም ማመስገን እፈልጋለሁ። ሌላው አብረውኝ ሲሰሩ ለነበሩት የአሰልጣኞች አባላት በአጠቃለይ ማመስገን እፈልጋለሁ። ሌላው እኔ በሥራ ላይ እያለሁ ለክለቡ እገዛ ሲያደረጉ ከነበሩት ውስጥ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ፣ የጎንደር ከተማ ከንቲባ ተቀባ ተባባል እና ማተሚያ ቤት ሃላፊ አቶ ነጋ እንዲሁም ከደጋፊዎች ማህበር ስራ አስፈፃሚ ደግሞ ጌትሽ ጋሹ እና አበበ ገብረመስቀልን በጣም ለክለቡ ድጋፍ ሲያደርጉ ነበር። በተጨማሪ በግል ምክትል እያለሁ ኮን እንድተክል ሳይሆን ልምድ እንዳገኝ ስልጠናዎችን እንድሰጥ በብዛት እድሎችን ሲሰጠኝ ስለነበር ዘማርያም ወልደጊወርጊስን ማመስገን እፈልጋለሁ። በተጨማሪ 2010 ዋናው ቡድን አሰልጣኝ ባለሁበት ወቅት ሀብታሙ ዘዋለ በብዙ ነገሮች ሲያግዘኝ ስለነበር በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!