በአጨዋወቱ ምክንያት የበርካታ የእግርኳስ ቤተሰቦች ቀልብ የሳበው ሚኪያስ መኮንን በዛሬው የዘመናችን ከዋክብት ገፅ ላይ እንግዳ አድርገነው አዝናኝ ጥያቄዎችን አቅርበንለታል።
አበባ ሰሜን ሆቴል አካባቢ ተወልዶ ያደገው ሚኪያስ እንደአብዛኞቹ ተጫዋቾች በእግርኳስ የተለከፈው ገና በልጅነቱ እያለ ነበር። በተለይ ተወልዶ ባደገበት አካባቢ ጉቶ ሜዳ የሚባል የመጫወቻ ሜዳ ስለነበረ እግርኳስን በቀላሉ ይጫወት እንደነበረ ያወሳል። ሚኪያስ ከምንም በላይ ወላጅ አባቱ ለእግርኳስ ልዩ ፍቅር ስለነበራቸው ልጃቸውን ወደሚወዱት ሙያ እንዲገባ ይገፋፉት እንደነበር ያስታውሳል። በዚህም ሳፍሪ በተባለ የሠፈሩ የፕሮጀክት ቡድን ውስጥ ተይዞ ራሱን ማጎልበት ያዘ። ተጫዋቹ በፕሮጀክቱ ወደ እግርኳሱ በደንብ መቅረብ ከጀመረ በኋላ ቀጣይ መዳረሻውን የሀረር ሲቲ ከ17 ዓመት በታች ቡድን በማድረግ ወደ ታላቅነት የሚያርገውን ጉዞ ማሳመር ቀጠለ። በሀረር ሲቲም ለሁለት ዓመታት ከቆየ በኋላ የኢትዮጵያ ቡናን የታዳጊ ቡድን ለማገልገል የመዲናውን ክለብ ተቀላቀለ። በክለቡም ለጥቂት ጊዜያት በታዳጊ ቡድኑ ግልጋሎትን ከሰጠ በኋላ ወዲያው ወደ ዋናው ቡድን በማደግ የብዙዎች ዐይን ውስጥ መግባት ቻለ። በዚህም ከ2009 ጀምሮ በቡናማዎቹ ቤት ድንቅ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል።
2008 ላይ ለሀረር ሲቲ እየተጫወተ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገሩን እንዲያገለግል በአሠልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ ጥሪ ቀርቦለት የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች የሆው ሚኪያስ በመጀመሪያ ጨዋታው ግብፅ ላይ ድንቅ ብቃቱን በማሳየት አንድ ጎል አስቆጥሮ አድናቆትን አግኝቷል። ከዛም ከ20 ዓመት በታች እና የኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድኑን በደረጃ በማገልገል በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋናውን የዋሊያዎቹ ስብስብ እንዲቀላቀል ጥሪ ቀርቦለታል። በአሁኑ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ውበቱ አባተም ጥሪ የቀረበለት ተጫዋቹ እስካሁን ግን በዋና ብሔራዊ ቡድን ደረጃ ምንም ጨዋታ አላደረገም።
“ሚኪ-ዲኒሆ” እያሉ በርካታ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች የሚጠሩት ይህ “የዘመናችን ኮከብ” ተጫዋች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን ቆይታ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
የእግርኳስ አርኣያህ ማነው?
ከሀገር ውስጥ ከሆነ መስዑድ መሐመድን እንደ አርኣያ እመለከት ነበር። እርግጥ ብዙ ስታዲየም እየገባሁ አልመለከተውም ነበር ግን ከሚነገረው እና ከሚሰማው ነገር በመነሳት መስዑድን በደንብ አደንቀው ነበር። 2009 ላይም ወደ ዋናው ቡድን ሳድግም ስመለከተው ድንቅ ነበር።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በኮቪድ-19 ምክንያት ከተቋረጠ በኋላ ጊዜህን በምን እያሳለፈ ነው?
አብዛኛውን ጊዜዬን ቤት ውስጥ ነበር የማሳልፈው። በሽታውም ማኅበራዊ ነገሮችን የሚገድብ ስለሆነ እንቅስቃሴዬን ቆጥቤ ነበር። አንዳንድ ጊዜም በጥንቃቄ ከጓደኞቼ ጋር እየተገናኘን ጊዜ እናሳልፍ ነበር።
ኮሮና ከመጣ በኋላ የለመድከው ምን አዲስ ልማድ አለ?
በፊት በፊት እቤት ብዙ አልውልም ነበር። ውድድርም ስለሚኖር ካምፕ ወይንም ለጨዋታ ከከተማ እወጣ ነበር። ይህ በሽታ ከመጣ እና እግርኳስ ከተቋረጠ በኋላ ግን ውሎዬ ከቤተሰብ ጋር ሆኗል። እና በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ከቤተሰብ ጋር ጊዜን ማሳለፍ ለምጃለሁ።
ኮሮና አሁን ጠፋቷል ብትባል መጀመሪያ የምታረገው ነገር ምንድን ነው?
አሁን ላይ ይህንን ጥያቄ መመለስ ከባድ ነው። ግን ገደብ ተጥሎባቸው የነበሩትን ነገሮች እማደርግ ይመስለኛል። መጨባበጥ፣ መተቃቀፍ የመሳሰሉትን። በዋናነት ግን ከጓደኞቼ ጋር ተሰባስበን እንጨዋወት ነበር። እግርኳስንም ያለ ገደብ በደጋፊዎች ታጅበን እንጫወት ነበር።
በግልህ ጥሩ ጊዜ ያሳለፍክበት ዓመት መቼ ነው?
2010 ላይ የነበረኝ ነገር ምርጥ ነበር። በወቅቱ ዲዲዬ ጎሜዝ ነበር አሠልጣኛችን። ቡድኑም በዓመቱ ሦስተኛ ሆኖ ነበር ያጠናቀቀው። እኔም በተለይ በሁለተኛ ዙር በየጨዋታው እየተሰለፍኩ እጫወት ነበር። እና ይህ ዓመት በቋሚነት ቡናን በጥሩ ብቃት ማገልገል የጀመርኩበት ስለነበረ ለእኔ ጥሩ ዓመት ነበር።
ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችህ ምንድን ናቸው?
ጠንካራ ጎኖቼን እንተዋቸው እና እኔ ብዙ ደካማ ጎኖች አሉብኝ። በተለይ ራሴን ለማጎልበት በግሌ ልምምዶችን መስራት እንዳለብኝ ይሰማኛል። በተጨማሪም በጨዋታ ላይ ጎሎችን ማስቆጠር መቻልን መልመድ አለብኝ። እነዚህ በዋናነት እኔ እንደ ድክመት የማያቸው ጎኖቼ ናቸው።
ሚኪያስ እግርኳስ ተጫዋች ባይሆን ምን ይሆን ነበር?
አላቅም። ከእግርኳስ ውጪ ምንም ፍላጎት የለኝም። ሲጀምርም አስቤበት አላቅም። እኔ ለእግርኳስ ነው የተፈጠርኩት።
ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ላይ ሆነህ ግብፅ ላይ ያስቆጠርካት ጎል የማትረሳ ነች። እስቲ ስለዚህች ጎል የሆነ ነገር በለኝ?
ጎሏን እስካሁን ድረስ ሳስባት ደስ የምትለኝ እና መቼም ከአዕምሮዬ የማትጠፋ ነች። የጎሏ ውበት ብቻ ሳይሆን በልጅነቴ ለሃገሬ ያስቆጠርኳት ጎል ስለነበረች ጥሩ ስሜት ትሠጠኛለች። ሁሌም ስለዚህች ጎል ሳስብ ደስታ ይሰማኛል።
ኳስ የምትገፋበት መንገድ በጣም የሚያስገርም ነው። በተጨማሪም ያለህ የራስ መተማመን ከእድሜህ በላይ ይመስላል። እነዚህን ሁለት ነገሮች በምን መልኩ ነው ያዳበርካቸው?
የተፈጥሮ ነገር ይመስለኛል። ቀድሜ እንዳልኩህ ጠንካራ ልምምዶችን ብዙም አልሰራም። ግን በተፈጥሮ ያገኘሁትን ነገር እያጎለበትኩ ነው እዚህ የደረስኩት። ግን አንተም እንዳልከው ደጋፊዎች በዚህ ብቃቴ ቢያደንቁኝም ከዚህ የበለጠ ማሻሻል እንዳለብኝ ይሰማኛል።
የራስህ አጨዋወት ከማን ጋር የሚመሳሰል ይመስልሃል? ከሃገር ውስጥም ሆነ ከውጪ ካለ ተጫዋች ጋር…
የግራ እግር ተጫዋቾች በጣም ይመቹኛል። በተለይ እንደ ሜሲ እና ማህሬዝ የመሳሰሉት ይመቹኛል። ራሴን ከእነሱ ጋር እያነፃፀርኩ እና እያመሳሰልኩ አደለም። ግን በተወሰነ እነሱን ለመምሰል ነው እኔም የምጫወተው። ከሃገር ውስጥ ግን አላቅም። ስታዲየም ገብቼ ብዙም ጨዋታ ስለማልከታተል ብዙ ተጫዋቾችን አላቅም።
ከአቡበከር ጋር ስላለህ የጓደኝነት ህይወት አጫውተኝ እስኪ…
ከአቡበከር ጋር ከልጅነታችን ጀምሮ ነው አብረን ያደግነው። ያለን ግንኙነት ከጓደኛማማችነት አልፎ ወደ ወንድማማችነት ተቀይሯል። ከሀረር ሲቲ ጀምሮ በቡናም ቤት አብረን ነው የምናሳልፈው። ላለፉት ሠባት ዓመታት እንኳን አንድ ክፍል ውስጥ ነው የምናድረው። ብዙ ጊዜም አብረን ነው የምናሳልፈው። በአጠቃላይ ግን በጣም የምንዋደድ ወንድማማቾች ነን።
አብሬው ተጣምሬ መጫወት እፈልጋለሁ የምትለው ተጫዋች አለ?
ይኖራል። በተለይ ከዳዊት እስቲፋኖስ ጋር ብጫወት ደስ ይለኛል። ከዳዊት ጋር በተቃራኒ ብዙ ጊዜያት ተጫውተናል። አሁንም ብሔራዊ ቡድን ላይ በጉዳት እስኪወጣ ድረስ አብረን ተጫውተናል። ግን በክለብ ደረጃ ለረጅም ጊዜ አብሬው ተጣምሬ ብጫወት ደስ ይለኛል።
በተቃራኒ ስትገጥመው የሚከበደህ ተጫዋች ይኖር ይሆን?
እንደምታቀው ብዙ የጨዋታ ጊዜ አላሳለፍኩም። ከዚች ትንሽ ጊዜ ውስጥ ደግሞ ይሄንን ያህል ይከብደኛል የምለው ተጫዋች አይኖርም። ግን በአንፃራዊነት አስቻለው ታመነ ከባድ ተጫዋች ነው። ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለብዙ ሀገራችን አጥቂዎችም የአስቻለው ብቃት ከባድ ነው።
በዚህ ሰዓት በሃገራችን ከሚገኙ ተጫዋቾች ያንተ ምርጡ ተጫዋች ማነው?
ጓደኛህ ስለሆነ ነው አትበሉኝ እንጂ በዚህ ሰዓት በሀገራችን ከሚገኙ ተጫዋቾች ምርጡ አቡበከር ነው።
ከአሠልጣኞችስ…?
እኔን በርካታ ምርጥ ምርጥ አሠልጣኞች አሰርተውኛል። የተሻለ እንድሆንም ደግፈውኛል። ግን ካሳዬ አራጌ እስካሁን ካየኋቸው አሠልጣኞች ውስጥ ምርጡ አሠልጣኝ ነው። እሱም እያሠለጠነኝ ስለሆነ አደለም። ጥሩ እና የተሻለ አቅም ስላለው ነው። እንዳልኩት ግን ሌሎችም ምርጥ ምርጥ አሠልጣኞች አሠልጥነውኛል።
በእግርኳስ በጣም የተደሰትክበትን አጋጣሚ አውጋኝ?
በእግርኳስ የተደሰትኩባቸው አጋጣሚዎች ብዙ አሉ። ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ለብሔራዊ ቡድን ተጠርቼ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑን ወክዬ ስጫወት ደስታ ተሰምቶኛል። በጨዋታውም ግብፅን ስናሸንፍ ጎል በማስቆጠሬ ትልቅ ሀሴት ተሰምቶኛል። በተጨማሪም ለኢትዮጵያ ቡና የመጀመሪያ ጨዋታዬን ሳደርግ በጣም ነበር የተደሰትኩት። ወቅቶቹን መቼም አልዘነጋቸውም።
እርግጥ ገና ቢሆንም እግርኳስ ካቆምክ በኋላ ምን ለመሆን ታስባለክ?
ፈጣሪ በሠላም ያድረሰንና እግርኳስ ካቆምኩ በኋላ ወደ ንግዱ ዓለም የምገባ ይመስለኛል።
ቅፅም ስም አለህ እንዴ?
በይፋ የወጣ ቅፅል ስም የለኝም ግን አንዳንድ ደጋፊዎች ‘ሚኪ-ዲኒሆ’ ይሉኛል። የእኔን ስም እና የሮናልዲኒሆን በማጋጨት ያወጡልኝ ስም ነው።
ከኳስ ውጪ ሌላ ምን የተለየ ችሎታ አለህ?
ምንም የለኝም። ለዛም ነው ቅድም ለእግርኳስ ብቻ ነው የተፈጠርኩት ያልኩህ። ምንም ውስጥ የለሁበትም።
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!