ኢትዮጵያ 2-3 ዛምቢያ | የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ድሕረ ጨዋታ አስተያየት

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከዛሬው የብሔራዊ በድኑ የወዳጅነት ጨዋታ መገባደድ በኋላ በZoom አስተያየቶቻቸውን ሰጥተዋል።

የኮቪድ 19 ወረርሺኝ ከተከሰተ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ጨዋታውን አድርጓል። ቡድኑ ከዛምቢያ ጋር ባደረገው በዚህ ጨዋታም 3-2 ተሸንፏል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም አዲሱ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በZoom ከሚዲያ አካላት ጋር ቆይታ አድርገዋል። በቆይታቸው ካተኮሩባቸው ነጥቦች መሀከል ዋነኞቹ እነዚህ ነበሩ።

ጨዋታው ከደጋፊ ውጪ ስለመደረጉ…

አንዳንድ ነገሮች ወደተለመደው እንቅስቃሴ እንዲገቡ ቢፈቀድም በደጋፊዎች ላይ የተጣለው ዕገዳ ግን እንደፀና ነው። በሜዳችን እንደመጫወታችን የደጋፊዎች መኖር ያስፈልገን ነበር። ያኝ ሆኖ በቡድናችን ውስጥ የሥነ-ልቦና ባለሙያ ስላለ ከእሱ ጋር በመስራት ላይ እንገናኛለን ፤ ወደፊትም በዚህ መልኩ እንቀጥላለን። ከዚህ ቀደም ጨዋታዎች በባህር ዳር እና ሀዋሳ ስታድየሞች ሲደረጉ የደጋፊዎች መኖር ያለው ጠቀሜታ በግልፅ የታይ ነበር።

ቡድኑ በሜዳው ላይ ስለመጫወቱ…

ሰበታን እያሰለጠንኩ በነበረበት ወቅት ስታድየማችን እድሳት ላይ የነበረ በመሆኑ 17 ጨዋታዎችን ከሜዳችን ውጪ ለመጫወት ተገደን ነበር። በዚያ ወቅት ያገኘውትን ልምድ ለብሔራዊ ቡድኑ ጥቅም ላይ የማውለው ይሆናል። የዛምቢያ ብሔራዊ ቡድንን ደረጃ ስንመለከት እንዲሁም የእኛን የልምምድ ጊዜ እጥረት ከግምት ውስጥ ስናስገባ ተጫዋቾቻችንም ከውድድር ብዙ ስለራቁ ጉዳት ሊገጥመን የሚችልበትም ዕድል ነበር። ጨዋታውን የቀረብንበት መንገድ ካሰብነው በላይ ነበር። የተወሰኑ ተጫዋቾች ባሰብኩት መንገድ ላይጫወቱ ይችላሉ የሚል ስጋት የነበረብኝ ቢሆንም በጥቅሉ ግን መልካም እንቅስቃሴ አድርገናል።

ስለእሁዱ ጨዋታ…

የጨዋታው ዋና አላማ ተጨዋቾች ያሉበትን የአካል ብቃት ደረጃ ማወቁ ላይ ነው። ከ18 ባልበለጡ ቀጣዮቹ ቀናት ውስጥ የስብስባችንን ብዛት እንቀንሳለን። በእነዚህ ጊዜያትም ኒጀርን የሚገጥመው ሙሉ ቡድንም ብቁ እና ዝግጁ ይሆናል።

ስለቡድኑ ትኩረት..

ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው ፊሽካ ትኩረት በእጅጉ ያስፈልጋል። ሜዳ ላይ ነገሮች በቀላሉ ሊቀየሩ ይችላሉ። ግቦቹ የተቆጠሩብን ግን ከትኩረት ማጣት ነው ማለት አልችልም። ከዚያ ይልቅ በተጋጣሚያችን ተጫዋቾች የግል ብቃት የተቆጠሩ ናቸው። በትኩረት ጉዳይ ቡድኑን ለመውቀስ ጊዜው በጣም ገና ይመስለኛል። ለመሥራት በቂ ጊዜ ባልነበረን ጉዳይ ላይ ጥያቄ ላነሳም አልችልም። አሁን ላይ ትኩረታችን የአካል ብቃት ዝግጁነታችን ላይ ነው። ቀሪዎቹ ነገሮች አሁን ላይ የመጀመሪያ ጉዳዮቻችን አይደሉም።

ቡድኑ ላይ ስለታዩ ችግሮች…

በጨዋታ ዝግጁነታችን ላይ ብዙ መሥራት እንዳለብን ተመልክቻለው። በእርግጥ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ከተጨዋቾቹ ብዙ መጠበቅ ለጉዳትም ሊዳርጋቸው ይችላል። በጨዋታው 21 ተጫዋቾችን ተጠቅመናል፤ የሚያበረታታ ነገርም ተመልክተናል። አሁን በተመለከትነው ብቻ ተጫዋቾቹ ላይ መፍረድ ግን ከባድ ነው። የጨዋታው ዋነኛ ዓላማችን የነበረው ያለንበትን ደረጃ ማወቁ ላይ ነው። በወዳጅነት ጨዋታው ላይ የተመለከትናቸው ነገሮችም ይበልጥ እንድንጠነክር ያደርጉናል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!