የብሔራዊ ቡድኑ ስድስት ተጫዋቾች ጉዳይ…?

በሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ላይ ያልተሰለፉት ስድስት ተጫዋቾች ጉዳይ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል ?

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አሁጉራዊ ውድድሮች መቋረጥ በኃላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአዲስ አሰልጣኝ እየተመራ ለአርባ አንድ ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ከሳምንታት በፊት አያት በሚገኘው የካፍ ልኅቀት ማዕከል ሲዘጋጅ መቆየቱ ይታወቃል። የቡድኑን ወቅታዊ ሁኔታ ለመመልከት እንዲረዳ እና ክፍተቶቹን ከዋናው ከኒጀር ጨዋታ አስቀድሞ ለማወቅ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ለማድረግ ከዛምቢያ አቻው ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ሁለት ጨዋታ በማድረግ ሽንፈት አስተናግዷል።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ አስቀድሞ ዳዊት እስጢፋኖስ እና አሕመድ ረሺድን በጉዳት ከቡድኑ ማጣታቸው እንዳለ ሆኖ ሽመልስ በቀለ እና መስፍን ታፈሰ ከሀገር ውጭ በመሆናቸው ከቡድኑ ጋር መቀላቀል ሳይችሉ ሲቀሩ በሁለቱ የወዳጅነት ጨዋታ በቀጣይ ሊመርጡ የታሰቡትን የመጨረሻ 23 ተጫዋቾችን ለመለየት ካሏቸው 36 ተጫዋቾች መካከል ስድስት ተጫዋቾችን ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። እነርሱም ግብጠባቂዎቹ ምንተስኖት አሎ፣ ሰዒድ ሀብታሙ፣ ተከላካዩ ደስታ ደሙ፣ አማካዩ ፍፁም ዓለሙ እንዲሁም አጥቂዎቹ አቤል ያለው እና አቡበከር ናስር ናቸው። ከእነዚህ ተጫዋቾች መካከል ምንተስኖት አሎ፣ ሰዒድ ሀብታሙ እና ደስታ ደሙ በሙሉ ጤንነት ላይ ቢገኙም በሁለቱም ጨዋታ ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል። 

ቀሪዎቹ ሦስት ተጫዋቾች ማለትም አቤል ያለው፣ ፍፁም ዓለሙ እና አበቡበከር ናስር በሁለቱም ጨዋታ ያልተመለከትንበት ምክንያቱ ጉዳት እናቤተሰብ ጉዳይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። ፍፁም ዓለሙ የቤተሰብ ጉዳይ አጋጥሞት በአሁኑ ሰዓት ከቡድኑ ጋር የማይገኝ መሆኑን ስናረጋግጥ አቤል ያለውም በጉዳት ምክንያት ልምምድ ማቋረጡን ሰምተናል። አቡበከር ናስር በተመለከተ በግሉ ቀለል ያለ ልምምድ እየሰራ እንደሆነና ለኒጀሩ ጨዋታ የመድረስ ተስፋ እንዳለው ተገምቷል። 

ሌላው በመጀመርያው የዛምቢያ ጨዋታ ላይ መጫወት የቻለው ሚኪያስ መኮንን ባጋጠመው ጉዳት በትናንትናው ጨዋታ ያልተሰለፈ መሆኑ ሲታወቅ ምን አልባትም ጉዳቱ ትንሽ ከበድ ያለ በመሆኑ ለኒጀር ጨዋታ እንደማይደርስ ለማረጋገጥ ችለናል።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በቀጣይ ቀናት ኒጀር ከማቅናታቸው በፊት የመጨረሻዎቹን 23 ተጫዋቾች ያሳውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!