በሕይወት የሌሉ የእግርኳስ ሰዎችን በምናስታውስበት አምዳችን የቀድሞው እና በበርካቶች ዘንድ የምን ጊዜውም ታላቅ እግርኳስ ተጫዋች እንደሆኑ የሚነገርላቸው መንግሥቱ ወርቁን እያሰብን እንገኛለን። የዛሬ ትኩረታችን ደግሞ ኢትዮጵያ በብዙ ተጠብቃበት ሳታሳካው በቀረችው ስድስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ የነበረውን የመንግሥቱ ወርቁ ሚና ይሆናል።
ማስታወሻ ፡ በገነነ ሊብሮ በመፅሀፍ መልክ የተዘጋጀው ከመንግሥቱ ወርቁ ጋር የተደረገው ሰፊ ቃለ ምልልስ ዋነኛ ግብዓታችን መሆኑን እንገልፃለን።
1960 ላይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለሁለተኛ ጊዜ የማስተናገድ ዕድል ገጠማት። ስድስተኛው የአህጉሪቱ ውድድርም አዲስ አበባ እና አስመራ ላይ በሁለት ምድቦች ተከፍሎ እንዲካሄድ ሆነ። ታድያ በዚህ ወቅት የብሔራዊ ቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች መንግሥቱ ወርቁ በሚሰራበት የኢንሹራንስ ድርጅት በኩል እንግሊዝ ሀገር ለከፍተኛ ትምህርት የመሄድ ዕድልን አግኝቶ ነበር። እስከዚያ ወቅት ድረስ ለአራት የአፍሪካ ዋንጫዎች ሀገሩን ያገለገለው ታላቁ ስምንት ቁጥር ለወደፊት ህይወቱ እጅግ ጠቃሚ የሆነውን ይህን ትምህርት ለመማር ወደ እንግሊዝ ሊያመራ አሰበ። ነገር ግን ውድድሩ በሀገር ውስጥ መዘጋጀቱን እና በቂ ተተኪ ያልነበረ መሆኑን ሲያስብ ደግሞ ቡድኑን ከአህጉሪቷ ትልቅ ውድድር ዋዜማ ላይ ጥሎ መሄድ እንደሌለበት ከውሳኔ ላይ ይደርሳል።
በውድድሩ አዲስ አበባ ላይ በነበረው ምድብ አዘጋጇ ኢትዮጵያ ከኮትዲቯር ፣ አልጄሪያ እና ዩጋንዳ ጋር ስትደለደል ጋና ፣ ሴኔጋል ኮንጎ ኪንሻሳ እና ኮንጎ ብራዛቪል ደግሞ አስመራ ላይ ከተሙ። ከ1954ቱ ድል በኋላ በሀገሪቱ እግር ኳስ በተሻለ ሁኔታ የመታወቅ እና የመወደድ ዕድል አግኝቷል። የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾችም በሀገር ውስጥ ከባድ ፉክክር በነበረባቸው ውድድሮች እና በሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች በስለው የተገኙበት ወቅት ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ አስተናጋጅ ከመሆኗ አንፃርም ውድድሩን በድል እንደምታጠናቅቅ ከፍተኛ ግምት ተሰጣት። ይህ ግምት በእግር ኳስ አፍቃሪው እና በተጫዋቾቹም ዘንድ ተጋብቶ ከፍተኛ በራስ መተማመን ላይ ተደረሰ። ቡድኑ ውድድሩን በድል ካጠናቀቀ በአዲስ አበባ ተጨማሪ ስታዲየም ይገነባል መባሉ ደግሞ የሁሉም ሰው ጉጉት እንዲጨምር አደረገ።
በውድድሩ ጅማሮ የምድብ ጨዋታዎች ግምቱ ዕውነትነት እንደነበረው በግልፅ መታየት ጀመረ። ኢትዮጵያ ዩጋንዳን 2-1 ፣ ኮትዲቯርን 1-0 እንዲሁም አልጄሪያን 3-1 በመርታት ምድቡን የላብዙ ችግር በአንደኝነት አጠናቀቀች። በአስመራው ምድብ ጋናን ተከትላ ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ኮንጎ ብራዛቪልም ኢትዮጵያ ለዋንጫ ለማለፍ የምትገጥማት ሀገር ሆነች። ቀድሞ የነበረው ለብሔራዊ ቡድኑ የተሰጠው ከፍተኛ ግምት በምድብ ጨዋታዎቹ ከተመዘገቡት ውጤቶች ጋር ተዳምሮም አስተናጋጇ ሀገር ፈተና ሳይገጥማት ዋንጫውን እንደምታነሳ በፅኑ ታመነ። በተለይም የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች በራስ መተማመናቸው ከገድቡ እንዲያልፍ ምክንያት የሆነ አንድ ክስተት ተፈጠረ። ይህም ለቡድኑ ታላቅ ስህተት ሆነ።
የኮንጎ (የቀድሞዋ ዛየር) ብሔራዊ ቡድን የአስመራውን የምድብ ጨዋታዎች አጠናቆ ለግማሽ ፍፃሜው ወደ አዲስ አበባ መጣ። ከጨዋታው በፊትም ልምምዱን በያኔው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ስታዲየም ሲደርስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችም ልምምዳቸውን ሊያከናውኑ ስለነበር ሜዳውን ለሁለት ተካፍለው መስራት ጀመሩ። የተጋጣሚያቸውን ተጫዋቾች በተመለከቱበትም ወቅት ጨዋታውን በቀላሉ እንደሚያሸንፉ እርግጠኛ ሆኑ። ይህ ተጋጣሚን አቅልሎ የማየት ትልቅ ስህተት እንዲፈጠርባቸው ያደረገውን ምክንያት መንግሥቱ ወርቁ ሊብሮ ላይ እንዲህ አብራርቶት ነበር። “ልምምድ ልንሠራ እኩል ስቴዲየም ደረሰን፡፡ ግማሽ ግማሽ ሜዳ ተካፍለን መሥራት ጀመርን፡፡ ስናያቸው ኳስ ምንም አይችሉም። በእርግጥም አይችሉም ፤ ኮንትሮል ሲያደርጉ በቅልጥማቸው ነው። ኳስ ማቀበል እንኳን አይችሉም፡፡ እኛ ልምምዳችንን አቁመን እንስቃለን፡፡ እነኚህ ላይ ስድስት ነው የምናገባው ማለት ጀመርን፡፡ አልጄሪያን እና ኮንጎን ስታስተያይ አልጄሪያ በጣም ይበልጣቸዋል፡፡ አልጄሪያ ላይ እኛ በ15 ደቂቃ 3 ነው ያገባነው፡፡”
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዚህ ዓይነት የተጋነነ የማሸነፍ ሥነ-ልቦና የግማሽ ፍፃሜውን ጨዋታ ለማድረግ ወደ ሜዳ ገባ። ተጫዋቾቹ ጨዋታው እንደጀመረ አከታትለው ግቦችን ለማስቆጠር እና ጨዋታውን ዘና ብለው ለማጠናቀቅ ጓጉተዋል ፤ ይህን ማድረግ እንደማያቅታቸውም እርግጠኞች ነበሩ። በጨዋታው ላይ ግን የገጠማቸው ፈተና ከባድ ነበር። ጨዋታው ከመጀመሩ የኮንጎ ቡድን ጎል አስቆጠረ። ብዙም ሳይቆይ ሁለተኛ ግብ አከለ። በ16 ደቂቃ ውስጥ ኢትዮጵያዊያኑ 2-0 መመራት ጀመሩ። በዚህ ቅፅበት ብሔራዊ ቡድን ውስጥ በተሳሳተ ግምት ሰበብ የተፈጠረውን መረበሽ በመንግሥቱ ወርቁ አንደበት እንዲህ ተገልፆ ነበር። “ዕድላችን እየጠበበ መጣ የንቀት እንጂ የማሸነፍ ዝግጅት ይዘን ወደ ሜዳ ስላልገባን ለጊዜው ግራ ተጋባን፡፡ ከዚያ ለመምራት ሳይሆን እነርሱ ላይ ለመድረስ መሯሯጥ ጀመርን፡፡ ያ ሁሉ ጉልበትና ችሎታ አቻ ለመሆን መባከን ጀመረ። በዚያ ላይ የሸዋንግዛው በክንፍ ያለመኖር ቡድኑን ገድቶታል። ፍሰሐ ታሞ መርፌ ተወግቶ ስለገባ ያን ያህል ነው። ዋናውና የቡድኑ የመሀል ሜዳ ቁልፍ ተጫዋች የሆነው ተስፋዬ (ወዲ ቀጭን) ታሞ አልተሰለፈም። የእነዚህ ሁሉ ልጆች ያለመኖር ሜዳ ውስጥ ያለውን ኃላፊነት ከባድ አደረገው።”
ጨዋታው ወደ ዕረፍት ከማምራቱ ቀደም ብሎ መንግሥቱ ወርቁ ለሉቻኖ ቫሳሎ ያደረሰውን ኳስ ሎቻኖ አስቆጥሮ ልዩነቱን ማጥበብ ቻለ። በሁለተኛው አጋማሽ ስህተታቸውን አርመው ሌላ ግብ በማስቆጠር ጨዋታውን ወደ ተጨማሪ 30 ደቂቃዎች ለመውሰድ የይድነቃቸው ተሰማ ልጆች መታገላቸውን ቀጠሉ። በዚህ ወሳኝ ሰዓት ታድያ ብሔራዊ ቡድኑን አቻ ለማድረግ የምታስችል ግን ደግሞ ከባድ መስዕዋትነት የምትጠይቅ ኳስ ወደ መንግሥቱ ወርቁ መጣች። “አንድ ኳስ በአየር ላይ መጣች እኔ በኃይል ዘልዬ ተነሳሁ በረኛው ደግሞ ፓንች ለማድረግ ተንደርድሮ መጣ። ኳሷ ጋር እኩል መጣን ፤ ዞሬ ወደ ጎሉ በቴስታ ስለምመታ በረኛው እጁን በኃይል ሠንዝሮ መጣ። ራሴን ከዱላ ለማስመለጥ ከፈለኩ ኳሱን መንካት የለብኝም። ኳሱን በቴስታ ከመታሁ ግን በቡጢ እንደሚመታኝ አውቃለሁ። አንድ ዓይኔን ሸጬ ገባሁ። ጭንቅላቱን ሙሉ ለሙሉ አስገባሁና ኳሱን ስመታ ጎል ገባ በረኛው ግን አይኔን በኃይል በቡጢ ብሎ ጣለኝ፡፡ ወድቄ ሰማይ ምድሩ ሁሉ ዞረብኝ። ደስታ ስለነበር ተነሳሁ ፣ 2 ለ 2 ሆነን ወደ ጭማሪ ሰዓት ገባን።” ሲል ታላቁ የእግር ኳስ ሰው ስለወሳኟ ግብ አስታውሶ ነበር።
አሸናፊውን ለመለየት የተሰጡት ተጨማሪ ሠላሳ ደቂቃዎች ለመንግሥቱ ወርቁ እጅግ ከባድ ነበሩ። ዓይኑ እጅግ በማበጡ ኳሷንም ሆነ ተጋጣሚዎቹን መለየት የማይችልበት ሁኔታ ተፈጠረ። የቡድኑ ሐኪምም የዓይኑን ሁኔታ በማየት ከሜዳ መውጣት እንዳለበት ሀሳብ ሰጠ። ነገር ግን ቡድኑ ቅያሪ ጨርሶ ስለነበር መንግሥቱ ቀሪዎቹን ደቂቃዎች እንደምንም ጨርሶ ጨዋታውን ለማሸነፍ ውሳኔ ላይ ደረሰ። ከግብ ጠባቂው ጌታቸው በስተቀር ቀሪዎቹ ተጫዋቾች በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ ሆነው ግብ ፍለጋ ቢማስኑም ያገኟቸውን ዕድሎች መጨረስ ባለመቻላቸው ሦስተኛውን ግብ ማግኘት ሳይችሉ ቀሩ። ይልቁኑም ብራዛቪሎች በመልሶ ማጥቃት ያገኟትን አንድ ኳስ አስቆጥረው በማሸነፍ ለፍፃሜው አለፉ። የዚህ ጨዋታ ታሪካዊ ሽንፈት በታላቁ የእግርኳስ ሰው ህይወት ውስጥ ትልቅ ጠባሳን ትቶ አልፏል። ከጨዋታው በኋላ ስለተፈጠሩ ነገሮች ሳምንት እንመለሳለን። ለዛሬ ግን ይህን ለዛሬውም የእግርኳስ ባለሙያዎች ወሳኝ የሆነውን የመንግሥቱ ወርቁን ምክር አክለን እናብቃ።
“እግርኳስ ጨዋታ እንዳሰብከው የሚሆን አይደለም፡፡ ይሄንንም የኮንጐ ቀን አየሁት ‘እግር ኳስ እርግጠኛ ሆነህ የማትገባበት ስፖርት ነው’። ይሄንንም አሰልጣኝ ሆኜ ብዙ ጊዜ ለተጫዋቾች አስተምሬአለሁ፡፡ ተጋጣሚ 6 ሆኖ እንኳን ቢገባ ዝቅተኛ ግምት አይኑርህ።”
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!