ይህን ያውቁ ኖሯል? (፮) | የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ…

ዕለተ ሐሙስ ወደ እናንተ በምናደርሰው ይህን ያውቁ ኖሯል? አምዳችን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የተመለከቱ ዕውነታዎችን ለአምስት ተከታታይ ሳምንታት ስናቀርብ ቆይተናል። ዛሬም ብሔራዊ ቡድኑን የተመለከቱ ነጥቦችን አጠናክረን በተከታይ ክፍል ይዘን ቀርበናል።

(1) – ኢትዮጵያ በተሳተፈችባቸው 22 የማጣርያ ውድድሮች በአጠቃላይ 107 ጨዋታ ያደረገች አከናውናለች። የጨዋታ ብዛቱም ፎርፌ እና የተሰረዙትን ውጤቶችን ያካተተ ነው።

– ኢትዮጵያ ካከናወነቻቸው 107 ጨዋታዎች መካከል የተሰረዙት አምስት ሲሆኑ ለ2010 ውድድር አራት ጨዋታ ከሞሮኮ፣ ሩዋንዳ እና ሞሪታንያ (2 ጨዋታ) ያደረገቻቸው ጨዋታዎች በፊፋ በመታገዷ ምክንያት ውጤታቸው ተሰርዟል። ቀሪው አንድ ጨዋታ ደግሞ በ2019 ማጣርያ ሴራሊዮንን 1-0 ያሸነፈችበት ጨዋታ ሴራሊዮን በፊፋ በመታገዷ ምክትያት ተሰርዟል።

– ከ107 ጨዋታዎች መካከል ስድስት ጨዋታዎች የፎርፌ ውጤቶች ናቸው። ከነዚህ መካከል አንዱ ብቻ ጨዋታው ተደርጎ (ከኬንያ) በተጫዋች ተገቢነት ለኢትዮጵያ ፎርፌ ሲሰጥ በቀሪዎቹ አሞስት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ለጨዋታ ባለመቅረቧ ፎርፌ ተሰጥቶባታል። እነዚህም በ1988 ማጣርያ ከታንዛኒያ ጋር የመልስ ጨዋታ ባለመገኘት እንዲሁም በ1992 የምድብ ማጣርያ ሁለት ጨዋታዎች ካከናወነች በኋላ ከውድድሩ በመውጣት ቀሪዎቹን አራት ጨዋታዎች ያልቀረበችባቸው ናቸው።

(2) – ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ 107 ጨዋታዎች 34 አሸንፋ (3 የተሰረዘ እና 1 ፎርፌ ጨምሮ)፣ 18 አቻ ተለያይታ 55 ተሸንፋለች። (2 የተሰረዘ እና 5 ፎርፌ ጨምሮ)።

በተጠቀሱት ጨዋታዎች 109 ጎሎችን ስታስቆጥር (9 የተሰረዘ እና 2 የፎርፌ ጎሎች ጨምሮ) 181 ጎሎች ተቆጥረውባታል። (6 የተሰረዘ እና 10 የፎርፌ ጎሎች ጨምሮ)

(3) – ካደረገቻቸው 107 ጨዋታዎች መካከል 54 በሜዳዋ (3 የተሰረዘ እና 2 ፎርፌ ጨምሮ) ስታከናውን በዚህም:-

27 ጨዋታ (2 የተሰረዘ ጨምሮ) አሸንፋለች
14 ጨዋታ (1 የተሰረዘ እና 2 ፎርፌ) ተሸንፋለች
13 አቻ ተለያይታለች

(4) – በአንፃሩ ከሜዳዋ ውጪ 53 ጨዋታዎች (1 የተሰረዘ እና 4 ፎርፌ ጨምሮ) ስታከናውን በዚህም:-

– 9 ጨዋታ (1 ፎርፌ ጨምሮ) አሸንፋለች
– 39 ጨዋታ (2 የተሰረዘ እና 3 ፎርፌ) ተሸንፋለች
– 5 አቻ ተለያይታለች

(5) – ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታዋን ያደረገችው በአምስተኛው የቱኒዚያ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ሲሆን የካቲት 7 ቀን 1957 ናይሮቢ ላይ በተከናወነ ጨዋታ የፎርፌ አሸናፊ ሆናለች። ጨዋታው በኬንያ 3-2 አሸናፊነት ቢጠናቀቅም ኬንያዎች ያልተገቡ ሁለት ተጫዋቾች በማሰለፋቸው ለኢትዮጵያ የፎርፌ ውጤት ሊሰጥ ችሏል።

(6) – የኢትዮጵያን የመጀመርያ የማጣርያ ጎል ያስቆጠረው ከላይ በተጠቀሰው ጨዋታ ፍስሀ ወልደአማኑኤል ቢሆንም ውጤቱ ተሰርዞ ኢትዮጵያ የፎርፌ አሸናፊ በመሆኗ የመጀመርያው የማጣርያ ጎል አስቆጣሪ ጌታቸው ወልዴ ነው። የቀድሞ የድሬዳዋ ኮተን ተጫዋች ካምፓላ ላይ ኢትዮጵያ ዩጋንዳን 2-1 ስታሸንፍ የመጀመርያውን ጎል አስቆጥሯል።

(7) – በአንፃሩ የመጨረሻ የማጣርያ ጨዋታዋን ያደረገችው ለካሜሩኑ የ2021 ውድድር ሲሆን ባህር ዳር ላይ አይቮሪኮስትን 2-1 አሸንፋለች። ሽመልስ በቀለም የመጨረሻው ጎል አስቆጣሪ ነው።

(8) – የመጀመርያው ሐት-ትሪክ የሰራ ተጫዋች እርማ አስመሮም ነው። በዋናው አፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ ጎል ካስቆጠሩ 12 የኢትዮጵያ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ግርማ ለ1970 የሱዳን አፍኪካ ዋንጫ ማጣርያ ኢትዮጵያ ታንዛኒያን 7-0 ስታሸንፍ (በማጣርያ ታሪኳ ከፍተኛ ውጤት) ሦስት ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።

(9) – ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ በሜዳዋ ያደረገችው የማጣርያ ጨዋታ የካቲት 24 ቀን 1957 ሲሆን ቀ/ኃ/ሥ ስታዲየም ላይ በተደረገ ጨዋታ ዩጋንዳን 2-0 አሸንፋለች። ከሜዳዋ ውጪ ያደረገችው ደግሞ ኬንያን በፎርፌ ያሸነፈችበት ነው (ከላይ ተጠቅሷል።)

(10) – የመጀመርያ የማጣርያ ሽንፈቱን ያስተናገደው በሱዳን ሲሆን መጋቢት 1957 ካርቱም ላይ 2-1 ተሸንፏል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!