የዳኞች ገፅ | የተረጋጋው ሰው ኢንስትራክተር ኤፍሬም መንግሥቱ

በዳኝነት ዘመኑ ሙያውን አክብሮ ለዓመታት ትልልቅ ጨዋታዎችን በመምራት አገልግሏል። በአሁኑ ወቅትም የጨዋታ ታዛቢ ከመሆኑ ባሻገር የአካል ብቃት ኢንስትራክተርም በመሆን እየሰራ የሚገኘው ኤፍሬም መንግሥቱ የዛሬው የዳኞች ገፅ ዕንግዳችን ነው። 

ወደ ዳኝነቱ ከመግባቱ አስቀድሞ እግርኳስን ይጫወት ነበር። ተጫውቶም ብቻ አላበቃም ወደ አሰልጣኝነቱም በመግባት በተወሰነ መልኩ አገልግሏል። እግርኳሱን ይጫወት እንጂ የሁልጊዜ ፍላጎቱ ዳኛ የመሆን ነበር እና ከመምሪያ የጀመረው የዳኝነት ህይወቱ እስከ ኢንተርናሽናል ዳኝነት በመድረስ በሀገር ውስጥ ትልቅ ግምት የሚሰጣቸውን ጨዋታዎችን በብቃት ዳኝቷል። አስር ዓመት በቆየው የኢንተርናሽናል የዳኝነት አገልግሎቱ ወደ ተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በመሄድ በርከት ያሉ የሀገራት እና የክለቦች ውድድሮች ላይ በረዳት ዳኝነት አገልግሏል። ዳኝነት ካቆመ በኃላ የጨዋታ ታዛቢ (ኮሚሽነር) በመሆን ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸውን ጨዋታዎችን እስካሁን ድረስ እየመራ ሲሆን በተጨማሪም በካፍ የአካል ብቃት ኢንስትራክተር በመሆን የዳኞችን የአካል ብቃት ደረጃ በመፈተን ሀገሩን እያገለገለ ይገኛል። እጅግ የተረጋጋ መልካም ሰው እንደሆነ እና ሙያውን አክባሪ መሆኑን የሙያ ባልደረቦቹ የሚመሰክሩለት የቀድሞው ኢንተርናሽናል ዳኛ የአሁኑ ኢንስትራክተር ኤፍሬም መንግሥቱ የዳኝነት አጀማመሩን ፣ ጉዞውን እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንዲህ አቅርበነዋል።

ትውልድ እና ዕድገትህ የት ነው?

የተወለድኩት በባሌ ክፍለ ሀገር ነው። እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርቴንም እዛው ነው ያገባደድኩት። ከዚያም በኮተቤ የመምህራን ኮሌጅ በጤና እና ሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት በመምህርነት ተመርቄያለሁ። ከዚያም ወደ ሸዋ ክፍለ ሀገር በመጓዝ በተማርኩበት የትምህርት ዘርፍ ሥሰራ ቆይቻለሁ። በኋላም በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በማገልገል ቀጥያለሁ። በአሁኑ ሰዓትም ኑሮዬን በቢሾፍቱ ከተማ አድርጌያለሁ።

ወደ ዳኝነቱ እንዴት ልትገባ ቻልክ ? መነሻህ ምን ነበር ?

በፊት እግርኳስ ተጫዋች ነበርኩ። በተወሰነ ደረጃም በተጫዋችነት ዘልቄያለሁ። በአንድ አጋጣሚ አሁን በምኖርበት ደብረዘይት የዳኝነት ኮርስ እንደሚሰጥ ሰማሁ። ከዛም ወዲያው 1980 ላይ በሦስት ከተሞች የተሰጠውን ኮርስ በመውሰድ ወደ ሙያው ገባሁ። እንዳልኩት ተጫዋች ስለነበርኩ እና በደብረዘይት ብዙም ዕድል ስላልነበር ከስፖርቱ ሳልርቅ ወደ ዳኝነት የመግባት ፍላጎቱ ስለነበረኝ ገባሁ።

እግርኳስ ተጫዋች እንደነበርክ እየነገርከኝ ነው። እስከ ምን ደረጃ ተጫውተሀል ?

ያን ጊዜ ብዙም ክለቦች አልነበሩም። ነገር ግን በዞን እና በክፍለ ሀገር ደረጃ ተጫውቻለሁ። በመጀመርያ ይፋት እና ጥሚጋ ለሚባል ቡድን ሰሜን ሸዋ ላይ ተጫውቻለሁ። ከዛም ለአምቦ ተጫውቻለሁ። በሁለቱ ቡድኖች ተጫዋች ብቻ ሳልሆን አሠልጣኝም ነበርኩ። በተጨማሪም ለሸዋ ክፍለ ሀገር ምርጥም ተመረጬ ተጫውቻለሁ።

የዳኝነት ኮርስ የወሰድክበትን ሂደት በየደረጃው አጫውተኝ እስኪ ?

የመጀመሪያ የዳኝነት ትምህርት የሰጡኝ ጋሽ አበራ እሸቴ ናቸው። እንዳልኩት 1980 ላይ መምሪያ ሁለተኛ ደረጃን ወሰድኩ። ከዚያም አምስት ዓመት ቆይቼ 1985 ላይ መምሪያ አንደኛ ደረጃን ወሰድኩ። በድጋሚ አምስት ዓመት ከቆየሁ በኋላ በኢንስትራክተር ሽፈራው እሸቱ አማካኝነት የፌዴራል ኮርስ ወሰድን። በሁለቱም የመምሪያ ደረጃም ሆነ በፌዴራል ደረጃ በዋና እና በረዳት ዳኝነት እሰራ ነበር። ነገር ግን በጣም ጥሩ የነበርኩት ረዳትነት ላይ ነበር። 1990 ላይ የፌዴራል ዳኝ ሆኜ ሦስት ዓመታትን ካገለገልኩ በኋላ ደግሞ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሆንኩ።

ብዙዎች የፌዴራል ዳኛ ሆነው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታን የሚመሩበትን ቀን ይናፍቃሉ። አንተስ መቼ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ የመራኸው ?

አዎ አስታውሳለሁ። የፌዴራል ዳኛ ሆኜ በረዳትነት ከፍቃዱ ግርማ ፣ ፍቃዱ ጥላሁን እና ሠለሞን ገብረስላሴ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታን የመራሁት የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የመብራት ኃይል ግጥሚያን ነበር።

የፌዴራል ዳኛ ከሆንክ በኋላ ወደ ኢንተርናሽናልነት ለመሸጋገር ሦስት ዓመት ብቻ ነው የፈጀብህ ፤ እንዴት ኢንተርናሽናል ዳኛ ሆንክ ?

በወቅቱ የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ፀሃዬ ነበር። እሱም በክልሎች የሚገኙ ዳኞች መሳተፍ አለባቸው ብሎ ነባሮቹን እና አዲሶቹን አወዳደረን። በውድድሩም የነበረ የአካል እና የጨዋታ መምራት ብቃት እንዲሁም የተለያዩ ፈተናዎችን ወሰድን። መስፈርቶቹንም አልፌ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሆንኩ።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ሆነህ ስንት ዓመት ሰራህ ? የመጀመሪያህንስ ጨዋታ ታስታውሳለህ ?

በአጠቃላይ ለአስር ተከታታይ ዓመታት ነው ግልጋሎት የሰጠሁት። የመጀመሪያ ጨዋታዬንም ከሀገር ወጥቼ ያጫወትኩት ኬኒያ ላይ ነው። በጊዜውም እኔ ፣ ፍቃዱ እና ጥላሁን ሆነን ነበር ኬኒያ ሄደን ጨዋታውን የመራነው።

ዳኝነት መቼ ነው ያቆምከው ?

2003 አካባቢ ደብረዘይት ጉልበቴ ላይ ትንሽ አደጋ አጋጥሞኝ ነበር። በወቅቱም የአካል ብቃት ፈተና በዓመት አንድ ጊዜ ነበር የሚሰጠው። ፈተናውንም በገጠመኝ አደጋ ምክንያት አቆምኩት። ከዚያ ወደ ታች ወርጄ መስራት ስላልፈለኩ ዳኝነቱን አቁሜ ወደ ኮሚሽነርነት ገባሁ። ደግም ለሌሎች ዕድሉን መልቀቅ ስለነበረብኝ ነው ዳኝነቱን ያቆምኩት። በነገራችን ላይ እኔ ከማቆሜ ከአንድ ዓመት በፊት ፌዴሬሽኑ የኢንስትራክተሮች ኮርስ አዘጋጅቶ ነበር። ያንንም ኮርስ ወስጄ ጁኒየር ኢንስትራክተር ሆኜ ነበር። ዳኝነቱን ካቆምኩም በኋላ በኮሚሽነርነት መስራቴን ቀጠልኩ።

በዳኝነት ዘመንህ የፈተነህ እና የማትረሳውን ጨዋታ አለ ?

በዳኝነት ውስጥ እያለሁ የተለያዩ ቦታዎች ሄጄ ጨዋታዎችን መርቼያለሁ። ለአስር ዓመታት በኢንተርናሽናል ዳኛነትም ሳገለግል ግብፅን ጨምሮ በርካት ሀገራት ሄጃለሁ። ግን ያን ያህል የከበደኝ ጨዋታ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ አላጋጠመኝም።

ሀገር ውስጥም ሆነ ውጪ ብዙ ጨዋታዎችን መርተካል። እስቲ በዚህ ቆይታህ የገጠመህን አስቂኝ ገጠመኝ ንገረኝ ?

የሚያስቅ ሳይሆን አሁን አዕሮዬ ላይ የመጣውን ገጠመኝ ላካፍልህ። በፊት አርባምንጭ ጨርቃጨርቅ የሚባል ቡድን ነበር። እና እዚያ ሄደን ጨዋታ ለማድረግ እኔ እና የጨዋታው ሌሎች ዳኞች አውቶብስ ተራ ተቀጣጠርን። እኔ እና የጨዋታው ኮሚሽነር በጠዋት ተገናኝተን አሁን ስሙን የማልገልፅልህን አንደኛውን ዳኛ መጠበቅ ጀመርን። ብንጠብቀው፣ ብንጠብቀው ዳኛው ቶሎ ሊመጣ አልቻለም። በጣም አርፍዶም ቢሆን ግን መጣ። ለካ እሱ መርካቶ አካባቢ ነበር ያደረው። ማታ ወደ ማደሪያው ሲገባ የተከታተሉት ሌቦች ጠዋት ጠብቀው ዘረፋ ፈፅመውበት ነበር። የጠፋ ገንዘብ አገኘን እንካፈል ብለውት ካዋከቡት እና የእርሱን ገንዘብ ከኪሱ ከወሰዱ በኋላ የታሰረ ሌላ ገንዘብ ሰጥተወት ነበር እኛ ጋር የደረሰው። እኛ ጋርም ሲመጣ የተፈጠረውን ነገር ካስረዳን በኋላ የተወሰነ ብር እንደሰጡት ይነግረናል። ስንት ብር ነው ብለን ስናየው ከላይ እና ከታች አንድ ብር አለው ውስጡ ግን መጫወቻ ካርታ ነበር የነበረው። እኛም የትራንስፖርቱን ሸፍነን ወደ ጨዋታው ቦታ አመራን። ሌላው ገጠመኝ ኮንጎ ሀገር ጨዋታ ለመምራት ስንሄድ የተፈጠረው ነው። እዚህ ጨዋታ አጫውተን እንደጨረስን ከሰዓታት በኋላ ወደ ኮንጎ አመራን። የዛ የምንመራው ጨዋታ ከአንድ ቀን በኋላ እንደሆነ ነበር የደረሰን መረጃ። ኮንጎ ደርሰን ወደ ሆቴል ስንሄድ በርካታ ደጋፊዎች እየጨፈሩ ወደ ስታዲየም ይሄዱ ነበር። እኛም አላወቅንም ሌላ ጨዋታ አለ ማለት ነው እያለን ሆቴል ደረስን። ልክ ሆቴል ስንደርስ ለማረፍ ስንል ጥቂት ደቂቃዎች የቀሩት ጨዋታ እኛ የምንመራው እንደሆነ ተነገረን። ደግሞ የቲፒ ማዜምቤ ጨዋታ ነበር። ምንም ማድረግ አንችልም ሳንዘጋጅ ወዲያው ወደ ስታዲየም ሄደን። ሆኖም በጥሩ ብቃት ጨዋታውን መርተን ወጣን።

በዳኝነት ዘመንህ ያገኘሀቸው የኮከብነት ሽልማቶ አሉ ?

በዳኝነት ውስጥ እያለሁ ያገኘሁት የኮከብነት ሽልማት የለም። ስጀምርም በእኛ ጊዜ ምስጉን ዳኞች ሽልማት አይሰጣቸውም ነበር። ከሚሌኒየሙ በኋላ ነው በደንብ የተለመደው። ግን እኔ በአካል ብቃት የፊፋ ኮርስ ሲሰጥ ወስጄ ነበር። በዛ ኮርስ ላይም አንደኛ ወጥቼ በጊዜው ውድ የነበረውን ኦክስፎርድ ፊሽካ በካፍ ኢንስትራክተሮች ተሸልሜያለሁ።

የካፍ የአካል ብቃት ኢንስትራክተር ነህ ፤ እስከ አሁንም እያገለገልክ ትገኛለህ። እስቲ ስለዚህ ጉዳይ የተወሰነ ነገር በለን ?

2010 ላይ በታንዛኒያ የተሰጠውን የካፍ ኢንስትራክተርነት ኮርስ ወስጄ ነው እዚህ ደረጃ የደረስኩት። እርግጥ ከዛም በፊት በተለያዩ የሥራ ዘርፎች እሰራ ነበር። ለምሳሌ 2009 ላይ የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ ውስጥ ነበርኩ። 2011 ላይም የአንደኛ ሊግ ኮሚቴ ውስጥ ነበርኩ። አሁንም በተለያዩ ኃላፊነቶች እየሰራሁ እገኛለሁ።

አንተ ዳኝነት ከጀመርክበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ያለውን የኢትዮጵያ የእግርኳስ ዳኝነት እንዴት ትገልፀዋለህ ?

እኛ በነበርንበት ጊዜ ብዙ ዳኞች አልነበሩም። ጥቂቶች ብቻ ነበርን በሙያው ውስጥ የምንገኘው። ውድድሮችም እንደ አሁኑ ብዙ ስላልነበሩ ዳኞችም ጥቂት ነበርን። ይህ ቢሆንም ግን ከብሔራዊ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ ከፍተኛ ፉክክር ነበር። በጊዜውም በፕሪምየር ሊግ የሚያጫውቱት እነኃይለመላክ ተሰማ ፣ ፍቃዱ ግርማን የመሳሰሉ ትላልቅ ዳኞች ነበሩ። እነሱ ጋር ለመድረስ ከፍተኛ ትግል ይጠይቅ ነበር። በዚያ ላይ ደግሞ ገንዘቡም አነስተኛ ነበር። በዳኝነት ሙያ ብቻ መኖር ይከብድ ነበር። ሌላ ስራ ከጎን ያስፈልጋል። አሁን በርካታ ዳኞች በሀገራችን አሉ። ውድድሮችም እንደ ድሮ ትንሽ አይደለሙ። የሚከፈለውም ገንዘብ ከድሮ ጋር ጭራሽ አይገናኝም። በአጠቃላይ ግን የአሁኖቹ ዳኞች ብዙ ነገር ተመቻችቶላቸዋል። በሰሩ ቁጥር የማደጋቸው ዕድል በጣም ሰፊ ነው። እኔም ሳገኛቸው እነግራቸዋለሁ።

ረጅም ዓመት በዳኝነቱ ቆይተሀል። እና ዳኛ መሆን ለሚፈልጉ ሰዎች ምን መልዕክት ታስተላልፋለህ ?

በመጀመሪያ ዳኛ ለመሆን የውስጥ ፍላጎት ያስፈልጋል። ሰዎችን አይቶ ብቻ ወደ ሙያው መግባት ፍፁም አያስፈልግም። ስለዚህ ዋናው ፍላጎት ነው። ሌላው ወደ ሙያው ከተገባ በኋላ ራስን ማዘጋጀት እና ማብቃትን እጅግ ይሻል። በአካልም ሆነ በአዕምሮ እንዲሁም ህጉን በመረዳት ትልቅ ዝግጁነት ያስፈልጋል። በተለይ ደግሞ ሴቶችን በጣም ነው የምናበረታታው። ምክንያቱም እነሱ ከሰሩ የተሻለ ደረጃ የሚደርሱበት ዕድል የሰፋ ስለሆነ። በአጠቃላይ ግን እንደነሊዲያ እና በዓምላክ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረስን እያሰቡ ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል። ስለዚህ የራስንም ሆነ የሀገርን ስም ለማስጠራት በጨዋነት ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል።

ሊጉ በኮቪድ-19 ምክንያት ከተቋረጠ በኋላ ስፖርተኞች እና ዳኞች ከሜዳ ርቀዋል። በዚህም የአካል ብቃት ጥያቄ በስፖርተኞች ላይ እንደ ስጋት ሲነሳ ነበር። ይህ ስጋት በዳኞች ላይም ይሰራል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ውድድሮች ታህሳስ ላይ ከመጀመራቸው በፊት ምን ዓይነት ሥራዎችን ለመስራት አስባችኋል?

ትክክለኛ ሃሳብ ነው። በኮቪድ ምክንያት ሁሉም ሰው በየቤቱ ነው ያለው። ውድድሮች እንደተቋረጡም በቴሌግራም ግሩፕ ለዳኞቻችን ልምምዶችን እንዲሰሩ መልዕክት ስናስተላልፍ ነበር። ምን ምን መስራት እንደሚገባቸውም በኢንስትራክተር ኃይለመልዓክ በኩል ስናሳውቃቸው ነበር። ሰሞኑንም ውድድሮች እንደሚጀምሩ እና ራሳቸውን አዘጋጅተው እንዲቀርቡ አሳስበናል። በእርግጥ እንደበፊቱ ወጥተው ስለማይሰሩ ክብደታቸው ሊጨምር ይችላል። ግን ውድድሮች ከፊታችን ስላሉ አካላዊ አቋማቸውን እንዲያስተካክሉ እና እንዲዘጋጁ አሳስበናል። እኛም በቶሎ እንዲዘጋጁ አንዳንድ ነገሮችን ለማመቻቸት እየተነጋገርን ነው የምንገኘው።

የቤተሰብ ህይወትህ ምን ይመስላል ?

ባለትዳር እና የሦስት ወንድ አንዲሁም የአንድ ሴት ልጅ አባት ነኝ። በአጋጣሚ ደግሞ መቅደላዊት ኤፍሬም የምትባለው ሴቷ ልጄ የእግርኳስ ዳኛ ነበረች። እስከ ፌዴራል ዳኛ ድረስ ደርሳ ውድድሮችን መርታ ነበር። ግን ከሁለት ዓመት በፊተ ይህንን ዳኝነት አቁመዋለች። ወደፊት ግን በኮሚሽነርነት ለመቀጠል ፍላጎቱ አላት። ሌሎቹ ወንድ ልጆቼም ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሰዋል።

በመጨረሻ…

በኮቪድ ምክንያት ውድድሮች ቆመዋል። ፈጣሪም ይህንን በሽታ አቅልሎልን ወደ ቀደመ ሥራችን እና እንቅስቃሴያችን በቶሎ እንድንመለስ ምኞቴን አስተላልፋለሁ። በተጨማሪም ውድድሮች የሚጀምሩበት ቀን ስለታወቀ ዳኞች እና ኮሚሽነሮች ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ምክሬን አቀርባለሁ።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!