አስራ አራት ዓመታትን በአንድ ክለብ ብቻ የተጫወተው የሰማንያዎቹ ኮከብ ሳምሶን አየለ የእግር ኳስ ህይወት።
ትውልድ እና ዕድገቱ በመዲናችን አዲስ አባበ በተለምዶው የድሮ ቄራ በሚባለው ሰፈር ነው። የእግርኳስ ህይወቱን በተወለደበት ሰፈር ጀምሮ ገና የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቱን ሳያገባድድ በትልቅ ደረጃ መጫወት ጀምሯል። በወቅቱ ከዕድሜው ጋር የማይመጣጠን ብስለት እንደነበረውም ይነገርለታል። ገና በለጋነት ዕድሜው በአምበልነት የመራቸው ጨዋታዎች እና ከአንጋፋቹ እኩል በድፍረት በብቃት የተወጣቸው ጨዋታዎችም ለዚህ ምስክር ናቸው። እንደ አብዛኞቹ የሰማንያዎቹ ተጫዋቾች ለአስራሥስት ዓመታት በእርሻ ሠብል የእግርኳስ ህይወቱን ያሳለፈው ሁለገቡ ሳምሶን አየለ በሁለቱም እግሮቹ በበርካታ ቦታዎች ተጫውቶ አሳልፏል። በክለብ ደረጃ አንድ ዓመት በሜታ ቢራ ከተጫወተበት ጊዜ ውጪ ጫማውን እስከሰቀለበት ጊዜ ድረስ በእርሻ ሰብል መለያ አሳልፏል። በክለቡ ቆይታው ከግብ ጠባቂ እና አጥቂ ቦታዎች ውጪ በሁሉም ቦታዎች ላይ ተጫውቷል ፤ ሆኖም የመስመር ተከላካይነት በይበልጥ የሚታወቅበት ቦታው ነው።
በ1977 ትምህርቱን እየተማረ ጎን ለጎን ደግሞ በእርሻ ሠብል የተጫወተበትን አጋጣሚ እና ወደ ክለቡ የገባበትን ሁኔታ እንደሚከተለው ያስታውሰዋል። ” ወቅቱ በርካታ አቅም ያላቸው ተጫዋቾች የነበሩበት ወቅት ነው። በዚያ ምክንያት ወደ ክለብ እግርኳስ ለመግባት አዳጋች ነበር። እኔ ደግሞ ተማሪ ነበርኩ። ትምህርቱን እና እግርኳሱን አንድ ላይ ማስኬድ ደግሞ ትንሽ ፈተና ነበረው። ልምምድ ሰርተህ ወደ ክፍል መሄድ ከዚያ በኃላም ማጥናት ስለነበረው ከባድ ነበር። ሆኖም ክለቡ ሁለቱንም አብሬ ማስኬድ እንዳለብኝ በጥብቅ ስለሚፈልግ ቀላል አድርጎልኛል። በዚያን ወቅት ትምህርት ቤት ላይ ራሱ ትልቅ አክብሮት ነበረኝ። ምክንያቱ በዚያ ዕድሜ በከፍተኛ ሊግ መጫወት በጣም ትልቅ ነገር ነበር፤ ቅድም እንደነገርኩህ በርካታ ዓቅም ያላቸው ተጫዋቾች የነበሩበት ጊዜ ስለነበር ወደ ክለብ እግርኳስ መግባት ከባድ ነበር። አቶ ቃኘው እና አቶ ጌታቸው የሚባሉ የእርሻ ሠብል ከፍተኛ አመራሮች ትምህርቴን ይከታተሉኝ ነበር። እንደውም አንዳንዴ የልምምድ እና የትምህርት ጊዜ ሲጋጭብኝ ከክለብ ደብዳቤ አፅፌ ሺፍት አስቀይር ነበር። የዛኔ በሦስት ሺፍት ነበር የምንማረው።” ይላል።
ገና በወጣትነት ጊዜው ደፋር እና መሪ እንደነበር ወደ ክለቡ ከተቀላቀለ በኃላም ቋሚ ተሰላፊ ለመሆን ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም። እንደ ሳምሶን ገለፃም በዚያን ወቅት ጥቂት በማይባሉ አጋጣሚዎች ቡድኑን በአምበልነት የመምራት ዕድል ይገጥመው እንደነበርም ይገልፃል። ” ወጣት እያለሁ የብሔራዊ ቡድን ትላልቅ ተጫዋቾች ቡድኑ ውስጥ እያሉም አምበል ሆኖ የመምራት ዕድል ያጋጥመኝ ነበር። እንደውም የዛኔ ያዳበርኩት ነገር ለአሁኑ የአሰልጣኝነት ጊዜዬ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ነው የሚሰማኝ። ” ይላል በአምበልነት ስለመራቸው ጨዋታዎች ሲያስታውስ።
በአሰልጣኝ ገዛኸኝ ማንያዘዋል ያላሰለሰ ጥረት ወደ ክለቡ ገብቶ ውጤታማ የሆነው ሳምሶን አሰልጣኙ ጥረት ባያደርጉ በእግርኳሱ መቆየት ከባድ እንደነበር ሁኔታውን እያስታወሰ እንዲህ ይላል። ” በተክለሰውነታችን ምክንያት ብዙዎች ጥርጣሬ ገብቷቸው ነበር። በተለይም አፈወርቅ ካቻ የተባለ በኃላ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የተጫወተ ትልቅ ተጫዋች መጀመርያ ላይ ‘በጀት የለንም ምግብ እና ሻወር አንፈቅድም’ ብለውት ራሱ አሰልጣኝ ገዛኸኝ ነው በእኔ በጀት ምግብ ይብላ ሻወርም ይውሰድ ብሎ ወደ ክለቡ ያስገባው። በኃላ እኔም አፈወርቅም በጣም ጥሩ ደረጃ ላይ ደረስን እንደውም አፈወርቅ እስከ ብሔራዊ ቡድን ደረጃ ተጫውቷል። በዚህ አጋጣሚ ነብሱን ይማረው እና አሰልጣኝ ገዛኸኝ ማንያዘዋልን ማመስገን እፈልጋለሁ።”
በእርሻ ሠብል በርካታ አይረሴ አጋጣሚዎችም አሳልፏል። ከነዚህም ውስጥ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ አሰልጣኝ ገዛኸኝ ማንያዘዋል ጥሎት የሄደውን መሰረት አስቀጥለው የሰሩት ጥሩ ቡድን ዘመናዊ አጨዋወትን የሚከተል እንደነበር ይገልፃል። ለአስራ አራት ዓመታት በዘለቀው በእግርኳስ ህይወቱ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና እና የጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን አንስቷል። በ1982 ክለቡ እርሻ ሠብል በኢትዮጵያ ሻምፒዮና በቅዱስ ጊዮርጊስ ተሸንፎ ዋንጫውን ያጣበት ጨዋታም ምንጊዜም ከሚያስቆጩ ጨዋታዎች አንዱ ነበር ይላል።
ከዚህ ውጭም በ1986 ቡድኑ በፋይናንስ ዕጥረት ተቸግሮ ዘግይቶ የቅድመ ውድድር ዝግጅት በመጀመር በሁለት ሳምንት ዝግጅት ብቻ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ያነሳበት ጊዜ በጥሩ ጎኑ የምያስታውሰው አጋጣሚ ነው። ሆኖም ክለቡ በዛው ዓመት መጨረሻ ከሊጉ የወረደበት ወቅትም ነበር። ቡድኑ ቢወርድም ሳምሶን ግን አብሮ ወደ ታችኛው ሊግ በመውረድ ቡድኑ በወረደበት ዓመት ተመልሶ ወደ ዋናው ሊግ እንዲመለስ ከፍተኛ ጥረት ካደረጉት ተጫዋቾች አንዱ ነበር።
በ1988 እና 1989 በእግር ኳስ ህይወቱ የመጨረሻ ዓመታት በልምድ እና በብቃት የተሻለ የበሰለ ተጫዋች እየሆነ ቢመጣም በ1989 መጨረሻ ላይ የወቅቱ ዋና አሰልጠኝ ከአብዛኞቹ ነባር እና አንጋፋ ተጫዋቾች ጋር በፈጠረው ቅራኔ ከክለቡ ጋር ከተለያዩት ተጫዋቾች አንዱ ሆኖ ከአስራ አራት ዓመታት የእርሻ ሠብል ቆይታ በኃላ ከክለቡ ተለያየ። ሁኔታውን ወደ ኃላ መለስ ብሎ ሲያስታውስም የመጫወት አቅሙ እና ፍላጎቱ እያለው ከሚወደው እግርኳስ እንደተለየ ይናገራል። “በወቅቱ አዲስ አሰልጣኝ ሲመጣ ከአንጋፋ እና ነባር ተጫዋቾች ጋር አብሮ መስራት አልቻለም። እኛን አቀራርቦ ጥሩ ቡድን እንደመስራት በተለያዩ ምክንያቶች ከቡድኑ አለ አግባብ እንድንለያይ ሆነ። እኔ የመጫወት አቅሙም ፍላጎቱም ነበረኝ ሆኖም መቆየት አልፈለግኩም በ1990 ላይ ጫማዬን ሰቀልኩ። የክለቡ መጨረሻም በጣም አሳዛኝ ሆነ። ወደ ታችኛው ሊግ ወርዶ መጨረሻ ላይ ሲፈርስም በጣም በጣም ነው ያዘንኩት ፤ ለአስራ አራት ዓመታት የታገልክለት የምትወደው ክለብ እንደ ቀልድ ሲፈርስ ልብ ይሰብራል። የሚያስደንቅ ቡድን ነበር ፤ ደጋፊዎቻችንም ጥቂት የሚባሉ አልነበሩም።
በ1990 ከእግርኳስ ከተለያየ በኃላ በእርሻ ሠብል ድርጅት ፅህፈት ቤት ውስጥ መስራት ጀመረ። ወደ ሦስት ዓመታት የሚጠጉ ጊዜያትም እግርኳስ እርግፍ አድርጎ በመተው የፅህፈት ቤት ስራውን እየሰራ ቢቆይም በጓደኞቹ እና የቅርብ ሰዎች ገፋፊነት ጎን ለጎን የአሰልጣኝነት ኮርሶች መውሰድ ጀመረ። እስከ 1996 ባሉት ጊዜያትም በሥልጠናዎች እና ከአሰልጣኝነት ጋር የተያያዙ ነገሮች እየተከታተለ ቆይቷል።” ወደ አሰልጣኝነት በድፍረት ዘው ብዬ አልገባሁበትም ፤ አሰልጣኝነት መሰጠትን ይጠይቃል። ወደ ሙያው ከመግባቴ በፊት በተጫዋችነት ጊዜዬ ከአሰልጣኞች ጋር ቅርብ ነበርኩ ፤ እንደውም የኃላፊነቱን ውጥረት በደምብ ስለማውቀው አሰልጣኝ መሆን አልመኝም ነበር። በጓደኞቼ ግፊት ነው ሥልጠና የወሰድኩት ጎን ለጎንም ብዙ ዝግጅቶች አድርጌያለሁ። ወደ ሥልጠናውም ደረጃ በደረጃ ነው የገባሁት መጀመርያ በታዳጊዎች ላይ ንነበር እሰራ የነበረው።”
ቀስ በቀስ ረጅም በሚባል የሥልጠና እና ራስን የማብቃት ሂደት ወደ ክለብ አሰልጣኝነት የመጣው ሳምሶን በ1990 እግርኳስ ካቆመ ከስድስት ዓመታት በኃላ በክለብ ደረጃ አራዳ ስፖርት በሚባል በአዲስ አበባ አንደኛ ዲቪዝዮን የሚሳተፍ ክለብ የአሰልጣኝ መርሻ ሚደቅሳ ረዳት ሆኖ ስራውን ጀምሯል። ከዚያ በኋላም በድጋሚወደ ታዳጊዎች እግርኳስ በመመለስ ከአንድ የስዊዘርላንድ ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን ‘ ‘Sport the bridge ‘ በሚባል የታዳጊዎች ፕሮጀክት ለዓመታር ሰርቷል።
በመጀመርያው የአሰልጣኝነት ጊዜው አዲስ ነገር ለማወቅ እና ለመሞከር ትልቅ ጉጉት እንደነበረው የሚናገረው ሳምሶን በ1999 የአሰልጣኝነት ህይወቱ ላይ ትልቅ ዕድል አጋጠመው። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአሰልጣኝ ግርማ ፀጋዬ እና አሸናፊ በቀለ ረዳት አሳልጣኝ ሆኖ ተቀጠረ። ከአንድ ዓመት የንግድ ባንክ ቆይታ በኋላም ወደ ባህርዳር አቅንቶ ከ2000 እስከ 2002 ምዕራብ ዕዝ እግርኳስ ክለብና ባህርዳር ከተማን ሲያሰለጥን ቆየ። ከባህርዳር የተሳኩ ሁለት ዓመታት በኋላም በ2003 ወደ ዓድዋ አምርቶ ለአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ በዋና አሰልጣኝነት ሰርቷል። በአልመዳ አንድ ዓመት ካሰለጠነ በኃላም በድጋሚ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ የማሰልጠን ዕድል አግኝቶ ወደ ሐረር በመጓዝ የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ምክትል በመሆን ስራውን ጀምሯል። ከ2004 እስከ 2006 በሐረር ቢራ በቆየባቸው ሦስት ዓመታት ረዳት አሰልጣኝ ሆኖ ቢጀምርም በኃላ ላይ ዋና አሰልጣኙ ከክለቡ ጋር መለያየቱን ተከትሎ ዋና አሰልጣኝ ለመሆን በቅቷል።
በሂደት በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ዋና አሰልጣኝ ከሆነ በኃላ የነበሩት ፈተናዎችን ደግሞ እንደሚከተለው ታስታውሳቸዋል። ” በሐረር ቢራ በጣም ጥሩ ጊዜ ነበረኝ። በተለይም የመጀመርያው ዓመት ላይ ሊጉን እስከመምራት ደርሰን ነበር። መጨረሻ ላይ ግን የክለቡ ባለቤትነት ወደ ሄይኒከን ቢራ ከተዘዋወረ በኃላ ብዙ ነገሮች ተቀያየሩ። ድርጅቱም በክለቡ ላይ ያለው ትኩረት በመቀነሱ ክለቡም ወረደ። በዚህ አጋጣሚ ዕድሉን የሰጡኝ አቶ ጁነዲን እና ሙሉ የክለቡን አመራሮች ማመስገን እፈልጋለሁ። አቅሜን እንድጠቀም ዕድሉን ሰጥተውኛል ብዙ ጥሩ ስራዎችም ሰርቻለሁ” ይላል።
ከሐረር ቢራ ከተለያየ በኃላም በ2007 ወደ ሌላው የፕሪምየር ሊግ ክለብ ዳሽን ቢራ አምርቷል።
በክለቡ ቆይታውም ጥሩ ጊዜያት ቢያሳልፍም ከክለቡ ጋር ለመለያየትን ብዙ አልቆየም። ምክንያቱን ሲያስረዳም “ከሜዳ ውጪ ያለውን ነገር ብዙ ነገር አሳጥቶኛል። በክለብ አከባቢ ያሉት ነገሮች ትኩረትህን ስራህ ላይ እንዳታደርግ ያደርጋሉ ፤ ከዳሽን በኃላ ብዙ ውጣ ውረዶች ነበሩ። በዳሽን ቢራ ቆይታዬ ምንም ችግር አልነበረኝም። በክለቡ በነበርኩበት ጊዜ አንደኛ ዙር ሰባተኛ ደረጃ ክለቡም ስለቅ ደግሞ አስረኛ ደረጃ ነበር። እንደ አሰልጣኝ መለካት ያለበት በሜዳ ውስጥ ብቃት ነበር። ሆኖም ሌሎች ጣልቃ ገብነቶች ነበሩ። ዞሮ ዞሮ ስለዚህ ጉዳይ ብዙ ማለት አልፈልግም።” ይላል።
ከዳሽን ጋር ከተለያየ በኃላም በድጋሚ ወደ ታዳጊዎች እግርኳስ በመመለስ እስከ 2011 አጋማሽ ድረስ ቆይቷል። በ2011 አጋማሽ ደግሞ ወደ ስሑል ሽረ አምርቶ ወደ ከፍተኛ ሊግ ለመውረድ አንድ እግሩን አስገብቶ የነበረውን ክለብ ከገደል አፋፍ መልሶ በክለቡ ደጋፊ ልብ ውስጥ መቀመጥ ችሏል። ወደ ክለቡ የገባበትን አስገራሚ አጋጣሚም እንዲህ ያስታውሰዋል። ” ወደ ክለቡ የተቀላቀልኩበት አጋጣሚ በጣም አስገራሚ ነው ፤ እኔ በስልክ ብቻ የማውቀው እሱ ግን አቅሜን በደምብ የምያውቀው ዳንኤል አስመለሽ የሚባል ጋዜጠኛ አለ። በእሱ ጥቆማ ነው ወደ ስሑል ሽረ ያቀናሁት። ከስልክ ውጪ ምንም ዓይነት ግንኙነት አልነበረንም። ከዚያ የክለቡ አመራሮች ጊዜ ወስደው ተመለከቱኝ። እነሱ ካመኑብኝ በኃላም ቡድኑን ይዤ ያንን ትልቅ ስራ መስራት ችያለሁ። ስሑል ሽረ በሊጉ እንዲቆይ ያንን ስራ እንድሰራ የመጀመርያ ምክንያት የሆነኝ እና በድጋሚ ወደ አሰልጣኝነት እንድመለስ ያደረገኝ ዳንኤል አስመላሽ ነው። በስሑል ሽረ ቆይታዬ ከረዳት አሰልጣኜ ገብረኪሮስ አማረ ፣ ከደጋፊው ከተጫዋቾቼ ጋር እና ከመላው የክለቡ ቤተሰብ ብዙ ጥሩ ነገር አድርገናል። በሁለተኛው ዙር ውጤታችን ከፋሲል እና መቐለ 70 እንደርታ በኃላ ሦስተኛ ነበር። በመጀመርያው ዓመቴ የተሰራው ተዓምር ነው። በመጀመርያ ዙር ቡድኑ አስራ አንድ ነጥብ ብቻ ነበር የያዘው።” ብሏል።
በወቅቱ አሰልጣኙን የጠቆመው አንጋፋው የትግርኛ የስፖርት ጋዜጠኛ ዳንኤል አስመላሽም ወቅቱን እንዲህ ያስታውሰዋል። ” ክለቡ ችግር ላይ ነበር። በክለቡ ሁኔታ ሁሉም ተጨንቆ ነበር ፤ አመራሮቹ ለሀገር ውስጥ እግርኳስ ቅርብ እንደመሆኔ በአሰልጣኝ ቅጥር ላይ ኃሳብ እንድሰጣቸው አማከሩኝ። እኔም የሳምሶንን ጥንካሬ እና የስራ ፍላጎት ስለማውቅ ቀጥታ እሱን ነበር የጠቆምኩት። እሱም አላሳፈረኝም በጣም ትልቅ ስራ ነው የሰራው። ክለቡም ለሰራው ስራ ዕውቅና እና ምስጋና ሰጥቶታል። እንደአጋጠሚ ከእሱ ጋር ከስልክ ውጪ የቀረበ ግንኙነት አልነበረንም። እኔ ግን አቅሙን አውቀው ነበር።
አቅም እያለው በእግርኳሳችን ባለው መጠላለፍ የተጎዳ አሰልጣኝ ነው። በዚህ አጋጣሚ አመራሮቹ አማክረውኝ አሰልጣኙ ተቀጥሮ ቡድኑ ስለተረፈ በጣም ደስተኛ ነኝ ፤ እሱ እና ረዳት አሰልጣኙ ገብረኪሮስ አማረ ትልቅ ስራ ነው የሰሩት።” ብሏል።
ከስሑል ሽረ ከተለያየ በኃላ ላለፉት ወራት ከክለብ እግርኳስ ርቆ የሚገኘው ሳምሶን አየለ ከአንዳንድ የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ጋር በንግግር ላይ እንደሚገኝ ገልፆ በአጭር ጊዜ ወደ እግርኳሱ እንደሚመለስ አስታውቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!