“ከምንተስኖት ውጪ አብዛኞቹ የብሔራዊ ቡድኑ ግብ ጠባቂዎች ኪሎ ጨምረው ነው የመጡት”

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ የብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂዎችን በተመለከተ ሀሳባቸውን ሠጥተዋል።

ዛሬ ከሰዓት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በተመለከተ በዋና እና ረዳት አሠልጣኞቹ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል። በመግለጫውም ዋና አሠልጣኙ ቡድኑን በተመለከተ ገለፃዎች ካደረጉ በኋላ የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ የሆኑን ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ በስብስቡ የሚገኙ እና የተቀነሱ የግብ ዘቦችን በተመለከተ ጥያቄ ቀርቦላቸው ተከታዩን ሀሳብ ለጋዜጠኞች ሰጥተዋል።

“ከተቀነሱት ግብ ጠባቂዎች ከአንዱ ጋር ፀብ ውስጥ ገብተካል የሚባለው ነገር ውሸት ነው። እኔ ምንም የማውቀው ነገር የለም። እኔ ወደ ብሔራዊ ቡድኑ የመጣሁት ያለኝን እውቀት እና ልምድ ለተጫዋቾቹ ለማጋራት ነው። ተጫዋቾቹም የምሠጣቸውን ልምምድ ተመችቷቸው ተቀብለዋል። ምንም የተፈጠረ ነገር የለም። ከተቀነሱት ጋርም ምንም አልተፈጠረም። አቤልም ሆነ ሰዒድ የተቀነሱት በምክንያት ነው። በተለይ ሰዒድ ጎበዝ ግብ ጠባቂ እንደሆነ እናውቃለን ግን ልምድ ስለሌለው ቀንሰነዋል። ግን ለወደፊት ሀገራችንን የሚጠቅም ምርጥ እና ጎበዝ ግብ ጠባቂ ነው። በአጠቃላይ ከተቀነሱት ጋር በሠላም ነው የተለያየነው። ሲጀምር ከምንተስኖት ውጪ አብዛኞቹ ግብ ጠባቂዎች ኪሎ ጨምረው ነው የመጡት። እኛም ወደ አቋማቸው እንዲመለሱ ነገርግን ጉዳት እንዳያስተናግዱ ተጠንቅቀን ቀለል ያሉ ልምምዶችን ስናሰራቸው ነበር። ከዛምቢያው የወዳጅነት ጨዋታ በኋላ ግን ጠንከር ያሉ ስራዎችን እያሰራናቸው እየተሻሻሉ ይገኛሉ። በጨዋታው ላይም የታዩትን ክፍተቶች የሚያርሙ ስራዎችን ሰርተናል። በአጠቃላይ አሁን ያሉን ግብ ጠባቂዎች ልምምድ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ከዕለት ዕለት እየተሻሻሉ ነው የመጡት።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!