ስለ ጸጋዘአብ አስገዶም ሊያውቋቸው የሚገባቸው እውነታዎች

በሜዳ ላይ ቡድን ከመምራት ውጪ ከአንደበቱ ክፉ የማይወጣው እና በጣም የተረጋጋው ሰው እንደሆነ ብዙዎች የሚመሰክሩለት በዘጠናዎቹ ውስጥ ከተመለከትናቸው ድንቅ ግብ ጠባቂዎች መካከል የሚመደበው ጸጋዘአብ አስገዶም ማነው ?

አስመራ ከተማ ውስጥ ወጣቶች ተሰባስበው በየቀበሌያቸው ውድድሮች የማድረግ ልምድ ነበራቸው። በአንድ የቀበሌ ተወካይ ቡድን ውስጥ ታዲያ ግብጠባቂው የቀን ስራ ያገኝና ኑሮን ለማሸነፍ ሲል ሥራው በልጦበት በጨዋታ ቀን ይቀራል። በዚህ ግብጠባቂ መጉደል ግራ የተጋባው አሰልጣኝ ሌለ ቅያሪ ግብጠባቂ ፈልጎ ሳያገኝ ቀረ። ታዲያ ሁሉም ተጫዋቾች ግብጠባቂ ላለመሆን ይሸሹ ጀመር፡፡ ሆኖም ከተጫዋቾቹ መሀል አንዱን “አንተ ከሌሎቹ ደፋር ስለሆንክ ግብጠባቂ ሁን” ይለዋል። ተጫዋቹ በተቃውሞ “እኔ እግርኳስ ተጫዋች እንጂ ግብጠባቂ መሆን አልፈልግም” በማለት ከአሰልጣኙ ጋር ከመከራከር አልፎ ግብጠባቂ ላለመሆን እስከ ማልቀስ ሁሉ ይደርሳል። ሆኖም በወቅቱ የሚጫወትበት ቀበሌ ሊቀመንበር በተለያዩ መንገዶች ጫና ውስጥ እንደሚከቱት ተረድቶ ሳይፈልግ የሊቀመንበሩን ትዕዛዝ አክብሮ ግብጠባቂ ይሆናል። ይህ በእንዲህ ሆኖ ካለፈ በኃላ በየጨዋታዎቹ የሚያሳየውን ድንቅ ብቃት ብዙዎች እየወደዱለት በአጋጣሚ በጀመረው ግብጠባቂነት ከቀበሌ አልፎ እስከ ብሔራዊ ቡድን ድረስ መጫወት የቻለው የዛሬው የዘጠናዎቹ ኮከብ ዕንግዳችን ጸጋዘአብ አስገዶም ነው።

በቀበሌ የጀመረው የግብጠባቂነት ህይወቱ ወደ ክለብ ተሻግሮ ለአስመራው ታላቅ ቡድን አዱሊስ መጫወት ጀምሯል። ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ለጉምሩክ ሲጫወት ያሳየው ጥሩ እንቅስቃሴ በ1985 ለወጣት ብሔራዊ ቡድን እንዲመረጥ አስችሎት በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ እስከ መጨረሻው ምዕራፍ ጫፍ ደርሶ በካሜሮን ተሸንፎ በወደቀው እና አፍሪካን የሚወክሉው ሦስት ሀገራት በመሆናቸው ምክንያት ኢትዮጵያ አራተኛ ሆና በማጠናቀቋ ሳይሳካለት በቀረው ቡድን ውስጥ አባል ነበር። በመቀጠል ከጉምሩክ በኋላ ትልቅ ስም እና ዕውቅና ወዳገኘበት መብራት ኃይል ክለብ በ1990 በማምራት ለአስር ዓመታት እጅግ ስኬታማ የነበረ ቆይታ አድርጓል። መብራት ኃይል በ1990 የመጀመርያውን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ሲያነሳ እንዲሁም በ1993 የሦስትዮሽ ዋንጫ ክብርን ሲቀዳጅ የቡድኑ ግብጠባቂ ነበር።

በመብራት ኃይል እና በብሔራዊ ቡድን አብሮት የተጫወተው የቀድሞ ግብጠባቂ ደያስ አዱኛ ስለ ፀጋዘአብ ይሄን ይናገራል ” ከፀጋ ጋር በመብራት ኃይል አብረን ቆይታ አድርገናል። በጣም የማከብረው እና የማደንቀው ፤ ለእሱ ትልቅ ክብር ያለኝ ሰው ነው። በችሎታው በተለይ የታይሚንግ አጠባበቁን በጣም ነው የምወድለት ፤ ከዛም አልፎ ጥሩ ችሎታ ነበረው። ከእርሱ ብዙ ትምህርት አግኝቻለሁ። በጣም ትልቅ በረኛ ነው። በፀባዩም እንደዛው ፤ በጣም ሰው አክባሪ ለተጫዋቾች ምሳሌ መሆን የሚችል ትልቅ ሰው ነው። ለእኔ ደግሞ ባለውለታዬ የሆነ ትልቅ ግብጠባቂ ነው።”

ከአስር ዓመታት የኤሌክትሪክ ቤት ቆይታ በኋላ በምስራቋ አዳማ ከተማ ለአጭር ጊዜ ተጫውቶ በመቀጠል ሙገርን ተቀላቅሎ ሳለ በእግሩ ላይ ባጋጠመው ከፍተኛ ጉዳት የህክምና ባለሙያው ከዚህ በኋላ መጫወት እንደማይችል በገለፀለት መሠረት በ2001 ጓንቱን በመስቀል ወደ ሌላ ምዕራፍ ሊሻገር ችሏል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሁሉም ዕድሜ እርከኖች መጫወት የቻለው አመለሸጋው ፀጋዘአብ በተለይ በ1989 የአፍሪካ ዋንጫ ምድብ ውስጥ ለመግባት ከዮጋንዳ ጋር በነበረው ጨዋታ እርሱ ባዳነው መለያ ምት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ምድብ ድልድል ውስጥ የገባች ሲሆን በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ 1994 ላይ ከሀገር ውጪ የመካከለኛው እና ምስራቅ አፍሪካ ዋንጫን ሩዋንዳ ላይ ስታነሳም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡

ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ በግብ ጠባቂነት ያገኘውን ልምዱን በሚገባ በተረዱት እና ወደፊት ሊሰጥ የሚችለውን ጠቀሜታ ከግምት ባስገቡት ገብረመድህን ኃይሌ ጥቆማ በኮሎኔል ዐወል መልካም ፍቃድ ከ2003 ጀምሮ የደደቢት የግብጠባቂዎች አሰልጣኝነት ሥራውን ጀምሯል። ከደደቢት ጋር የግብጠባቂነት አሰልጣኝነቱ ጊዜ የ2005 የፕሪሚየር ሊጉ ቻምፒዮን በመሆን በተጫዋችነት እና በአሰልጣኝነት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ያነሳ ባለታሪክ መሆን ችሏል። ደደቢት በ2010 ሙሉ ለሙሉ ተጠቃሎ ወደ መቐለ ሲጓዝ ደግሞ የኢትዮጵያ ቡና የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ በመሆን እስካሁን እያገለገለ ይገኛል።

አንጋፋው ጋዜጠኛ ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) ስለ ፀጋዘአብ ሲናገር “በጣም ጎበዝ በረኛ ነው። እኔ ራሴ ፍፁም ቅጣት ምት ስቼበታለሁ። ሜታ እና አዱሊስ ለኢትዮጵያ ቻምፒዮና ስንጫወት ቆሞ ጠብቆኝ አድኖብኛል። ፀጋ በተለይ ሪጎሬ የማዳን ችሎታ ነበረው። ቡድን ከመምራት ውጪ ከአንደበቱ ምንም ክፉ ቃል የማይወጣው ፣ የትም ቦታ የማይታይ ፣ ድምፁ የማይሰማ ተጫዋች ነው። በአጠቃላይ ካየኋቸው ተጫዋቾች ሁሉ በጣም ጨዋ ተጨዋች ብዬ የምሰክርለት ፀጋን ነው።” በማለት ይናገራል።

በክለብ ያላበቃው የግብ ጠባቂ አሰልጣኝነቱ ጉዞ ወደ ብሔራዊ ቡድን ተሻግሮ ከ20 ዓመት በታች እና የዋናው የሴቶች ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ዘመን የወንዶች ብሔራዊ ቡድን የግብጠባቂዎች አሰልጣኝ ሆኖ አገልግሏል። በመልካም ስብዕና የተሞላው በዘጠናዎቹ ከተመለከትናቸው ምርጥ ግብ ጠባቂዎች ውስጥ የሚመደበው ፀጋዘአብ አስገዶም በዛሬው አምዳችን ከኛ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንድታነቡ ጋብዘናል።

“ግብጠባቂ በነበርኩባቸው ረጅም ዓመታት በሙያው ብዙ ሰው አፍርቼበታለሁ። በአቅምም የተወሰነ ተጠቅሜበታለሁ። ከምንም በላይ ግን በምወደው ሙያ በማሳለፌ እና በጣም ስኬታማ መሆኔ ያስደስተኛል። ስኬት ከዋንጫ ጋር ከሆነ ደግሞ ከኤልፓ ጋር ሁለት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ፣ ከብሔራዊ ቡድን ጋር የሴካፋ ዋንጫ እንዲሁም አሰልጣኝ ሆኜ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ከደደቢት ጋር ማንሳቴ ሌላው ስኬቴ ነው።

“አሁን ላይ ሆኜ ብዙ የምቆጭበት ነገር አለ። የዛኔ ተጫዋች ሆኜ የማይገቡኝ ነገሮች አሁን ላይ ሆኜ ወደ ኋላ ሳስባቸው ብዙ የሚገቡኝ ጉዳዮች አሉ። በተለይ አሰልጣኝ ስሆን በተጫዋችነቴ ብዙ ነገር እንዳላደረኩኝ ገብቶኛል። ብዙ መስራት እየቻልን በስንፍና ሳንሰራቸው የቀረናቸው ነገሮች አሉ። ራሳችንን መለወጥ እየቻልን ሳንሰራ የቀረነው ነገር ይቆጨኛል።

“በእኛ ዘመን ለመምረጥ የምትቸገርበት በጣም ተቀራራቢ አቋም ያላቸው ግብ ጠባቂዎች ነበሩ። በነገራችን ላይ አሁንም በረኛ የለም ማለት አይደለም። በረኞች አሉ ! ችግር እየሆነ ያለው ምን እንደሆነ ታውቃለህ ? ክለቦች የውጪ ግብ ጠባቂ ጥገኛ መሆናቸው ነው። በእኛ ዘመን ግብጠባቂ የምትሆነው የግብጠባቂ አሰልጣኝ ኖሮ አይደለም። የሚያሰለጥንህ ጨዋታ ነበር። በተደጋጋሚ የጨዋታ ዕድል ስለምናገኝ እየተሳሳትን በቀጣይ እያረምን ጥሩ እየተሻሻልን እየተለወጥን ሄደናል። አሁን ግን አንድ ኢትዮጵያዊ ግብጠባቂ ሲሳሳት ከየትም ይሁን ከየት መጥተው የውጪ ግብ ጠባቂዎች እንዲገቡ ይድረጋል። ይህ ደግሞ የትም አያደርሰንም። በእኛ ጊዜ ግን የውጪ በረኛ ስለሌለ እና በአንድ ጨዋታ ብንሳሳት የምናጣው ብዙ ነገር ስለለ ሌሎች ተቀያሪ ወንበር ላይ የተቀመጡ ጠንካራ ልጆች ስለሚጠብቁንም ተጠባባቂ ወንበር ላይ ላለመውረድ ጠንክረን በመስራታችን ይመስለኛል ብዙ ግብ ጠባቂዎች እንዲኖሩ ያደረገው።

“የውጪ ግብጠባቂን በተመለከተ ስንት ዓመት በተጠባባቂ ወንበር የተቀመጠ የውጪ ሀገር ግብ ጠባቂ ስለሆነ ብቻ በማጫወት በኢትዮጵያውያን በረኞች ሞራል የሚቀልዱ አሉ። በዚህ ምክንያት ብዙ በረኞች በዚህ ዘመን እንዳይወጡ ሆኗል እንጂ በጣም ጥሩ ጥሩ ልጆች አሉ። በረኛን ሀምሳ ጊዜ ልምምድ ላይ ብታሰራው ጥሩ በረኛ ላይሆን ይችላል። ግን አንድ በረኛ ጥሩ የሚሆነው በጨዋታ ላይ ነው። ጨዋታ በራሱ ራሱን የቻለ ሥልጠና ነው። ከጨዋታ ጨዋታ ራስህን እያሻሻልክ እየለወጥክ የምትሄድበት ነው። አሁን እኮ የእኛ ሀገር በረኞች መቼ ወደ ጨዋታ ገቡ እና ነው አቅማቻውን እያዳበሩ እንዲሄዱ የሚጠበቀው ? አሁን ሁሉም ክለብ የኢትዮጵያ ቡናን መንገድ መከተል አለበት ባይ ነኝ።

” የብሔራዊ ቡድን ቆይታዬ በጣም ረጅም ነው ፤ በዚህም ደስተኛ ነኝ። በብሔራዊ ቡድን ቆይታዬ መቼም የማረሳው በ1994 ሩዋንዳ ላይ በተካሄደው የሴካፋ ዋንጫ ላይ ከኬንያ ጋር የነበረውን የፍፃሜ ጨዋታ መጫወቴን ነው። በዚህ በጣም ደስተኛ ብሆንም የዛኑ ያህል በብሔራዊ ቡድን የማዝነው በሱማሊያ አንድ ለዜሮ ስንሸነፍ ተሰላፊ የነበርኩ በመሆኔ ነው።

“አዲስ አበባ ውስጥ በ1984 ባቡር የሚባል ቡድን ነበር። እንደ አጋጣሚ ሆኖ በዚህ ዘመን አንድ ቡድን ወደ ታች ከወረደ ይፈርስ ነበር። በዚህ ምክንያት ላለመውረድ የነበረው ፉክክር ከፍተኛ ነበር። እኔ ለጉምሩክ እጫወት ነበር። ከባቡር ጋር በምናደርገው ጨዋታ ወደ ታችም አንወርድም ወደ ላይም አንወጣም ነበር ፤ ይህ ጨዋታ ለኛ ትርጉም አልነበረውም። ባቡር ደግሞ እኛን ካሸነፈ ነው መትረፍ የሚችለው ፤ ከተሸነፈ መውረዱ ነው። ‘በቃ ጨዋታው ለኛ አያስፈልግም እንልቀቅላቸው’ ብለን እየተጫወትን ነው። ዳኛው ደግሞ ኪነ ነበር ፤ እርሱም ልንለቅላቸው እንዳሰብን አውቆ ለቀቅ አድርጎ ያጫውት ጀመር። በኋላ ላይ ባቡሮች ፍፁም ቅጣት ምት ያገኛሉ። ሊመታ የመጣውን ‘ወዴት ልሂድልህ ?’ አልኩት። እርሱም ‘ወደ ቀኝ ሂድ’ አለኝ። እኔ ከአስመራ ገና እንደመጣሁ ስለነበር ብዙም አማርኛ አላውቅም ነበር። በእጅ ምልክት ‘በእዚህ ልውደቅልህ ?’ ስለው ‘እሺ’ አለ። ከዚያ ሲመታ ኳሱን ደረቴ ላይ ሰጠኝ። በዚህ ሰዓት ሌሎቹ እኔ የያዝኩባቸው መስሏቸው እኔን ይሰድቡኛል። እርሱ ደግሞ ተንበርክኮ ‘ኧረ እርሱ አይደለም የኔ ጥፋት ነው ኡ’ እያለ እየጮኸ ያለቀሰበትን አጋጣሚ መቼም አልረሳውም።

” እየተጫወትኩም በረኞችን አሰራ ነበር ፤ እንደምታቀው በእኛ ዘመን የግ ብጠባቂ አሰልጣኝ አልነበረም። ሁላችንም በራሳችን ልፋት እና ጥረት ነው በትልቅ ደረጃ እንድንጫወት የሆንነው። ሆኖም ግን በውስጤ ምን ዓይነት አቅም እንዳለ በወቅቱ ባልረዳም በረኞችን ሰብስቤ እየተጫወትኩ አሰለጥን ነበር። ለምሳሌ ሙገር እያለው ቢንያም (ኦሼ) ፣ ዮሐንስ ሽኩር ፣ መብራት ኃይል ቅጣው በሌለበት ወቅት ደያስ አዱኛን አሰራው ነበር። ይህን ሳደርግ ገብረመድን ኃይሌ ያይ ስለነበር ደደቢት የግብጠባቂ አሰልጣኝ ለመቅጠር ማንን ላድርግ ብሎ ኮነሬል ዐወል ገብሬን ሲጠይቀው እኔ እንድሆን ነገረው በዚህ አጋጣሚም ወደ አሰልጣኝነቱ ልገባ ችያለሁ።

“እኛ ሀገር የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ኮርስ እየተሰጠ አይደለም። ይህ የሆነው ትኩረት ካለመስጠት የተነሳ ይመሰለኛል። በዘመናዊ እግርኳስ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ሥልጠና በስፋት ይሰጣል። እኛ ሀገር ብዙም የለም። በተጫዋችነት ዘመናችን ካሳለፍነው እና ከገጠመን ነገር ተነስተን እንጂ በተሰጠን ሥልጠና ያገኘነው ነገር የለም።

“ስለራሴ ማውራት በጣም ከባድ ነው። ብችል እና ብናገር ደስ ባለኝ ነበር። እርጋታው እና ዝምተኝነቱን በተፈጥሮ ያገኘሁት ይመስለኛል። ያው ብዙ ጊዜ ተጫውተህ ስታልፍ ሜዳ ላይ ካጋጠሙህ ነገሮች ካየኸውም በጣም ጥሩም በጣም መጥፎም ነገሮች ስለምታልፍ ከእነርሱ የምትወስደው ትምህርት ይሆናል። አብዛኛው ግን በተፈጥሮ ያገኘሁት ይመስለኛል።

“እኔ ካየኋቸው ግብጠባቂዎች ትልቅ ቦታ የምሰጠው ለደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ ነው። ምን አልባት በጣም አውቄው ከህፃንነቴ ጀምሮ አይቼው ያደግኩት እርሱን ስለሆነ ይመሰልኛል። ደሳለኝ አንድ ለአንድ ሲገናኝ ፣ ከኃላ ቡድን ሲመራ ፣ ቁመናው ፣ ሁሉ ነገሩ ምርጥ የሆነ እንደ አርዓያ የምከተው በኢትዮጵያ ምርጡ ግብ ጠባቂ ነው።

“በቤተሰብ ህይወቴ ባለትዳር እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነኝ። በ2011 ከሀሌታ ቡድን ጋር ከ17 ዓመት በታች ውድድር ላይ በአማካይ ስፍራ ተጫውቷል። እንደኔ ግብ ጠባቂ አልሆነም። ራሱ በመረጠው መንገድ መጓዝ ችሏል። ልጅ ‘ይህ መንገድ ነው የሚያወጣኝ’ እያለ አንተ በዚህ ሂድ አትለውም። የራሱን ፍላጎት ታከብርለታለህ ፣ ታግዘዋለህ። ዓምና የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተፈታኝ በመሆኑ ትምህርቱ ላይ ትኩረት አድርጎ ፈተናውን ከጨረሰ በኃላ ወደ ኳሱ ይገባል ብዬ ዓምና በየትኛውም ክለብ አልተጫወተም። ምናልባት ዓምና በኮሮና ምክንያት ትምህርት ባይቋረጥ ኖሮ ዘንድሮ አንዱ ክለብ ጋር ይገባል ብዬ ነበር።
“በመጨረሻ ለግብ ጠባቂዎች ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት በተቻለ መጠን የተረጋጉ እንዲሆኑ ነው። በረኝነት መውደቅ ብቻ የሚመስላቸው አሉ። በረኝነት ተረጋግቶ ፣ አይቶ መጫወት ነው። ስለዚህ እንዲረጋጉ ፣ ራዕይ እንዲኖራቸው ፣ ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ማድረግ ያለባቸው ማወቅ አለባቸው። ከዚህ በተጨማሪ ሊሰማቸው ይገባል። ‘ለምንድነው በውጪ ግብ ጠባቂዎች የሚታመነው ፣ በእኛ ለምን አይታመንም ?’ በሚል ሊቆረቆሩ ይገባል። ይህ እልህ ይዟቸው እነርሱን ለመጣል ጥሩ ነገር ቢሰሩ ብዙዎችን ማሳመን ይችሉ ነበር እላለሁ።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!